'በትግራይ የሕክምና ተቋማት ሆን ተብሎ ጥቃትና ዘረፋ ተፈጽሞባቸዋል'-ኤምኤስኤፍ

ዘረፈ ከተፈፀመባቸው ሆስፒታሎች መካከል አንዱ

የፎቶው ባለመብት, MSF

ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) የተሰኘው በሕክምና ላይ የተሰማራው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በትግራይ ክልል በሚገኙ የሕክምና ተቋማት ላይ ሆን ተብሎ ዘረፋ እና ጥቃት ተፈጽሟል ሲል ገለፀ።

ድርጅቱ ዛሬ ሰኞ፣ ባወጣው መግለጫ እንዳለው በተፈጸመው ዘረፋ የተነሳ በጣም ውሱን ሠራተኞች ብቻ የሥራ ገበታቸው ላይ እንደሚገኙ፣ እንዲሁም አንዳንድ ቦታም ምንም ዓይነት ባለሙያ አለመኖሩን አስታውቋል።

ኤምኤስኤፍ ካለፈው ታኅሣስ ጀምሮ ከመቶ በላይ የሕክምና ተቋማትን መጎብኘቱን ገልፆ ሦስት አራተኛዎቹ ዘረፋ እንደተፈፀመባቸው ገልጿል።

ድርጅቱ በዚሁ መግለጫው አንዳንዶቹ ዘረፋዎች የተፈፀሙት በወታደሮች ጭምር ነው ያለ ሲሆን 13 በመቶ የሚሆኑ የጤና ተቋማት ብቻ በአግባቡ እየሰሩ ነው ብሏል።

የሠላም ሚኒስቴር ትናንት ባወጣው መግለጫ በትግራይ ክልል ከሚገኙ ሆስፒታሎች ውስጥ 75 በመቶዎቹ ሙሉ በሙሉ ሥራ መጀመራቸውን አስታወቋል።

ሚኒስቴሩ በዚሁ መግለጫው ላይ 10 በመቶ የሚሆኑት በግማሽ አቅም አገልግሎት እየሰጡ ነው ብሏል።

አገልግሎት በመስጠት ላይ በሚገኙ የጤና ተቋማት ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑ ሠራተኞች በሥራ ገበታቸው ላይ ይገኛሉም ሲል አክሏል።

በትግራይ ክልል ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የህወሓት ኃይሎች በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን ተከትሎ ግጭት መቀስቃሱ ይታወሳል።

ከሦስት ሳምንት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የፌደራል መንግሥቱ ኃይሎች መቀለን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ "ሕግ የማስከበር ዘመቻው" መጠናቀቁን ቢገልፁም አሁንም በአንዳንድ ስፍራዎች ግጭቶች እንዳሉ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ይናገራሉ።

በዚህ ግጭት የተነሳም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ ጠባቂ ሲሆኑ፣ ከ60ሺህ በላይ የሚሆኑ ደግሞ ወደ ሱዳን ተሰድደዋል።

ኤምኤስኤፍ በመግለጫው በርካቶቹ የጤና ተቋማት በኤርትራና በኢትዮጵያ ወታደሮች ተይዘው እንደሚገኙም ገልጿል።

አክሎም ከአምስት የጤና ተቋማት አንዱ በወታደሮች ተይዞ ይገኛል ያለ ሲሆን ከኢትጵያ መንግሥት በኩል በዚህ ጉዳይ ላይ ተባለ ነገር የለም።

ኤምኤስኤፍ በመግለጫው ላይ በጣም አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የጤና ተቋማት አምቡላንሶች እንዳላቸው አመልክቷል።

የሠላም ሚኒስቴር በበኩሉ 54 አምቡላንሶች ሙሉ በሙሉ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ጠቅሶ በቀጣይ ጊዜያትም ተጨማሪ 52 አምቡላንሶች ተጠግነው አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ ብሏል።

በኢትዮጵያ መንግሥት ሠራዊትና በህወሓት አማፂያን መካከል በተደረገው ወታደራዊ ግጭት የተነሳ በርካታ መሰረተ ልማቶች መውደማቸው የተነገረ ሲሆን መንግሥትም ጥገና በማድረግ ወደ ሥራ እየመለሳቸው መሆኑን እየገለፀ ይገኛል።