እንግሊዝ በኮቪድ-19 ስጋት ኢትዮጵያን ጨምሮ የ4 አገራት ተጓዦችን ልታግድ ነው

ወደ ለንደን የምትገባ ተጓዥ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

እንግሊዝ በኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአራት አገራት ወደ ግዛቷ የሚገቡ ተጓዦች ላይ ከመጪው አርብ ጀምሮ እገዳ መጣሏን አስታወቀች።

ከዚህ ቀደም 30 ያህል አገራት ላይ ተመሳሳይ እርምጃ የወሰደችው እንግሊዝ አሁን ደግሞ ከዝርዝሩ ውስጥ ኢትዮጵያ፣ ኳታርን፣ ኦማንንና ሶማሊያን ማካተቷን አስታውቃለች።

አገሪቱ ለዚህ እንደምክንያት ያቀረበችው እየተካሄደ ያለው የወረርሽኙ ክትባት መስጠት ዘመቻ ወሳኝ ደረጃ ላይ ባለበት ወቅት በደቡብ አፍሪካ በብራዚል የተገኙትን የመሰሉ አዲስ አይነት የኮሮናቫይረስ ዝርያዎችን ለመከላከል ነው ተብሏል።

ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ በእንግሊዝ "ቀዩ ዝርዝር" ውስጥ ከተካተቱት ከኢትዮጵያና ከሦስቱ አገራት ከአርብ መጋቢት 10/2013 ዓ.ም ቀደም ብሎ ካሉት አስር ቀናት ጀምሮ ጉዞ ያደረጉ ወይም በዚያ ያለፉ ሰዎች ወደ እንግሊዝ እንዲገቡ አይፈቀድላቸውም።

ተጓዦቹ የብሪታኒያ ወይም የአየርላንድ ዜጎች ወይም የረጅም ጊዜ ቪዛን ጨምሮ የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው ከሆኑ ግን እንዲገቡ የሚፈቀድላቸው ሲሆን፤ ነገር ግን በመንግሥት እውቅና ባላቸው ማቆያዎች ውስጥ ለ10 ቀናት ተለይተው እንዲቆዩና በሁለተኛና በ8ኛ ቀናቸው የኮሮናቫይረስ ምርመራ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ከተጓዦች በተጨማሪም ከተጠቀሱት አገራት በሚመጡ የንግድና የግል አውሮፕላኖች ላይም እገዳ ይጣላል። ይህ ግን የጭነት አውሮፕላኖችን እንደማይመለከት የወጣው መግለቻ አመልክቷል።

መግለጫው ጨምሮም እዚህ ውሳኔ ላይ የሚደረሰው በሽታውን በተመለከተ የተለያዩ መረጃዎችን መሠረት በማድረግ መሆኑን ጠቅሶ ከዚህ ውስጥም በየአገራቱ በሕብረተሰቡ ውስጥ ያለው የቫይረሱ ዝርያ እና የስጋት ደረጃ በዋናነት የሚጣዩ ናቸው።

የአገራቱን ዝርዝር በተመለከተም በየጊዜው እየተፈተሸ የሚጨመሩና የሚቀነሱ አገራት የሚኖሩ ሲሆን አሁን ከተጨመሩት በተቃራኒው ከዚህ በፊት ዝርዝሩ ውስጥ የነበሩት አውሮፓዊቷ ፖርቱጋልና አፍሪካዊተወ ሞሪሺየስ እንደሚወጡ ተገልጿል።

እንግሊዝ በኮሮረናቫይረስ ስጋት ምክንያት የጉዞ ዕገዳ የታለችባቸው አገራት ከ30 በላይ ሲሆኑ ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ የአፍሪካ፣ የመካከለኛው ምሥራቅና የደቡብ አሜሪካ አገራት ናቸው።