አማራ ክልል፡ "የትግራይ ክልል ጥያቄ ካለው ለፌደራል መንግሥት ማቅረብ ይችላል"

አቶ ግዛቸው ሙሉነህ
የምስሉ መግለጫ,

አቶ ግዛቸው ሙሉነህ

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የወልቃይትና የራያ አካባቢዎችን በተመለከተ ያሚያቀርበው ጥያቄ ካለ በሕጋዊ መንገድ ማቅረብ ይችላል ሲል የአማራ ክልል አስታወቀ።

የአማራ ክልል የመንግሥት ጉዳዮች ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሚያነሳው ጥያቄ ተገቢነት የሌለው ክስ እና ውሃ የማይቋጥር ነው" ብለዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብረ መስቀል ካሳ በአማራ ክልል ኃይሎች የክልሉ ግዛቶች መያዛቸውን ገልጸው፤ አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ በተደጋጋሚ መጠየቃቸውን ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

በአማራ ክልል በኩል በወልቃይትና በራያ አካባቢዎች ቀደም ሲል አንስቶ የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች ሲነሱ የቆዩ መሆናቸውን ያስታወሱት አቶ ግዛቸው፣ ለዚህ የሕዝብ ነው ላሉት ጥያቄ "በሕገ-መንግሥቱ መሠረት ምላሽ ሳይሰጥ መቆየቱን" ይናገራሉ።

በጥቅምት ወር መጨረሻ በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ ከፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ጋር የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ተሰማርቶ እንደነበር የሚታወስ ነው።

ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የህወሓት ኃይሎች በቅራቅር እና በሶሮቃ በኩል የከፈቱትን ጥቃት ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ "በተደራጀ መልኩ" መመከት ችለዋል ሲሉ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ አስታውሰዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የኤርትራ ሠራዊት እና የአማራ ክልል ኃይል ከትግራይ ክልል እንዲወጡ በቅርቡ ባወጣው መግለጫ ላይ ጠይቋል።

ኃላፊው የክልሉ መንግሥት እነዚህን የራያና የወልቃይት አካባቢዎች በጊዜያዊነት እያስተዳደረ መሆኑን ገልፀው ሕግ የማስከበሩ ሥራ መቀጠሉን፣ የዕለት እርዳታ ማቅረብ እና የመንግሥት ተቋማትን መልሶ ማደራጀትና ሥራ እንዲጀምሩ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

እንደ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ገለጻ ከሆነ በአካባቢው አሁንም የሕግ ማስከበር ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸው የመንግሥት ተቋማት ወደ ሥራ እንዲገቡም ጥረት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

ኃላፊው አካባቢዎቹን በኃይል መያዝ ሕገ-መንግሥቱን አይጻረርም? ተብለው ተጠይቀው በየትኛውም ዓለም አቀፍ ሕግ ቢለካ ሕገ መንግሥቱን የሚጻረር ተግባር አይደለም ሲሉ መልሰዋል።

ይህንንም ሲያስረዱ "ከመጀመሪያው በሕገ-መንግሥት ወይንም በአዋጅ የተወሰዱ ቦታዎች አይደሉም" በማለት በአሁኑ ወቅት የትግራይ ክልል "ጥያቄ ካለው በሕጋዊ መልክ ማቅረብ ይችላል" ብለዋል።

ጨምረውም የአማራ ክልል አካባቢውን በጊዜያዊነት እያስተዳደረው መሆኑን ገልፀው የፌደራል መንግሥቱ በዘላቂነት መፍትሄ እንዲሰጠው ጥያቄያችን ይቀጥላል ብለዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የጽህፈት ቤት ኃላፊ በአማራ ክልል ኃይሎች የክልሉ ግዛቶች መያዛቸውን ገልጸው፤ "አስተዳደሩ ህወሓት ያስተዳድረው ከነበረው ግዛት በሴንቲሜትር የቀነሰ ክልልን አያስተዳድርም" ብለዋል።

አቶ ገብረ መስቀል እንዳሉት ጊዜያዊ አስተዳደሩ በሕገ መንግሥቱ ላይ የተገለጸውን የትግራይ ክልልን እንደሚያስተዳድር ገልጸው፤ "እነዚህን ቦታዎች ከሕግ ውጪ የያዙ ኃይሎች የአገሪቱን ሕገ መንግሥት እየተጻረሩ ነው" ብለዋል።

እንደ አማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ደግሞ "በሕግ ማስከበሩ ሂደት" ውስጥ እነዚህ የማንነት እና የወሰን ጥያቄዎችን "እግረ መንገዱን መልስ ሰጥቷል" ብለዋል።

"በጉልበት ተወስዷል፤ በጉልበት ተመልሷል፤ በኃይል ተነጥቀናል በኃይል አስመልሰናል" ባሉት በዚህ እርምጃ "የተጠቀሱት አካባቢዎች የአማራ እንጂ የትግራይ አይደሉም፤ በዚህ ጉዳይ ላይ የውጭ ኃይልም ሆነ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጣልቃ ሊገባብን አይገባም" ብለዋል።

አጠቃላዩ ምዕራባዊ የትግራይ ክፍል እንዲሁም በደቡብ አላማጣ፣ ኮረምና ሌሎች የገጠር አካባቢዎች በአሁኑ ጊዜ በአማራ ክልል ስር መሆናቸውን ያመለከቱት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ፤ ይህም ለፌደራል መንግሥቱ ሪፖርት ተደርጎ ኃይሎቹ ከአካባቢዎቹ እንዲወጡ በተደጋጋሚ መጠየቃቸውን ገልጸዋል።

"ግፊት የምናደርገው የተሰማራው ኃይል እንዲወጣ ብቻ ሳይሆን በአካባቢዎቹ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እንዲቆሙና ፈጻሚዎቹ በሕግ እንዲጠየቁ ነው" ሲሉ አቶ ገብረ መስቀል ተናግረዋል።

አቶ ግዛቸው "የትግራይ ክልል ቦታዎቹ የእኔ ናቸው፣ ይገባኛል የሚል ከሆነ አሰራሩን ተከትሎ በሕጋዊ መንገድ ይጠየቅ" በማለት የአማራ ክልልም "ሕጋዊ አካሄዱን ይቀጥላል" ብለዋል።

ወልቃይት፣ ጠለምት፣ ሰቲት ሁመራ፣ ራያ፣ አላማጣ፣ ኮረም አካባቢዎች በአማራ ክልል መንግሥት ስር መሆናቸውን ኃላፊው አረጋግጠው፤ "በእነዚህ አካባቢዎች ያለው ሕዝብ ነጻነቱን በኃይል አውጇል" ብለዋል።

በተጠቀሱት አካባቢዎች ባሉ የትግራይ ተወላጆች ላይ በደል ተፈጽሟል እንዲፈናቀሉም ተደርጓል በሚል ለቀረበው ክስም አቶ ግዛቸው ሲመልሱ "የትግራይ ተወላጆችም ከአማራ ሕዝብ ጋር አብረው የኖሩ አብረውም የሚኖሩ ናቸው። አንድም የትግራይ ተወላጅ እንዲገፋ አልተደረገም" በማለት በአካባቢው ባሉ የሥራ እድሎች ማንንም ሳይለዩ ቅጥር መፈፀማቸውን ተናግረዋል።

ነገር ግን ግጭት ሲከሰት መፈናቀል የማይቀር ነው ያሉት ኃላፊው፤ ከአካባቢው ተፈናቅለው የነበሩት ነዋሪዎች እንዲመለሱ የክልሉ መስተዳደር አስፈላጊውን ሥራ እያከናወነ ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል እነዚህን የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው አካባቢዎች "በህወሓት የአስተዳዳር ዘመን በኃይል የተወሰዱ ናቸው ይመለስልኝ ሲል ለዓመታት ጥያቄ ሲያቀርብ መቆየቱን" አቶ ግዛቸው ገልጸዋል።

ጨምረውም በወቅቱም በአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ላይ መፈናቀልና ከዚያም ያባሱ በደሎች ተፈጽመዋል በማለት "አሁን ሕዝቡ ከዚህ አፈና ነጻ ወጥቷል" ብለዋል።

በመሆኑም ጥያቄውን ሕጋዊ ለማድረግ ከፌደራል መንግሥት ጋር እየተነጋገሩ እንደሆነ የገለፁት ኃላፊው፤ ከዚህ ጋር በተያያዘ ክልሉ በሕዝቡ ጥያቄ ላይ እንደማይደራደር ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የህወሓት ኃይሎች ትግራይ ውስጥ በሚገኘው የአገሪቱ ሠራዊት ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወታደራዊ ዕርምጃ እንዲወሰድ ማዘዛቸው ይታወሳል።

ለሦስት ሳምንታት በተካሄደ ወታደራዊ ዘመቻ የፌደራሉ ሠራዊት የክልሉን ዋና ከተማ መቀለን ሲቆጣጠር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተካሄደው "ሕግ የማስከበር ዘመቻ" መጠናቀቁን አውጀው ነበር።

ነገር ግን ከዚያ በኋላም ባለፉት ሦስት ወራት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች እየተካሄዱ መሆናቸውን ከክልሉ የሚወጡ ሪፖርቶችና የዓለም አቀፍ ተቋማት የገለጹ ነው።

በጦርነቱ ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ በትክክል የታወቀ ነገር ባይኖርም በሺዎች የሚቆተሩ ሊሆኑ እንደሚችል ይገመታል። ከዚህ ባሻገር ግጭቱን በመሸሽ ከ60 ሺህ በላይ ሰዎች ወደ ሱዳን መሰደዳቸው የተነገረ ሲሆን፤ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ደግሞ የሰብአዊ እርዳታ ለማቅረብ መንግሥትና ረድኤት ድርጅቶች ጥረት እያደረጉ ነው።