ክሪፕቶአርት: ዲጂታል ሥዕል በመሸጥ ሚሊየነር እየሆኑ ያሉ የሥነ ጥበብ ባለሙያዎች

አላና ኤዲንግተን

የፎቶው ባለመብት, Alana Edgington

የምስሉ መግለጫ,

አላና ኤዲንግተን

ክሪፕቶአርት ይባላል። አሁን አሁን ይህ የዲጂታል ሥዕል ግብይት ዘዴ እጅጉን የገነነ ነው። ለዘመናት በድህነት የጎበጡ የሥነ ጥበብ ሰዎች ክሪፕቶአርት ሠርግና ምላሽ ሆኖላቸዋል።

ይህን አዲስ ጥበብ በዚህ አዲስ ዘመን ላይ በመምጣቱ ሕይወታቸውን እየለወጡ የሚገኙ የምዕራቡ ዓለም አርቲስቶች ቁጥር ቀላል አይደለም።

አርቲስት ቢፕል ከሰሞኑ አንድ ዲጂታል ሥዕል 69 ሚሊዮን ዶላር በመሸጥ አዲስ ክብረ ወሰን አስመዝግቧል።

ሥዕሉ የተሸጠው በብሎክቼይን የዲጂታል ግብይት ዘዴ ነው።

በዚህ መንገድ ሥዕሉን የሸጠው አርቲስት እንደሚለው ይህ የክሪፕቶአርት ሽያጭ በዓለም ላይ ትልቅ ተሰሚነት ካላቸው 3 አርቲስቶች መሀል አንዱ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

አላና ኤዲንግተን ሌላዋ አርቲስት ናት። በእዳ ቁልል ኑሮዋን ስትገፋ ነው የኖረችው። ይህ የዲጂታል ሥዕል ገበያ ግን ሚሊየነር አድርጓታል።

በምህጻሩ ኤንኤፍቲ (NFT) በሚሉ ቃላት የሚወከለው ይህ አዲስ ዘዴ Non-Refundable Token የሚል ሐረግን የሚወክል ነው።

ነገሩ አርቲስቶች ሥራዎቻቸውን በዲጂታል መንገድ የሚሸጡበት አዲስ አሰራር ነው።

በሌላ አነጋገር ኤንኤፍቲ የዲጂታል ጉሊት ሲሆን አርቲስቶችና አጫራቾች እንዲሁም ሸማቾች የሚገናኙበት ዲጂታል ሥፍራ አድርገን ልናየው እንችላለን። ገዢው የሚገዛው የአርቲስቱን ቱባ ሥራ ዲጂታል የባለቤትነት ካርታ ነው።

እንደ ቢትኮይን ያለ የዲጂታል ገንዘብ አንድ ቅጥያ የሆነው ኤንኤፍቲ ዓለምንና የገንዘብ ልውውጥን ከሥር መሠረቱ ይለውጣል ተብሎ የሚጠበቀው የክሪፕቶከረንሲ አካል ነው።

በዚህ ዘዴ የሚሸጠው የዲጂታል ሥዕል በምንም መንገድ እንዳይቀዳ፣ እንዳይባዛ፣ እንዳይጋራ ስለሚደረግ ዘላለሙን ቱባነቱን ይዞ ይቆያል።

አንድ ሰው ይህን ዓይነት ሥራ ሲገዛ የሥዕል ሥራው ወደሚገኝበትን ፋይል ለመግባት የሚያስችል ቁልፍ ወይም ዲጂታል ካርታ አገኘ ማለት ነው። ልክ ሰዎች ለመሬታቸው ካርታ እንደሚሰጣቸው ሥዕሉን የሚገዛው ሰው ዲጂታል የባለቤትነት ካርታን ያገኛል። ገንዘቡን በሥዕል ሥራው ላይ የሚከሰክሰውም ይህንኑ ለማግኘት ነው።

ይህም ካርታ በምንም መልኩ የማይደመሰስና በሌላ ሰው የማይቀዳ ዘላለማዊ የሥዕል ሥራ በእጅ የማስገባት መብትን ያስገኛል።

ይህ ሥዕል በድጋሚ በተሸጠ ቁጥር ፈጣሪው በመቶኛ ትርፍ ስለሚያገኝ ሁልጊዜም ተጠቃሚ እንዲሆን ያደርገዋል።

ሰዎች ቢትኮይንን በቢትኮይን ሊቀይሩ ይችሉ ይሆናል። ይህ የዲጂታል ካርታ ግን በምንም መልኩ ሊጋሩት ወይም ሊለዋወጡት የሚችሉት አይደለም።

አንድ ቢትኮይን በሌላ ቢትኮይን ቢቀየር በተመሳሳይ ጊዜ ከሆነ አንድ ብርን በአንድ ብር መቀየር እንደማለት ነው።

የይህንን ዲጂታል ካርታ ከሌላ ሰው ጋር ለመጋራት መሞከር ግን አንድን የኮንሰርት ትኬት ግማሹን ቆርጦ ለሰው የመስጠት ያህል ትርጉም አልባ ነው።

ይህ ቱባነቱ ነው ሰዎች በዲጂታል ገበያ እንዲወዳደሩና ገንዘባቸውን ከስክሰው ዲጂታል የሥዕል ባለቤትነት ካርታን እንዲገዙ የሚያደርጋቸው።

የፎቶው ባለመብት, Alana Edgington

የምስሉ መግለጫ,

አላና ኤዲንግተን ከልጆቿ

ሚሊየነርነት እንደዋዛ

አርቲስት አላና ጎበዝ ሠዓሊ ብትሆንም ራሷን "መሸጥ" የምትችል ሴት አልነበረችም። ዓይነ አፋር ናት፤ ሥራዎቿን ጋለሪ ለመውሰድ እንኳ ትፈራለች።

ስለዚህ በትርፍ ጊዜዋ ሥዕል እየሰራች 3 ልጆቿን በማሳደግ ተጠምዳ ነው የኖረችው። ኑሮዬን ከደጎመልኝ በሚል በዲግሪ የአበባ እርሻ ሳይንስ ስታጠና ቆየች።

እንደ ብዙ የዓለም ሕዝብ ሁሉ ሁልጊዜም ሐሳቧ ከዞረ ድምር የዕዳ እሽክርክሪት መቼ እንደምትወጣ ስትጨነቅ ነው የኖረችው። ኑሮ ሞልቶላት አያውቅም።

ሸራ ላይ በዘይት ቀለም የሠራችውን ሥዕሏን የሆነ ቀን ድንገት ወደ ድረ-ገጽ ገብታ በ500 ዶላር ስትሸጠው ለራሷ ደነገጠች።

በሌላ ቀን ወደ ድረ-ገጽ የሥዕል ጨረታ በገባችበት ጊዜ 16 ሥዕሎቿን በመቶ ሺህ የካናዳ ዶላር የሚገዛ ሰው አገኘች። ይህ ከአእምሮ በላይ ሆነባት። ማመን ተሳናት።

የ35 ዓመቷ አርቲስት አላና "ሰዎች ለእኔ ሥዕል ይህን ያህል ዋጋ ይከፍላሉ ብዬ ለማመን ተቸግሬያለሁ" ስትል ተናግራለች።

ይህ ስኬቷ የአርቲስቷን ሕይወት ወደ ሌላ ምዕራፍ አሸጋገረው።

መጀመርያ የኮሌጅ ትምህርት ክፍያዋን ከፈለች፣ ጣሪያ የነኩ የእዳ ክምሮቿን አቃለለች፣ ቤተሰቧን ወደ ሌላ ከተማ ወስዳ ማኖርም ጀመረች።

በአእምሮ እድገት ውስንነት ይሰቃይ የነበረውን አንድ ልጇን ጥሩ ሕክምና እንዲያገኝም አደረገች።

"ይህ የዲጂታል ሥዕል ግብይት በተለይ ለሴት አርቲስቶች አዲስ በር የከፈተ ነው" ትላለች አርቲስት አላና።

የፎቶው ባለመብት, Alana Edgington

የምስሉ መግለጫ,

22 ሺህ የካናዳ ዶላር የተሸጠው የአላና ዲጂታል ሥዕል

ኤንኤፍቲ ምንድን ነው?

ኤንኤፍቲ (NFT)ዲጂታል ሰርተፍኬት ወይም የሥዕል ባለቤትነት ካርታ እንደማለት ነው። የአንድን የፈጠራ ሥራ ባለቤትነት የሚመሰክር ዲጂታል ካርታ።

በክሪፕቶአርት ዓለም አንድን የፈጠራ ሥራ አንድ ሰው ብቻ በባለቤትነት ይዞት ይቆያል። ቱባውን የሥዕል ሥራ ማባዛትም፣ መቅዳትም፣ መለወጥም አይችልም።

ይህ ዲጂታል ሰርተፍኬት በብሎክቼይን ውስጥ ነው የሚገኘው።

ብሎክቼይን ቴክኖሎጂ የዲጂታል ገንዘብ ልውውጥና ግብይት የሆነውን ክሪፕቶከረንሲን የሚያስተዳድር ሲሆን ቢትኮይን የመሰሉ ዲጂታል ገንዘቦች በስሩ ይገኛሉ። ይህም ኤንኤፍቲ የዚህ አካል ነው።

ስለዚህ አንድ የሥዕል ሥራን ሁሉም ሰው ኦንላይን ገብቶ ቅጂውን ሊያየው ቢችልም ኤንኤፍቲ ግን ባለቤትነቱን ለገዛው ሰው ብቻ ስለሚሰጥ የሥዕሉ ባለቤት ያ ሰው ብቻ ይሆናል ማለት ነው።

ስለዚህ ሥዕሉን ሁልጊዜም በአስተማማኝ ጥበቃ ስር እንዲቆይ ያደርገዋል።

ልክ የቤት ካርታ እንደመያዝ ሁሉ የኤንኤፍቲ ካርታ መያዝ የባለቤትነት ሰርተፍኬት ያስገኛል።

አንድ የመሬት ባለቤት መሬቱን ሲሸጥ ካርታ እንደሚሸጠው ይህ ኤንኤፍቲ የፈጠራ ባለቤትነት መብት ለሌላ ሁለተኛ ሰው ለማስተላለፍም ተመሳሳይ ሂደትን ይከተላል።

ሰዎች ሥዕሉን በገዙበት ጊዜ ሁሉ ግን የፈጠራ ባለቤትነቱ የአርቲስቱ ሆኖ ይቆያል። ከሽያጩም በመቶኛ ክፍያን ያገኛል።

የፎቶው ባለመብት, Darius Puia

የምስሉ መግለጫ,

ዳሪየስ ፑያ

"ሙልጭ ያልኩ ድሀ ነበርኩ፤ድንገት በአንድ ጊዜ 250ሺህ ዶላር ጌታ ሆንኩ"

የሳይንስ ልቦለድና የ3ዲ አርቲስት ዳሪየስ ፑያ ሕይወቱን የቀየረውን አጋጣሚ ሲያስብ ይገረማል።

መጀመርያ ጓደኞቹ በድረ ገጽ ሥራዎቻቸውን መሸጣቸውን ሲነግሩት አላመነም ነበር። እስኪ ልሞክረው ብሎ ፈራ ተባ እያለ ገባበት።

ብዙም ተስፋ አድርጌ አልነበረም ዲጂታል ገበያውን የተቀላቀልኩት ይላል።

ዳሪየስ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ሳንቲሞችን ማግኘት ጀመረ።

አክሮፎቢያ የተሰኘው ዲጂታል ሥዕል ሥራው በአንድ ጊዜ 12 ሺህ ዶላር ተሸጠለት። ማመን አልቻለም።

"ፍቅረኛዬን ወዲያውኑ ደውዬ፣ ምን እየሆነ እንደሆነ ልትነግሪኝ ትችያለሽ? ይህ የማየው ነገር እውነት ነውን?" ስል ጠየቅኳት ይላል።

ከዚህ ስኬት በኋላ አርቲስት ዳሪየስን የሚያቆመው ሰው ጠፋ።

"ከ20 ቀናት በፊት ሳንቲም ቸግሮኝ ግራ የገባኝ ሰው ነበርኩ። በ20 ቀን ውስጥ የ250 ሺህ ዶላር ጌታ ሆንኩ፤ ይህም ማን ያምናል?" ይላል።

የፎቶው ባለመብት, Darius Puia

የምስሉ መግለጫ,

ከ35 ሺህ ዶላር በላይ የተሸጠው የዳሪየስ ዲጂታል ሥዕል

ዲጂታል ሥዕሎችን የሚገዛው ማን ነው?

ራጋቫንዴራ ራዉ በኬምብሪጅ ዩኒቨርስቲ የገንዘብና ተያያዥ ጉዳዮች ፕሮፌሰር ናቸው።

ይህ የዲጂታል ግብይት ዘላቂ ይሆናል ብለው እምብዛም አያምኑም። "ብዙ ሰዎች በወረርሽኙ ምክንያት ወደ ውጭ ስለማይወጡ ለዚያ ማካካሻ ገንዘባቸውን በዚህ መንገድ ወጪ እያደረጉት ነው የሚመስለው" ሲሉ ለቢቢሲ ሐሳባቸውን አጋርተዋል።

ፕሮፌሰሩ እንደሚተነብዩት ዲጂታል ግብይቱ ቢቀጥል እንኳ በዚህ ዘዴ ወደፊት ሁሉም አርቲስት ይሸጣል ማለት አይደለም። ምናልባት ገናናዎቹ ብቻ በዚህ የዲጂታል ግብይት ተፈላጊነታቸው ሊቀጥል ይችል ይሆናል።

"ገዢዎች ለጊዜው ብዙ ገንዘብ ሊያገኙ ይችላሉ፤ ብዙ ገንዘብም ሊያጡ ይችላሉ። እንዲህ ዓይነት ነገሮች አስተማማኝ አይደሉም፤ ጊዜያዊ ናቸው" ይላሉ።

በኤንኤፍቲ ገበያ ላይ ተሳታፊው ኔልሰን ሮህርባች በበኩሉ የክሪፕቶ አርት መነቃቃትና መጎልበት የአመጽ ያህል ነው ይላል። ለዓመታት አርቲስቶች ሲበዘበዙና ሥራቸውም ዋጋ እያጣ ቆይቷል። አሁን ያን ለመቀየር የተደረገ ተቃውሞ ነው።

እሱ እስካሁን 20 ሺህ ዶላር በማውጣት የተወሰኑ ሥዕሎችን መግዛት ችሏል። ያን ማድረጉ ትልቅ ኢንቨስትመንት እንደሆነ እንጂ ብክነት አድርጎ አያስበውም።

ወደፊት ግብይት የሚደረገው በዚህ መንገድ መሆኑ አይቀርም ይላል።

"አርቲስቶችን ማገዝ እፈልጋለሁ። አርቲስቶች ለሥራዎቻቸው ዋጋ ሲያገኙ ማየት ነው ህልሜ። ገንዘቤን በዚህ መንገድ ዲጂታል ሥዕል በመግዛት ማውጣቴ አደጋ አለው፤ ነገር ግን የሚመጣውን ለመቀበል ፍቃደኛ ነኝ" ብሏል።