ጀርመን ምርጫ፡ የሜርክል ፓርቲ በክልላዊ ምርጫ መሰናክል ገጥሞታል

የጀርመኗ መራሂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል

የፎቶው ባለመብት, EPA

በመስከረም ወር ለሚካሄደው አጠቃላይ ምርጫ ፍንጭ ሰጪ ነው በተባለለት ምርጫ የጀርመኗ መራሂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ፓርቲ በሁለት ቁልፍ ክልሎች ከፍተኛ ኪሳራ ገጥሞታል፡፡

ክርስቲያን ዲሞክራት (ሲዲዩ) የሚባለው ፓርቲያቸው በባዴን-ዎርተምበርግ እና በርይንላንድ-ፓላቲኔት ዝቅተኛ ድምጽ ማስመዝገባቸው ቅድመ ውጤቶች አሳይተዋል፡፡

በእነዚህ ምዕራባዊ ግዛቶች ፓርቲው ጠንካራ ድጋፍ ሲያገኝ ቆይቷል፡፡

ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የተሰጠው ምላሽ በሕዝብ ዘንድ ቁጣ መቀስቀሱ ለደካማ ውጤት በዋናነት ምክንያት ተደርጓል፡፡

በሃገሪቱ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ከፍተኛ መሆንና ክትባቱ የማዳረስ ሥራ ደካማ በመሆኑ ባለሥልጣኖቹ ገደቦችን ለማቃለል ተቸግረዋል፡፡ በርካታ የሲዲዩ ፖለቲከኞችም መንግስት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ለመግዛት ከስምምነት ሲደርስ ከፍተኛ ኮሚሽን ተቀብለዋል መባሉን ተከትሎ ከኃፊነታቸው ተነስተዋል፡፡

ውጤቱ በያዝነው ፈረንጆች ዓመት መገባደጃ በሚደረገው ምርጫ የፓርቲው ተስፋ ላይ ጥያቄዎችን ጭሯል፡፡

ለ16 ዓመታት ሃገሪቱን በመራሂተ-መንግስትነት መሩት ሜርክል ስልጣናቸውን በመስከረም ወር የሚለቁ ሲሆን ምርጫው የሲዲዩ መሪ ሆነው ለተመረጡት አርሚን ላሸት የመጀመሪያ ዋና ፈተና ይሆናል ተብሏል፡፡

የ60 ዓመቱ አርሚን ላሽት መስከረም 26 በሚካሄደው ምርጫ ፓርቲያቸውን በመወከል ለዋናው ወንበር ተወዳዳሪ የመሆን ዋስትና የላቸውም፡፡ ለቦታው ተፎካካሪ ይሆናሉ የተባሉት የሲዲዩ እህት ፓርቲ የሆነው የባቫርያው ሲኤስዩ መሪ ማርከስ ሶደር ናቸው፡፡

ፓርቲው ጉዳዩ እስከ ግንቦት መጨረሻ ድረስ መፍትሔ እንዲያገኝ አቅዷል፡፡

የመጀመሪያዎቹ ውጤቶች ምን ያሳያሉ?

ጀርመን በ16 ክልሎች የተዋቀረች ፌዴራላዊ መንግሥት ናት፡፡ በሃገሪቱ ስርዓት መሠረት ለክልል ህግ አውጪዎች እና ቡንደስታግ ለሚባለው ብሔራዊ ፓርላማ ምርጫዎች ይካሄዳሉ፡፡

በባዴን-ዎርተምበርግ ግሪን ፓርቲ 32 በመቶ በሆነ ድምጽ እንደሚያሸንፍ ሲተነበይ ሲዲዩ ደግሞ 24 በመቶ ድምጽ ያገኛል ተብሏል። በዚህም ሲዲዩ ከ2016 ምርጫ ጋር ሲነፃፀር ያነሰ ድምጽ ነው ያስመዘገበው፡፡

በአጎራባቹ ርይንላንድ-ፓላቲኔት ደግሞ ሶሻል ዴሞክራትስ (ኤስፒዲ) በ 35 በመቶ ድምጽ ስልጣኑን እንደሚይዝ ተገምቷል፡፡

ሲዲዩ በህዝብ ሃሳብ መስጫ ወቅት ቢመራም 27 በመቶው ድምጽ ብቻ እንደሚያገኝ ተገምቷል፡፡

ሁለቱም ውጤቶች ግሪንስ፣ ኤስፒዲ እና በሊበራል ፍሪ ዲሞክራትስ መካከል ለሚካሄዱ ክልላዊ ህብረት መንገዱን ይጠርጋል፡፡ ይህም በተመሳሳይ ፓርቲዎች መስከረም ከሚደረገው አጠቃላይ ምርጫ በኋላ ብሔራዊ መንግስትን ለመመስረት ጥምረት ሊፈጥሩ ይችላሉ የሚል ተስፋን ጭሯል፡፡

የግሪን ፓርቲ ሊቀመንበር ሮበርት ሀቤክ ፓርቲው "ይህንን ስኬት ለቡንደስታግ የምርጫ ዘመቻ መነሻ ተድርጎ ይወስዳል" ብለዋል፡፡

ከህዝብ በተሰበሰበ አስተያየት ሲዲዩ የነበረው ብሔራዊ ተወዳጅነት ጀርመን ወረርሽኙን ለመከላከል አበረታች ተግባር ማከናወኗ ከተነገረበት ያለፈው ሰኔ ከነበረበት ከ40 በመቶ ወደ 33 በመቶ ዝቅ ብሏል።

የሲዲዩ የፓርላማ አባል ካይ ዊትከር ውጤቱ ተስፋ አስከፊ ነው ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል፡፡ "ለእኛ መጥፎ ቀን ነው፡፡ ከሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነት እያጣን ነው የሚል ስጋት መኖሩን መካድ አንችልም" ብለዋል።