ቅርስ፡ እስራኤል ውስጥ 'ታሪካዊ' የተባለ ጥንታዊ የብራና ጥቅልና ቅርስ ተገኘ

አሁን የተገኘው አዲስ ቅሪት የዘካሪያስና የናሆም መፅሐፍ ጥቅሶችን ይዘዋል

የፎቶው ባለመብት, ISRAEL ANTIQUITIES AUTHORITY

በእስራኤል በርሃ ውስጥ በሚገኝ ዋሻ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የብራና ጥቅል ስብርባሪዎችና የሌላ ቅርስ ቅሪት መገኘቱን ባለሥልጣናት አስታወቁ።

ባለሥልጣናቱ ግኝቱን "ታሪካዊ" ብለውታል።

እነዚህ የተገኙት በርካታ የብራናው ቁርጥራጮች በግሪክ የተጻፈባቸው ሲሆን የእግዚአብሔር ሥም ብቻ በእብራይስጥ ቋንቋ ተጽፎበታል።

ይህ የብራና ጥቅል የአይሁድ አማጺያን ሳይሆን እንደማይቀር ይታመናል።

የአይሁድ አማጺያን በሁለተኛው ክፍለ ዘመን በሮማ አገዛዝ ላይ ያካሄዱት አመፅ አለመሳካቱን ተከትሎ ወደ ተራሮች ተሰደው ነበር።

እነዚህ የብራና ጥቅሎች የተገኙት በአካባቢው ያሉ ዋሻዎችን ከዘረፋ ለመከላከል በተካሄደ ዘመቻ ወቅት ነው።

ከአውሮፓዊያኑ 1960ዎቹ መጀመሪያ ወዲህ እንዲህ ዓይነት ቅርስ ሲገኝ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።

የፎቶው ባለመብት, ISRAEL ANTIQUITIES AUTHORITY

የምስሉ መግለጫ,

የፈጣሪ ሥም የተጻፈበት የብራና ቁራጭ

በ1960ዎቹ መጀመሪያ 'አስፈሪ ዋሻ' በመባል በሚታወቀው በዚያው አካባቢ ተመሳሳይ የብራና ቁርጥራጮችና 40 አፅሞች ተገኝተው ነበር።

አሁን የተገኘው አዲስ ቅሪት የዘካሪያስና የናሆም መፅሐፍ ጥቅሶችን የያዙ ሲሆን ጥቅሶቹ የ12ቱ ንዑሳን ነብያት በመባል የሚታወቁት መጽሐፍ አካል ናቸው።

ቅሪቱ በግሪክ የተጻፈ ሲሆን ቋንቋው የተወሰደው ከክርስቶስ ልደት በፊት በአራተኛው ክፍለ ዘመን ታላቁ እስክንድር የእስራኤሎችን ምድር ከወረረ በኋላ ነው። ይሁን እንጅ የእግዚአብሔር ሥም በእብራይስጥ ቋንቋ በግልጽ ተጽፎ ይገኛል።

የእስራኤል የቅርስ ባለሥልጣን ዳሬክተር እስራኤል ሀሰን "ጥቅሉና ሌሎች በሥፍራው የተገኙ ቅርሶች ዋጋቸው የማይተመን ነው" ብለዋል።

ከአይሁዶች ሽንፈት ወዲህ እምብዛም ያልተለመዱ ሳንቲሞች፣ 6 ሺህ ዓመታት ያስቆጠረ እንዳይፈርስ የተደረገ የህጻን አጽም እና 10 ሺህ 500 ዓመታት የተቀመጠ ትልቅ ቅርጫትም በቦታው ተገኝቷል።

ይህ ዋሻ 80 ሜትር ከፍታ ላይ ይገኛል።

ወደ ዋሻው በቀላሉ መሄድ ግን የማይታሰብ ነው። ወደዚያ መድረስ የሚቻለው ተራራውን እየቧጠጠ መውጣትም ሆነ መውረድ ኢሊያም በገመድ ታስሮ መውረድ መቻልን ይጠይቃል።

ጉዞው የአገሪቷ የቅርስ ባለሥልጣን "በጣም ውስብስብና ፈታኝ" ያለው የዋሻዎቹን ስብስብ ከቅርስ ዘራፊዎች ለመጠበቅ የተደረገ ዘመቻ አካል ነበር።

በጁዳን በርሃ ተራራዎችና ዋሻዎች በተደረገ ፍለጋ ከአስርተ ዓመታት ወዲህ በዓለማችን የታወቀው የአይሁድ መጽሐፍ [የሙት ባህር ጥቅሎች] እና የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎችን ጨምሮ ሌሎች ጥንታዊ ቅርሶችን የያዘ ግምጃ ቤቶች ተገኝቷል።