በደቡብ አፍሪካ ከእርባታ ማዕከል ያመለጡት አዞዎች እየታደኑ ነው

አዞ

የፎቶው ባለመብት, Science Photo Library

በደቡብ አፍሪካዋ ምዕራባዊ ኬፕ ግዛት ቁጥራቸው ለጊዜው ያልታወቀ ታዳጊ አዞዎች ከአንድ ማራቢያ ማዕከል ማምለጣቸውን ተከትሎ እየተፈለጉ እንደሆነ ተገልጿል።

27 የሚሆኑት አዞዎች እስካሁን የተያዙ ሲሆን የአካባቢው ባለስልጣናት እንደሚሉት ከሆነ ግን ያልተያዙት አዞዎች ቁጥር ምን ያክል እንደሆነ እርግጠኛ መሆን አልቻሉም።

አዞዎቹ ከማራቢያ ማዕከሉ ሊያመልጡ የቻሉት ከግቢው ውስጥ በአንደኛው አጥር በኩል ቀዳዳ አግኝተው እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን ምናልባትም በአቅራቢያ ወደሚገኘው 'ብሪድ' ወንዝ ሳኣቀን እንዳልቀረ ተገምቷል።

የአካባቢው ነዋሪዎችም እንዚህን አዞዎች ከተመለከቱ እንዳይቀርቧቸውና ለአካባቢው ባለስልጣናት እንዲያሳውቁ ማሳሰቢያ ተላልፏል።

''እነዚህ እንስሳት በጣም አደገኞች ናቸው። በሰዎች ቁጥጥር ስር የነበሩ የዱር እንስሳት ናቸው'' ብለዋል የክልሉ የአካባቢ ጥበቃ አገልግሎት ቃል አቀባይ ፔትሮ ቫን ሪን።

'' ሁሉም አዞዎች በቁጥጥር ስር እንኪሆኑ ድረስ ሰዎች በምን አይነት ሁኔታ ሊቀርቧቸው አይገባም። ወንዙ አካባቢም ለጊዜው መሄድ የለባቸውም'' ብለዋል።

እስከ 1.5 ሜትር የሚደርስ እርዝማኔ እንዳላቸው የተገመቱት ታዳጊ አዞዎች ከትናንት በስቲያ ረቡዕ ዕለት ነበር ከማራቢያ ማዕከሉ አምልጣው በአቅራቢያ ወደሚገኝ ወንዝ የገቡት።

ፖሊስ በበኩሉ በወንዙ ዳርቻዎች አካባቢ ወጥመዶችን በማዘጋጀት አዞዎቹን ለመያዝ ጥረት እያደረገ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን ሁሉም አዞዎች መያዛቸው እስኪረጋገጥ ድረስ የአካባቢው ነዋሪዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ተጠይቋል።