ኮሮናቫይረስ፡ በኢትዮጵያ ኮቪድ-19 በጽኑ የሚታመሙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር "በአስደንጋጭ ሁኔታ" ጨመረ

በአዲስ አበባ ጎዳና ላይ የአፍ መሸፈኛ ያደረጉ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

በኢትዮጵያ ከጥቂት ሳምንታት ወዲህ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የሚያዙ፣ ወደ ጽኑ ህሙማን ክፍል የሚገቡና በበሽታው ህይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥር "በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ" መሆኑን የሕብረተሰብ ጤና ኢነስቲቲዩት አስታወቀ።

ቀደም ሲል በጽኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ህክምና እያገኙ የነበሩ ሰዎች ቁጥር በአራት መቶዎች ውስጥ የቆየ ሲሆን ይህ አሃዝ ባለፉት ቀናት ውስጥ አምስት መቶን ተሻግሮ ወደ ስድስት መቶ መጠጋቱን በየዕለቱ የሚወጣው የበሽታው የዕለት ሁኔታ ሪፖርት ያመለክታል።

ሰኞ ዕለት በጽኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ይገኙ የነበሩት ሰዎች ቁጥር 531 የነበረ ሲሆን ትናንት ማክሰኞ ቁጥሩ በ60 ጨምሮ 591 በመድረሱ በህክምና ተቋማቱ ላይ ጫና መፈጠሩ ተነግሯል።

በዚህም ሳቢያ የጽኑ ህሙማን ክትትል ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች በሚውሉት የሰው ሰራሽ መተንፈሻ መርጃ (ቬንትሌተር) እና ኦክስጂን አቅርቦት ላይ እጥረት አጋጥሟል የሕብረተሰብ ጤና ተቋም ትናንት እናደለው የሰውሰራሽ መተንፈሻ ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው ሰዎች መካከል ስምነቱ በመጠባበቅ ላይ ነበሩ።

ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በነበሩ ቀናት የተደረጉ የኮቪድ-19 ምርመራ ውጤቶች እንደሚያመለክቱት በየዕለቱ በአማካይ ከ1300 በላይ ሰዎች ላይ በወረርሽኙ መያዛቸውን ያመለክታል።

አጠቃላይ የምርመራው ውጤት በመቶኛ ሲሰላ ከተመረመሩት 100 ሰዎች ውስጥ በአማካኝ 19 ሰዎች ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል። በዚህም በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከ32 በመቶ በላይ ጨምሯል።

በበሽታው ሰበብ ለህልፈት የሚዳረጉ ሰዎችን ቁጥር ስንመለከትም ከዕለት ዕለት ዕየጨመረ በአማካይ ከ15 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ህይወት እያለፈ ነው። ይህም ቀደም ካሉት ሳምንታት ጋር ሲነጻጸር በ89 በመቶ መጨመሩን ባለሙያዎቹ ተናግረዋል።

ወረርሽኙ ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሆን ተሰግቷል

የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ማክሰኞ ዕለት፣ በሰጡት መግለጫ "ወረርሽኙ ከቁጥጥር ውጭ ከመሆኑ በፊት ሁሉም ኃላፊነቱን መወጣት አለበት" ሲሉ አሳስበዋል።

የበሽታው ስርጭት ባለፉት ወራት በተለይም ባለፉት ሳምንታት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ጠቅሰው፤ ቀደም ሲል በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ከ10 በመቶ በታች የነበረው ከፍ ብሎ አዲስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በአማካይ 17 በመቶ ማሻቀቡን ተናግረዋል።

በዚህም እስካሳለፍነው ቅዳሜ ድረስ በነበሩት 10 ቀናት ውስጥ "ከ12 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሲረጋገጥ፣ የ149 ሰዎች ህይወትም በወረርሽኙ ሳቢያ አልፏል" ብለዋል።

የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን እንዲሁም የጽኑ ህሙማን ህክምና የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥርም በባለፉት ቀናት ለመጀመሪያ ጊዜ ከ450 መብለጡን ተናግረዋል።

በዚህም ሳቢያ የጽኑ ህሙማን ክፍሎች መሙላታቸውን፣ ያሉ የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያዎች (ቬንትሌተር) በህሙማን ሙሉ ለሙሉ መያዛቸውን እንዲሁም የኦክስጅን እጥረት ማጋጠሙን ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, EPHI

በኢትዮጵያ እስከ መጋቢት 06/2013 ዓ.ም ድረስ በተደረገ የኮሮናቫይረስ ምርመራ 176,618 ሰዎች በወረርሽኙ መያዛቸው የተረጋጠ ሲሆን 2,555 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

በተጨማሪም 531 ግለሰቦች በኮቪድ-19 ምክንያት በጽኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፤ ይህ ቁጥርም በሽታው ኢትዮጵያ ውስጥ ከተገኘ በኋላ ከፍተኛው ነው።

የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ተቋም እንዳለው ከእነዚህም ውስጥ 66ቱ ሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መሳሪያ (ቬንትሌተር) ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው።

የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ተቋም ዛሬ ባወጣው መረጃ መሰረት ያሉት የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያዎች በመያዛቸው በጽኑ የታመሙ 8 ያህል ግለሰቦች የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።

"ክትባት መሰጠቱ ይቀጥላል"

የጤና ሚኒስትሯ በአገሪቷ እየተሰጠ ያለውን የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባት አስመልክቶ የአስትራዜኒካ ክትባትን መስጠት እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

አንዳንድ አገራት ከአስትራዜኒካ የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባት ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል ባሉት ችግር ምክንያት ክትባቱን መስጠት ቢያቆሙም በኢትዮጵያ ክትባቱ መሰጠት እንደሚቀጥል የጤና ሚኒስቴር ገልጿል።

ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያን፣ ዴንማርክ፣ ኖርዌይ እና ስፔንን ጨምሮ ስምንት የአውሮፓ አገራት ክትባቱ ከደም መርጋት ጋር የተያያዘ ችግር ሊኖረው ይችላል በሚል የአስትራዜኔካ ክትባት ለጊዜው እንዲቆም አድርገዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ዛሬ ማክሰኞ፣ በሰጡት መግለጫ ላይ እንዳሉት በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ውስጥ እየተሰጠ ያለው የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ጋር በተያያዘ እስካሁን ያጋጠመ ችግር እንደሌለ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ መሰጠት የተጀመረው ወረርሽኙ በአገሪቱ ውስጥ መገኘቱ ይፋ በተደረገ በዓመቱ ባለፈው ቅዳሜ መጋቢት 04/2013 ዓ.ም ነበር።

በአገሪቱ እየተሰጠ የሚገኘው የአስትራዜኔካ ምርት የሆነው 2.2 ሚሊየን ብልቃጥ ክትባት ኮቫክስ ከተሰኘው ዓለም አቀፍ የክትባት አቅርቦት ጥምረት የቀረበ ነው።

ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ እስካሁን ባለው መረጃ ተከሰተ የተባለው ችግር "ከአስትራዜኒካ ክትባት ጋር ግንኙነት እንደሌለውና ክትባቱ መቀጠል እንዳለበት የዓለም የጤና ድርጅት፣ የአውሮፓና የእንግሊዝ የመድኃኒት ጥናትና ቁጥጥር ባለስልጣን በይፋ አስታውቀዋል" ብለዋል።

በአውሮፓ ሕብረት አባላት አገራትና በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ እስካሁን 17 ሚሊዮን ሰዎች የአስትራዜንካ ክትባትን መከተባቸውና ከእነዚህ ውስጥም 40ዎቹ የደም መርጋት ችግር እንዳጋጠማቸው የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

የዓለም ጤና ድርጅት በርካታ የአውሮፓ አገራት የአስትራዜኒካ ክትባት እንዳይሰጥ ማገዳቸውን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ክትባቱ የደም መርጋት ስለማስከተሉ ምንም አይነት ማስረጃ የለም ብሏል።

ዶ/ር ሊያ ታደሰም ክትባቱ በበርካታ አገራት ውስጥ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች መዳረሱንና በኢትዮጵያም መሰጠቱ እንደሚቀጥል ተናግረው ጉዳዩ "በሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በኩል ጥብቅ ክትትል ይደረግበታል" ብለዋል።

በዚህም መሠረት ክትባቱን በተመለከተ አዲስ ነገር የሚኖር ከሆነ ሕብረተሰቡ እንዲያውቀው እንደሚደረግ ገልጸው "ከክትባቱ ጋር ተያይዞ እስካሁን የገጠመ ችግር ባለመኖሩ ክትባቱን መስጠታችንን እንቀጥላለን" ብለዋል።

በዚህም መሠረት ክትባቱ ለጤና ባለሙያዎች፣ ተጓዳኝ በሽታ ላለባቸው ሰዎችና ለአረጋዊያን በተከታታይ የሚሰጥ መሆኑን በመግለጽ እስከሚቀጥለው ዓመት ታኅሣስ ድረስ ከአገሪቱ ሕዝብ 20 በመቶውን እንዲከተብ ይደረጋል ብለዋል።