ምርጫ 2013፡ ስድስተኛው ክልላዊና አገራዊ ምርጫ በኦሮሚያ ክልል

የምርጫ ሳጥኖች

የፎቶው ባለመብት, NEBE

የስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ የቀሩት ከሦስት ወራት ያነሱ ጊዜያት ብቻ ናቸው።

በኦሮምያ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሱ እና በዚህ ምርጫ ጠንካራ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብለው ከተጠበቁት መካከል የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) "ተገፍተናል" በሚል በምርጫው እንደማይሳተፉ ተናግረዋል።

እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው ላለመሳተፍ ካቀረቧቸው ምክንያቶች መካከል የአባላቶቻቸው እና የአመራሮቻቸው መታሰር እንደዚሁም ደግሞ የጽህፈት ቤቶቻቸው መዘጋት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

ኦፌኮም ሆነ ኦነግ በኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ጊዜ የቆዩ እና በርካታ ደጋፊዎች እና አባላት አሏቸው የሚባሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው።

ኦፌኮ በ2004 ዓ.ም በኦሮሞ ፌደራሊስት ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዲን) እና በኦሮሞ ሕዝብ ኮንግረስ (ኦሕኮ) ፓርቲዎች ውህደት የተመሰረተ ነው።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በ1968 ዓ.ም ነጻ የወጣች እና ራሷን የቻለች የኦሮሚያ ሪፐብሊክን ለመፍጠር በማቀድ የተመሰረተ የፖለቲካ ድርጅት ው።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የትጥቅ ትግል በማካሄድ ረዥም ዓመታትን ያሳለፈው ይህ ፓርቲ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ወደ ሥልጣን መምጣት ተከትሎ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለመሳተፍ በመወሰን ወደ አገር ውስጥ ከገቡ ፓርቲዎች መካከል አንዱ ነው።

በኦሮሚያ ለመወዳደር ዕጩዎቻቸውን ያስመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ ዕጩዎቻቸውን ያስመዘገቡ 47 የፖለቲካ ፓርቲዎችን ዝርዝር ባለፈው ሳምንት ይፋ አድርጓል።

ከእነዚህ 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በኦሮሚያ ለመወዳደር አራት ዕጩዎቹን ያስመዘገበው የኦሮሞ ነጻነት ንቅናቄ (ኦነን) ይገኝበታል።

በሌላ በኩል ብልጽግና በኦሮሚያ ውስጥ ባሉ የምርጫ ወረዳዎች በሙሉ እንደሚወዳደር ይጠበቃል።

ኢዜማ በበኩሉ በኦሮሚያ ውስጥ በ70 የምርጫ ወረዳዎች ላይ ዕጩዎቹን ያስመዘገበ ሲሆን ባጋጠመው ችግር ምክንያት ፓርቲው በሃያ አምስት የምርጫ ወረዳዎች ዕጩዎችን እንዳላስመዘገበ የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት አቶ ናትናኤል ፈለቀ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በዚሁ ጉዳይ ላይም ከምርጫ ቦርድ ጋር እየተወያዩ መሆኑንም ጨምረው አመልክተዋል።

ከዚህም ውጪ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ እና እናት ፓርቲ በኦሮሚያ ለመወዳደር እጩዎቻቸውን ካስመዘገቡ ፓርቲዎች መካከል ናቸው።

የኦነግ እና የኦፌኮ ምርጫ አለመሳተፍ በምርጫ ቦርድ እና በብልጽግና ይን

የብልጽግና ፓርቲ ሕዝብ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) "ኦነግ እና ኦፌኮ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢኖሩ እንኳ ተቋቁመው መታገል አለባቸው እንጂ እንዲሁ በቀላሉ ወጥተናል ብለው መወሰናቸው ትክክል አይደለም" በማለት ይናገራሉ።

በተጨማሪም ቢቂላ (ዶ/ር) ፓርቲዎቹ መንግሥት ጫና ያደርስብናል፣ አባላቶቻችንን ያስራል፣ ጽህፈት ቤታችንን ዘግቷል ሲሉ የሚያቀርቡትን ውንጀላ "መሰረት የሌለው" ሲሉ አጣጥለውታል።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ባለፈው ሳምንት ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅት የአባላትን መታሰር አስመልክቶ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ የታሰሩት እንዲፈቱ እየሰሩ መቆየታናቸውን እና በተወሰነ መልኩም መፍትሔ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ከጽህፈት ቤቶች መዘጋት ጋርም ተያይዞ ኦነግና ኦፌኮ የተዘጉባቸውን ጽህፈት ቤቶችን ተመለከተ መረጃ እንዲያቀርቡ ተጠይቀው ሁለቱም ፓርቲዎች መልስ ሳይሰጡ መቅረታቸውን የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቀሳ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, National electoral Board of Ethiopia

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ ሁሎቱም ፓርቲዎች ባለመሳተፋቸው ሊያጋጥም ይችላል ብሎ የተዘጋጀበት ችግር እንደሌለ ተናግሯል።

የምርጫ እንቅስቃሴ በነዋሪዎች ይን

የምርጫ ዝግጅት እና የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ በተመለከተ፣ ቢቢሲ የተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች ነዋሪዎችን አነጋግሯል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ነዋሪ የሆኑት አቶ ሃብታሙ ያደቴ አካባቢያቸው እያስተዳደረ ካለው ብልጽግና ፓርቲ ውጪ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ እንደሌለ ይናገራሉ።

ውድድር ደግሞ ከአንድ በላይ በሆኑ አካላት መካከል የሚደረግ መሆኑን የሚናገሩት እኚህ ነዋሪ "በአሁኑ ጊዜ ግን የምርጫ ፉክክር እየተካሄደ መሆኑን የሚያሳይ ነገር እነደሌለ" ይናገራሉ።

በሌላ በኩል የቦረና ዞን ነዋሪ የሆኑት አቶ ገልገሎ ዋቆ እነዚህ ፓርቲዎች ያጋጠማቸውን ችግሮች ከመንግሥት ጋር በመሆን በመፍታት ምርጫ ላይ መሳተፋቸው መልካም እንደሆነ ይናገራሉ።

በክልሉ "ኦነግ እና ኦፌኮ የማይሳተፉበት ምርጫ የሕዝብ ተቀባይነት ይኖረዋል የሚለው ላይ ጥርጣሬ አለኝ" የሚለው የምሥራቅ ወለጋ ነዋሪ የሆነው ወጣት ናትናኤል ጳውሎስ ነው።

"ምርጫው አሳታፊ አይደለም" የሚለው ይህ ወጣት "በዚህም ከጥቅሙ ይልቅ አሉታዊ ተጽዕኖው ትልቅ ሊሆን እንደሚችል" ያለውን ስጋት ይናገራል/

ናትናኤል የፓርቲው አመራሮችና አባላት መታሰነርንም በማንሳት "...የክልላችን ሕዝብ የሚወክል ፓርቲ እና በዚህ ምርጫ ተሳትፎ ያለው የትኛው ፓርቲ ነው?" በማለት ይጠይቃል።

ከዚህም በተጨማሪ በአራቱም የወለጋ ዞኖች፣ በኢሊአባ ቦራ እና ጉጂ ውስጥ የሰላም ስጋት መኖሩን የሚናገረው ናትናኤል፣ "አሁን እኔ ለምሳሌ ሄጄ በሰልፍ ላይ ወረቀት ወስጄ ለመምረጥ ፍላጎት የለኝም፤ ምክንያቱም ለደህንነቴ እሰጋለሁ' በማለት ይናገራል።

ሲጠበቅ የነበረው አለመግባባት

በአምቦ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ሰለሞን ተፈራ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫ መውጣት ዋነኛ ምክንያት ኦነግ እና ኦፌኮ አገር እያስተዳደር ካለው ድርጅት ጋር በተፈጠረ አለመግባባት መሆኑን ይናገራሉ።

"የሁለቱ ፓርቲዎች ከምርጫ መውጣትም በአጋጣሚ የሆነ ሳይሆን ሲጠበቅ የነበረ ነው" የሚሉት እኚህ ምሁር የሁለቱ ፓርቲዎቹ በምርጫ አለመሳተፍ የመራጮችን ቁጥር ይቀንሰዋል ሲሉ ያስረዳሉ።

ፓርቲዎቹ ሰፊ ተቀባይነት ባላቸው አካባቢዎች የሚደረግ ምርጫ የሚገኘው ውጤት የሕዝብ ተቀባይነት እንዳእኖረው ሊያደርግ እንደሚችል ስጋታቸውን ይናገራሉ።

ስለዚህ በዚህ ምክንያት ሊያጋጥም የሚችል ችግር ከኦሮሚያ እና ከአገሪቷ አልፎ የአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት ላይ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል መምህር ሰለሞን ተፈራ አስረድተዋል።

አክለውም "እነዚህ አለመግባባቶች በአብዛኛው ከምርጫ በኋላ የሚቀጥሉና የአገሪቷን ሰላምና አንድነት አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ሊጥሉ ይችላሉ። ስለዚህ ይህ በትኩረት መታየት አለበት" ሲሉ ምክራቸውን ያቀርባሉ።