የካሜሮን ወታደሮች ሴቶችን "በብቀላ መድፈራቸውን" አንድ ሪፖርት አጋለጠ

የካሜሮን ወታደር መለዮ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የካሜሮን ወታደሮች ሴቶችን በብቀላ መድፈራቸውን አንድ ሪፖርት አጋለጠ።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት ሂውማን ራይትስ ዋች ከሰሞኑ የካሜሮን ወታደሮች በአንድ መንደር ውስጥ 20 ሴቶች መድፈራቸውን አረጋግጧል። ወታደሮቹ ጥቃቱን ያደረሱት ከአመት በፊት ሲሆን ድርጅቱ የብቀላ ጥቃት ብሎታል።

ጥቃቱ የደረሰው እንግሊዝኛ ተናጋሪ በሆኑት የደቡብ ምዕራቧ ግዛት ኢባም ሲሆን በአካባቢው ተገንጣዮች ነፃ ሃገር ለመመስረት የሚታገሉባት ናት።

ድርጅቱ እንዳለው ይህ የመደፈር ጥቃት በካሜሮን ጦር የተፈፀመ አንዱ አሰቃቂ ጥቃት ነው ብሎታል።

ይህ ወሲባዊ ጥቃት ሪፖርት እንዳልተደረገ በይፋ ያስታወቀው ድርጅቱ፤ ተጠቂዎቹ ከሰፈነባቸው ፍራቻ እንደሆነም አስታውቋል። ሂውማን ራይትስ ዋች አክሎም ምንም እንኳን መጠነ ሰፊ ጥቃት ቢደርስም ምርመራ አልተከፈተም ብሏል።

"በኢባም በርካታ ሴቶች መደፈራቸው ከተረጋገጠ አንድ አመት ሆኖታል። ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ካሳና ፍትህን ይፈልጋሉ። በተፃራሪው ጥቃት ያደረሱት ግለሰቦች ያለ ምንም ክትያ በነፃነት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ሲያዉቁ የሚሰማቸውን ማሰብ ትችላላችሁ" በማለት የድርጅቱ ሰራተኛ ኢዳ ሳውየር በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

የሂውማን ራይትስ ዋች ሪፖርት ምርመራውን መሰረት ያደረገው ከነሃሴ እስከ ጥር ባለው ወቅት ተጠቂዎችን፣ የአይን እማኞችን እንዲሁም ለተጠቂዎቹ ህክምና ያደረጉላቸውን የህክምና ባለሙያዎችን ነው።

የአይን እማኞች ለዶክተሮቹ እንደተናገሩት 50 የሚሆኑ ወታደሮች በባለፈው አመት መጋቢት ወር ላይ ከሌሊቱ 9 ሰዓት በኢባም መንደር የሚገኙ 75 ቤቶችን ሰብረው ገብተዋል።

የተወሰኑት ወታደሮች የአካባቢውን ነዋሪዎች ወንዶች የከበቡ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ሴቶቹን መድፈራቸውን ተናግረዋል። ወሲባዊ ጥቃት ከደረሰባቸው መካከል አራቱ የአካል ጉዳተኞች ናቸው ተብሏል።

ወንዶቹም በቁጥጥር ስር ውለው ከፍተኛ ድብደባ የደረሰባቸው ሲሆን አንድ የ34 አመት ግለሰብም በጫካ ውስጥ በወታደሮች መገደሉን ድርጅቱ አስታውቋል።

"አምስት ጭምብል የለበሱ ወታደሮች ቤቴ ውስጥ ገቡ። ጨለማ ነበር፤ ብቻዬንም ነበርኩ። ቤቴን ከፈተሹ በኋላ ስልኬንና ገንዘቤን ወሰዱ። ከዚያም አንደኛው ከኔ ጋር ወሲብ ካልፈፀምሽ እገልሻለሁ አለኝ" በማለት የ40 አመቷ ግለሰበ ለሂውማን ራይትስ ዋች ተናግራለች።

አክላም "ጥቃቱ ከደረሰብኝ በኋላ ምንም ነገር ለማድረግ ፈራሁኝ። ጫካ ውስጥ ገብቼ ለሁለት ወራት ያህል ቆየሁ። አሁንም በጣም ነው የምበሳጨው ህመም ይሰማኛል" ብላለች።

የአይን እማኞች እንደሚሉት ወታደራዊ ዘመቻው ተገንጣይ ቡድኖችን የሚደግፉ ንፁሃን ዜጎች ላይ ያነጣጠረ በቀል ነው።

የጦሩ ቃለ አቀባይ በበኩላቸው ሪፖርቱ ተቀባይነት የለውም ሲሉ አጣጥለውታል።

የካሜሮን እንግሊዝኛ ተናጋሪ መብት ተሟጋቾች ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው የፈረንሳይኛ ተናጋሪ ነዋሪዎች እንደሚገለሉ ይናገራሉ።

በሰሜንና ደቡብ ምዕራብ በሚገኙ ግዛቶች የሚንቀሳቀሰው የተገንጣይ ቡድን ምክንያት ከአውሮፓውያነኑ 2016 ጀምሮ ከ3 ሺህ 500 በላይ ነዋሪዎችን ህይወት እንደቀጠፈ ድርጅቱ አስታውቋል።

ተገንጣዩም ቡድን ሆነ የመንግሥት ወታደሮች በአገሪቷ ውስጥ በሚደርሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ይወነጀላሉ።