ጾታዊ ጥቃት፡ ከሦስት ሴቶች አንዷ ለጥቃት ተጋልጣለች - የዓለም ጤና ድርጅት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዓለም ጤና ድርጅት አዲስ ትንታኔ መሠረት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሦስት ሴቶች መካከል አንዷ በሕይወቷ ውስጥ አካላዊ ወይም ወሲባዊ ጥቃት ይደርስባታል።
በዚህ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ መሰረት እድሜያቸው 15 እና ከዚያ በላይ የሆነ 736 ሚሊዮን ያህል ሴቶች ጥቃት ደርሶባቸዋል ማለት ነው።
ሪፖርቱ እንደሚያመለክተው በጎርጎሮሳዊያኑ 2013 የዓለም የጤና ድርጅት ከሠራው ጥናት ወዲህ የተጎዱ ሴቶች ቁጥር በአብዛኛው ባይለወጥም ይሄኛው ግን ጥቃት የሚጀምረው ገና በልጅነት መሆኑን አመልክቷል።
ዕድሜያቸው ከ 15 እስከ 24 ዓመት ከሆኑት አራት ሴቶች መካከል አንዷ ዕድሜዋ እስከ ሃያዎቹ አጋማሽ እስኪደርስ በቅርብ አጋሯ ጥቃት ይደርስባታል።
የዓለም ጤና ድርጅት እንዳለው ጥናት በትልቅነቱ ቀዳሚው ነው፡፡ በዚህም በ 2013 የነበረውንም ማዘመን ተችሏል። ድርጅቱ ከ 2000 እስከ 2018 ባሉት ዓመታት ከ 161 አገራት የተገኘውን መረጃ በመተንተን እነዚህን አዳዲስ ግምቶች ለማውጣት ችሏል፡፡ ጥናቱ በኮቪድ -19 ወረርሽኝ የተገኘ መረጃን አላካተተም፡፡
በቅርብ ባልደረባ የሚደርስ ጥቃት በጣም የተስፋፋ ዓለም አቀፍ የጥቃት ዓይነት ሆኗል።
ወደ 641 ሚሊዮን የሚጠጉ ሴቶችም ይህ እንደደረሰባቸው ተናግረዋል፡፡
ስድስት በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ባለቤታቸው ወይም አጋራቸው ባልሆነ ሰው ጥቃት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል፡፡
"በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት በዓለም አቀፍ ደረጃ በወረርሽኝ መጠን የህብረተሰብ ጤና ችግር ሆኗል። የሚጀምረው ገና በለጋ ዕድሜ ነው፡፡ መገለልን በመፍራት ብዙ ሴቶች ወሲባዊ ጥቃትን ሪፖርት እንዳያደርጉ እንቅፋት ሊሆን ስለሚችል ቁጥሩ የበለጠ ሊጨምር ይችላል" ሲሉ የጥናት ጸሐፊ ዶ/ር ክላውዲያ ጋርሲያ-ሞሬኖ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሴቶች የበለጠ ለጥቃት የሚጋለጡት የት ነው?
እንደ ሪፖርቱ ከሆነ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሀገሮች ውስጥ የሚኖሩ ሴቶች በሕይወታቸው ውስጥ አካላዊ እና (ወይም) ወሲባዊ ጥቃት ከቅርብ ባልደረባቸው ይደርስባቸዋል፡፡
በእነዚህ ሀገሮች ውስጥ ከሚኖሩት ከአራት ሴቶች አንዷ (37 በመቶ) ጥቃት ይደርስባታል። በአውሮፓ (16-23 በመቶ) እና በማዕከላዊ እስያ (18 በመቶ) ለሚኖሩ ደግሞ ይህ ከአምስት ሴቶች ወደ አንድ ዝቅ ይላል፡፡
"በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት በሁሉም ሀገሮች እና ባህሎች ተንሰራፍቷል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሴቶችን እና ቤተሰቦቻቸውን የሚጎዳ ሲሆን ይህም በኮቪድ -19 ወረርሽኝ ምክንያት ተባብሷል። ከኮቪድ -19 በተቃራኒ ግን በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በክትባት ማስቆም አይቻልም" ብለዋል የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፡፡
የወረርሽኙ ተጽዕኖ
የጥናቱ አዘጋጆች "ቁጥሩ ቀድሞውኑ በሴቶች እና በሴት ልጆች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በከፍተኛ መጠን ያሳያል" ብለዋል። የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ቀጣይነት ያለው ተፅእኖን የሚያንፀባርቅ አይደለም፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ስር የተባበሩት መንግሥታት ሴቶች ዋና ዳይሬክተር ፉምዚሌ ምላምቦ-ንግኩካ በተለይ ለቢቢሲ እንደገለጹት በሴቶች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት "በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ እጅግ ተስፋፍቶ የሚገኝ፣ ቀጣይነት ያለው እና አውዳሚ ከሆኑ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች አንዱ ነው።''
"ኮቪድ -19 ከተከሰተ ጀምሮ ብቅ ያሉ መረጃዎች እና ዘገባዎች እንደሚያሳዩት በሴቶች እና በሴት ልጆች ላይ የሚፈጸሙ ሁሉም ዓይነት ጥቃቶች፣ በተለይም የቤት ውስጥ ጥቃቶች ተጠናክረዋል። ይህም ደብቁ ወረርሽን እንለዋለን" ብለዋል።
"ዘገባና የኮቪድ -19 ወረርሽኝ ተጽዕኖ የሚያሳዩት በሴቶችና በሴት ልጆች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለማስወገድ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እርምጃዎች መወሰድ እንዳለባቸው ነው" ብለዋል።
ቀጣይ እርምጃዎች
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገራት ለችግር ተጋላጭ ሴቶች አገልግሎት እንዲያገኙ ለማረጋገጥ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር እንዲሠሩ ጥሪ አቅርቧል። ለአገልግሎቶቹ እና ለፕሮግራሙ ማሻሻል የሚረዱ መረጃዎች እንዲሰበሰቡም የገንዘብ ድጋፍ ተደርጓል፡፡
"ፈቃደኝነት እና ድጋፍን በመጨመር በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለማስወገድ የሚረዳ አዲስ ቁርጠኝነት ማየት እንፈልጋለን" ብለዋል ዶ/ር ክላውዲያ፡፡
"እነዚህ ቁጥሮች ለመንግሥታት የማንቂያ ደወል ናቸው ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ከአምስት አመት በፊት ወሬ ነበር። እስከ 2030 ድረስ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በማስቀረት ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ከፈለግን አሁን የበለጠ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል" ብለዋል፡፡