አስትራዜኒካ የደም መርጋት ያስከትላል? የዓለም ጤና ድርጅት ክትባቱን ሊገመግም ነው

አስትራዜኒካ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የዓለም ጤና ድርጅት ብዙ እየተወራበት ያለውን የኦክስፎርድ አስትራዜኒካን ውጤታማነትን በተለይም ከደም መርጋት ጋር ያለውን ተያያዥነት በክትባት ሊቃውንት ሊያስገመግም ነው፡፡

ክትባቱ ውጤታማ ነው ከተባለ በኋላ ብዙ አገራት ለሕዝባቸው ማደል ጀምረው ነበር፡፡ ሆኖም ደም እንዲረጋ ያደርጋል የሚል መረጃ መውጣቱን ተከትሎ ብዙ የአውሮፓ አገራት ለጊዜው የክትባት እደላው እንዲቆም ወስነዋል፡፡

አንዳንድ ክትባቱን የወሰዱ ሰዎች ደማቸው የመርጋት ምልክት በማሳየቱ ነው ስጋት የተፈጠረው፡፡

እነዚህ የክትባት ሊቃውንት ለግምገማ የሚቀመጡት ዛሬ ማክሰኞ ነው፡፡

በተመሳሳይ የአውሮጳ መድኃኒት ኤጀንሲ ኃላፊዎችም ዛሬ በጉዳዩ ላይ ለመምከር ይሰበሰባሉ ተብሏል፡፡

የክትባት ሊቃውንት ቡድን ሁኔታዎችን ከገመገመ በኋላ ኦክስፎርድ አስትራዜኒካ ክትባት ለሰዎች ቢሰጥ የከፋ ጉዳት እንደሌለው የሚያትት መግለጫ ሐሙስ ያወጣል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡

በአውሮፓ ኅብረትና በታላቋ ብሪታኒያ በድምሩ 17 ሚሊዮን ዜጎች አስትራዜኒካ ክትባትን የወሰዱ ሲሆን ከዚህ ሁሉ ተከታቢ መሀል የደም መርጋት አጋጠማቸው የተባሉትን ሰዎች ቁጥር ከ40 አይበልጥም፡፡

አሁን ይህ ክትባት በእርግጥ የደም መርጋትን ያመጣል ወይ የሚለው በተጨባጭ የታወቀ ባይሆንም ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያን እና ስፔንን ጨምሮ በርካታ አገራት ክትባቱን ለጊዜው ይቆየን ብለዋል፡፡

ቤልጂየም፣ ፖላንድ፣ ቼክ ሪፐብሊክና ዩክሬን ግን ክትባቱን ለሕዝባቸው ማደላቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ ክትባቱ በእርግጥ የደም መርጋት ያስከትላል በሚለው ላይ አዲስ ምርመራ መጀመሩን ይፋ አድርጓል፡፡

ባለፈው ማክሰኞ የዓለም ጤና ድርጅት ቃል አቀባይ ክትባቱ ደም እንደሚያረጋ የተገኘ አንዳችም ተጨባጭ መረጃ የለም ብለው ነበር፡፡

በርከት ያሉ የጤና ባለሙያዎች እንደሚሉት ክትባቱን መውሰድ የጎንዮሽ ጉዳቱን በመፍራት ካለመውሰድ የተሻለ ነው፡፡ ክትባቱ ደም እንዲረጋ ያደርጋል የሚሉት አጋጣሚዎችም ከጠቅላላው ተከታቢ ቁጥር ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ይላሉ፡፡