ስደተኞች፡ የመን ውስጥ ኢትዮጵያውያን በሚበዙበት የስደተኞች መጠለያ ላይ በእሳት ከሞቱት መካከል 43ቱ መቀበራቸው ተነገረ

አስከሬኖች

የፎቶው ባለመብት, FB

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በየመን የካቲት 29/2013 ዓ.ም በእሳት አደጋ ቃጠሎ ምክንያት ሕይወታቸው ካለፉ ስደተኞች መካከል የ43ቱ ቀብር መፈፀሙን አስታወቀ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተናገሩት በእሳት አደጋው ከሞቱ መካከል 43 የተቀበሩ ቢሆንም ከእነዚህ ውስጥ ምን ያህሉ ኢትዮጵያውያን ስለመሆናቸው የታወቀ ነገር የለም።

አምባሳደር ዲና አክለውም ከየመን 150 ኢትዮጵያውያን በዛሬው ዕለት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱ ተናግረዋል።

ሂዩማን ራይትስ ዎች በየመን በስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ላይ ስለደረሰው የእሳት አደጋ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው በጣቢያው ላይ የእሳት አደጋ ያደረሰው በሁቲ አማፂያን የተተኮሰ መሳሪያ ነው ብሏል።

"የሁቲዎች ግዴለሽነት የተሞላበት የጦር መሳሪያ አጠቃቀም በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ለሞት መዳረጉ፣ በጦርነት በምትታመሰው የመን የሚገኙ ስደተኞች ሕይወት ምን ያህል በአደጋ የተከበበ መሆኑን አስታዋሽ ነው" ሲል በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።

የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ጉዳዩን በተመለከተ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር በሚገኘው የስደተኞች ማቆያ የሚገኙ አምስት ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን እንዲሁም በየመን የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣናትን ማናገራቸውን ገልጿል።

550 ስደተኞች የማቆያ ጣቢያው ያለበትን የጽዳት ችግርና መጨናነቁን በመቃወም የረሃብ አድማ ላይ መሆናቸውን ሂማን ራይትስ ዋች አመልክቷል።

እነዚህ ስደተኞች እንደሚሉት ከሆነ በማቆያው ውስጥ ለረዥም ጊዜ የኖሩ ሲሆን ከማቆያው ለመውጣት ለጥበቃ አባላቱ እስከ 70 ሺህ የየመን ሪያል ወይንም 280 ዶላር መክፈል ይጠበቅባቸዋል።

ስደተኞቹ ለሰብዓዊ መብቱ ተቆርቋሪ ድርጅቱ እንደተናገሩት ጥበቃ አባላቱ የተለያዩ አፀያፊ ዘር ጠቀስ ስድቦችንም በየጊዜው እንደሚሰነዝሩባቸው ተናግረዋል።

በወቅቱ የእሳት አደጋውን በተመለከ የሁቲ ታጣቂዎች ባወጡት መግለጫ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅትና የተባበሩት መንግሥታት ለስደተኞቹ መኖሪያ ባለማቅረብ እና ከየመን እንዲወጡ ለማድረግ ባለመተባበራቸው ለደረሰው አደጋ ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ ናቸው ሲሉ ወቅሰዋል።

ከአደጋው የተረፉት በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን የጠቀሰው የሰብዓዊ መብት ድርጅቱ የደረሰባቸውን ቃጠሎ በሰንዓ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ እየታከሙ ነው ተብሏል።

እነዚህ ስደተኞች ሕክምና በሚያገኙበት ሆስፒታል አካባቢ ከፍተኛ የፀጥታ ኃይል ተሰማርቶ እንደሚገኝ የገለፀው የሰብዓዊ መብት ድርጅቱ ይህም ሰብአዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች እና ቤተሰቦች ለመጠየቅ እንዲሁም ክትተል ለማድረግ አስቸጋሪ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግሯል።

የሁቲ አማፂያን ለሰብዓዊ እርዳታ ቡድኖች ፈቃድ እንዲሰጡም ጥሪ አቅርቧል።

የተባበሩት መንግሥታት ቡድን ክስተቱን በአገሪቱ ከተካሄዱ የሰብዓዊ መብቶት ጥሰቶች ተካትቶ ምርመራ እንዲያደርጉ ጠይቋል።

የሁቲ አማፂያን ሰንዓን ጨምሮ በርካታ የየመን ክፍሎችን ይቆጣጠራል።

የዓለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) በየመን 6000 ያህል ስደተኞች በማቆያ ውስጥ እንደሚገኙ ገልፆ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ በሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ጭምር ታግተው ይገኛሉ ብሏል።

አይኦኤም እንደሚገምተው በኮሮናቫይረስ ምክንያት የተጣለውን የመንቀሳቀስ ገደብ ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች የመን ውስጥ ወደየትም መሄድ ሳይችሉ እየተጉላሉ ነው።

ምንም እንኳ የመን ማብቂያ ባላገኘ ጦርነት ውስጥ ብትሆንም በተለይ ደግሞ መነሻቸው ከአፍሪካ ቀንድ የሆኑ በ100 ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ድንበሯን እያቋረጡ ወደ ጎረቤት አገር ሳዑዲ አረቢያ ለመግባት በመፍለስ ላይ ናቸው።

የመን ውስጥ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ሳዑዲ አረቢያ ድንበሯን በመዝጋቷ አብዛኞቹ ስደተኞች በጦርነት፣ በረሃብና በበሽታ እየተሰቃዩ በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ይገኛሉ።

የመን ውስጥ በሳዑዲ መራሹ ኃይልና በኢራን በሚደገፉት የሁቲ ታጣቂዎች መካከል ስድስት ዓመት የሆነውና አሁንም እየተካሄደ ያለው ጦርነት ከስደተኞቹ በተጨማሪ የአገሪቱን ዜጎች ህይወት አመሰቃቅሎታል።

የመን ውስጥ ከሚኖሩ ሰዎች መካከል 80 በመቶ ያህሉ እርዳታ ላይ ጥገኛ ሲሆኑ፤ በርካቶች አገራቸውን እየለቀቁ ጦርነቱን ሽሽት ይሰደዳሉ።