ክትባት፡ የዓለም ጤና ድርጅት ክትባቱ ችግር የለውም ቢልም ትልልቆቹ የአውሮፓ አገራት የአስትራዜኔካ ክትባትን መስጠት አቆሙ

አንድ አዛውንት ክትባት ሲከተቡ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ከደም መርጋት ጋር በተያያዘ ባጋጠሙ ተከታታይ የጤና ችግሮች ምክንያት ጀርመን፣ ፈረንሳይና ጣሊያን በአገራቸው የኦክስፎርድ-አስትራዜኒካ ክትባት እንዳይሰጥ አደረጉ።

እነዚህ አገራት ክትባቱ እንዳይሰጥ ያደረጉት ሌሎች የአውሮፓ አገራት ምርመራ ተደርጎ ውጤቱ እስኪታወቅ ድረስ ክትባቱን መስጠት ካቆሙ ከቀናት በኋላ ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት ግን በኦክስፎርዱ አስትራዜኔካ ክትባት ሳቢያ የደም መረጋት መከሰቱን የሚያሳይ ምንም ማስረጃ አለመኖሩን አስታውቋል።

ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ ከክትባቱ ጋር በተያያዘ የቀረቡ ሪፖርቶችን እየተመለከተ መሆኑን ገልጾ፤ የክትባት ዘመቻዎች ግን መቀጠላቸው አስፈላጊ ነው ብሏል።

የሚያጋጥሙ አሉታዊ ክስተቶችን መመርመርም ጥሩ ልምድ መሆኑን ድርጅቱ አክሏል።

በአውሮፓ ክትባቱ መሰጠት ከጀመረ በኋላ የደም መርጋት ያጋጠማቸው በርካታ ሰዎች ተመዝግበዋል።

ሆኖም ባለሙያዎች ከክትባቱ በኋላ የተመዘገቡ በርካታ የደም መርጋት ችግሮች ወትሮ ከጠቅላላው ሕዝብ ውስጥ ከሚመዘገበው የበለጠ አይደለም ብለዋል።

አስትራዜኔካ እንዳለው በአውሮፓ ሕብረት አባል አገራትና በዩናይትድ ኪንግደም እስካሁን 17 ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎች ክትባቱን የወሰዱ ሲሆን፤ እስካለፈው ሳምንት ድረስ የተመዘገቡ የደም መርጋት ችግሮች ግን ከ40 ያነሱ ናቸው።

የዓለም ጤና ድርጅትና ሌሎች ባለሙያዎችስ ምን አሉ?

የዓለም ጤና ድርጅት ቃል አቀባይ ክርስቲያን ሊንድሜር ድርጅቱ የቀረቡትን ሪፖርቶች እየመረመረ መሆኑን ተናግረዋል።

"ድርጅቱ ስለክስተቶቹ የተሟላ ግንዛቤ እንዳገኘ፤ ግኝቱን እንዲሁም አሁን ባለው ምክረ ሃሳብ ላይ የሚለውጡ ነገሮች ካሉ ወዲያውኑ ለሕዝቡ ያሳውቃል" ብለዋል።

ቃል አቀባይዋ እስከ ዛሬ ድረስ ግን ክስተቶቹ በክትባቱ ምክንያት የመጡ መሆናቸውን የሚያመለክት ምንም ማረጋገጫ አለመገኘቱን አረጋግጠዋል።

በመሆኑም የክትባት ዘመቻዎች እንዲቀጥሉ በማድረግ የበርካቶችን ሕይወት ማትረፍ ወሳኝ ነው ብለዋል-ቃል አቀባይዋ።

አሁን ላይ አጋጠሙ የተባሉ የደም መርጋት ችግሮችን እየተመለከተ የሚገኘው የአውሮፓ የሕክምና ማኅበርም ክትባቱ መሰጠቱ ሊቀጥል ይችላል ብሏል።

የዩናይትድ ኪንግደም የሕክምና ተቆጣጣሪ በበኩሉ "መረጃዎች ክትባቱ የደም መርጋት ችግር እንደሚያስከትል አያሳዩም" ሲል የአገሪቷ ሕዝቦች ክትባቱን እንዲወስዱ ሲጠየቁ መከተብ እንዳለባቸው አሳስቧል።

የኦክስፎርዱን አስትራዜኔካ ክትባት ያበለፀገው የኦክስፎርድ ክትባት ቡድን ዳሬክተር ፕሮፌሰር አንድሪው ፖላርድም እስካሁን በአውሮፓ ካሉ አገራት ብዙ ክትባት በተሰጠበት ዩናይትድ ኪንግደም የደም መርጋት ችግር እንዳልጨመረ የሚያረጋግጥ ማስረጃ መኖሩን ለቢቢሲ ተናግረዋል።