ትግራይ፡ ከ130 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ገለጸ

ታንክና በመንገድ ላይ የሚጓዙ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, AFP

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ባደረገው ቅኝት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከ131 ሺህ በላይ የተፈናቀሉ ሰዎች እንዳሉ አመለከተ።

ድርጅቱ እንዳለው ተፈናቃዮቹ በትግራይና ተጎራባች በሆኑት የአፋር እንዲሁም የአማራ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 39 በሚሆኑ ተደራሽ ስፍራዎች ላይ እንደሚገኙ ገልጿል።

ይህ የተፈናቃዮች መረጃ የተሰበሰበው አዲስ በሆነው 'ዲስፕሌስመንት ትራኪን ማትሪከስ' በተባለ ዘዴ ሲሆን በዚህም የሕዝብ ቁጥርን በተመለከተ መረጃ በመሰብሰብና የሰዎችን ተጋላጭነት እንዲሁም የተፈናቃዮችን ፍላጎቶችን መሠረት በማድረግ መረጃን በመሰብሰብ የሚተነትን ነው።

አይኦኤም እንዳለው በዚህ የቅኝት ተግባሩ 30,383 ተፈናቀሉ ቤተሰቦችን መለየት ችሏል።

ሴቶችና ህጻናትን ጨምሮ አብዛኞቹ ተፈናቃዮች የአስቸኳይ ጊዜ መጠለያ፣ ምግብና ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦቶችን እንደሚያስፈልጋቸው ተገልጿል።

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት እናዳለው "ይህ መረጃ በተከሰተው ቀውስ ምክንያት የተፈናቀሉትን አጠቃላይ ሰዎች የሚያመለክት አይደለም። ከዚያ ይልቅ መረጃውን ለማሰባሰብ አመቺ በሆኑ ስፍራዎች በአገር ውስጥ የተፈናቀሉትን ሰዎች ብቻ የሚወክል ነው።"

በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ በትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኘው የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ላይ የቀድሞው የክልሉ አስተዳዳሪ በነበረው በህወሓት ኃይሎች የተሰነዘረበትን ጥቃት ተከትሎ ወታደራዊ ግጭት መጀመሩ አይዘነጋም።

በዚህም ሳቢያ ጦርነቱን በመሸሽ ከ60 ሺህ የሚልቁ ሰዎች ድንበር ተሻግረው ወደ ሱዳን ሲሰደዱ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በእዚያው በክልሉ የተለያዩ ስፍራዎች እንደሚገኙ የእርዳታ ድርጅቶች አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በግጭቱ ሳቢያ የተፈናቀሉትን ለመርዳትና መልሶ ለማቋቋም ከፍተኛ ገንዘብ መድቦ የሰብአዊ እርዳታዎችን እያቀረበ መሆኑን ገለጸ ሲሆን፤ ሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶችና ዓለም አቀፍ ተቋማት እርዳታ ለማቅረብ ፈቃድ አግኝተው ተሳትፎ እያደረጉ ነው።