የ99 ዓመቱ ልዑል ፊሊፕ ከአንድ ወር ቆይታ በኋላ ከሆስፒታል ወጡ

የኤደንብራው ልዑል ፊሊፕ

የፎቶው ባለመብት, PA Media

የኤደንብራው መስፍን ለንደን ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል የልብ ሕክምና ክትትል ሲያደርጉ ከቆዩ በኋላ አገግመው መውጣታቸው ተነገረ።

የ99 ዓመቱ ልዑል ፊሊፕ ወደ ሜሪሌቦን ኪንግ ኤድዋርድ ሰባተኛ ሆስፒታል የገቡት ከአንድ ወር በፊት ነበር።

ከዚያ በኋላ ለንደን በሚገኘው ቅዱስ ባርቶሎሜውስ ሆስፒታል ከዚህ ቀደም ለነበረባቸው የልብ ህመም ሕክምና አድርገዋል።

28ቱ ምሽቶች ለልዑሉ በሆስፒታል ያሳለፉት ረዥሙ ጊዜ ነበር።

ልዑሉ መጀመሪያ ሆስፒታል የገቡበት ምክንያት አልተገለፀም፤ ይሁን እንጅ በጊዜው ባኪንግሃም ቤተመንግሥት ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዘ እንዳልሆነ አስታውቆ ነበር።

ልዑል ፊሊፕ እና የ94 ዓመቷ ባለቤታቸው ንግስት ኤልዛቤት በእንግሊዝ ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የተጣለውን ገደብ ያሳለፉት ከጥቂት ሰራተኞቻቸው ጋር በዊንድሶር ቤተ መንግሥት ነው።

73 ዓመታትን በትዳር ያሳለፉት ጥንዶቹ፤ ባሳለፍነው ጥር ወር የመጀመሪያውን የኮሮናቫይረስ ክትባት ወስደዋል።

ልዑል ፊሊፕ በኪንግ ኤድዋርድ ሰባተኛ በቆዩበት ወቅት በዌልሱ ልዑል ልጃቸው ተጎብኝተዋል።

ልዑል ፊሊፕ መጋቢት 3 የተሳካ ሕክምና በማካሄድ ቀደም ሲል ለነበረባቸው የልብ ህመም ሕክምና ለማድረግ ወደ ባርትስ ተወስደው ነበር።

በኋላ ላይ ልዑሉ ወደ ኪንግ ኤድዋርድ ሰባተኛ ሆስፒታል ተልከዋል።

ሆስፒታሉ ለንደን ውስጥ የሚገኝ የግል ክሊኒክ ሲሆን፤ በተለያየ ጊዜ ለንግሥቷ እንዲሁም ለልዑሉ እና ሌሎች ንጉሳዊያን ቤተሰቦች ሕክምና ሰጥቷል።

ልዑል ፊሊፕ፤ ከንጉሳዊያን ኃላፊነት እአአ በ2017 በጡረታ የተገለሉ ሲሆን፤ በእነዚህ ዓመታት ለተለያየ የጤና ችግር ሕክምና ወስደዋል።

እአአ በ2012 የሽንት ፊኛ ኢንፌክሽን ሕክምና ያደረጉ ሲሆን፤ ሰኔ 2013 ደግሞ በሆዳቸው ላይ ቀዶ ሕክምና አድርገዋል።