ልደቱ አያሌው፡ አቶ ልደቱ ለሕክምና ከአገር እንዳይወጡ ለሁለተኛ ጊዜ ለምን ተከለከሉ?

አቶ ልደቱ አያሌው

የፎቶው ባለመብት, The Reporter

የቀድሞው ኢዴፓ የብሔራዊ ምክር ቤት አባልና ፖለቲከኛው አቶ ልደቱ አያሌው ለሕክምና ወደ ውጪ አገር እንዳይሄዱ ለሁለተኛ ጊዜ መከልከላቸውን ለቢቢሲ ገለፁ።

አቶ ልደቱ እንደሚሉት፤ ባጋጠማቸው የልብ የደም ቧንቧ መዘጋት ችግር ምክንያት በአሜሪካ አትላንታ በሚገኝ ኢስት ሳይድ ሆስፒታል ሕክምና ያደረጉት ከዛሬ አንድ ዓመት ከስምንት ወር ገደማ በፊት ነበር።

በወቅቱ በልባቸው ሦስት የደም ቧንቧዎች ላይ ችግር በመኖሩ ለአንዱ ሕክምና ተደርጎላቸውና ሁለቱ የሚገኙበት ቦታ አስቸጋሪ በመሆኑ መድኃኒት እየወሰዱ እንዲቆዩና ከስድስት ወር በኋላ እንዲመለሱ ነበር ሆስፒታሉ ቀጠሮ የሰጣቸው።

ነገር ግን ለቀጠሯቸው ሰባት ቀናት ገደማ ሲቀራቸው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ይናገራሉ።

አቶ ልደቱ በቁጥጥር ሥር የዋሉት የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ አመፅ ለማስነሳት አስተባብረዋል በሚል ነበር።

አምስት ወራትን በእስር ካሳለፉ በኋላም፤ ከሁለት ወራት በፊት በ30 ሺህ ብር ዋስ ከእስር መለቀቃቸው ይታወቃል።

ፖለቲከኛው እንደሚሉት ያኔ በእስር ላይ ሳሉም ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ጤናቸው አስጊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ጠበቆቻቸውና የፓርቲያቸው ፕሬዚደንት አቤቱታ ሲያቀርቡ ነበር።

ይሁን እንጂ የውጪ አገር የሕክምና ጥያቄያቸው ከቀረበባቸው ክሶች ነጻ ከተባሉ በኋላም መልስ አላገኘም።

"በእስር ቤት አምስት ወራት፤ ከተፈታሁ ደግሞ ሁለት ወራት ተቆጥረዋል። ቀጠሮዬም ስምንት ወር አለፈው" ይላሉ።

የታሰሩበትና በእስር ቤት የቆዩበት መንገድ ሕገ ወጥ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ልደቱ፤ የቀረበባቸው ክስ ዋስትና የሚያስከለከል ባይሆንም ዋስትናቸውን ለማስከበር ውጣ ውረድ እንደነበረው ይናገራሉ።

በእስር ላይ ሳሉም ከኮሮናቫይረስ ወረርሽን ጋር ተያይዞ ያለባቸው የጤና ሁኔታ አስጊ በመሆኑ ሐኪሞቻቸው ዝርዝር የሕክምና ማስረጃቸውን አቅርበው ዋስትና እንደተፈቀደላቸው አስታውሰዋል።

'ያልተፈቀደ መሳሪያ መያዝ' በሚል በቀረበባቸው ክስ የዋስ መብታቸው ሲጠበቅላቸው ፍርድ ቤት ለመቅረብ የሁለት ወር ቀጠሮ የተሰጣቸው፤ "ውጭ አገር ታክሜ እንድመለስ በቂ ጊዜ እንዳገኝ ነበር" ይላሉ።

ከአገር እንዳይወጡ ለምን ተከለከሉ?

አቶ ልደቱ እንደሚሉት የዋስትና መብታቸው ከተከበረላቸው በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ውጭ አገር ለመሄድ ወደ አየር ማረፊያ ሲሄዱ እንዲመለሱ ተደርገዋል።

"የፍርድ ቤት እግድ አላችሁ ወይ?" ሲሉ ቢጠይቁም "የፍርድ ቤት እግድ የለንም። የብሔራዊ ደኅንነት ሠራተኞች ነን። የታዘዝነው ከመሥሪያ ቤታችን ነው። መውጣት አትችልም አሉኝ" ይላሉ።

ከአገር እንዳይወጡ የከለከላቸው ፍርድ ቤት ካለ እንዲነግሯቸው ቢጠይቁም፤ "የምናውቀው ነገር የለም አለቆቻችንን አነጋግር" የሚል ምላሽ ብቻ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።

በዚህ ጊዜ 'ሕገ-መንግሥቱን እና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን መናድ' በሚል የቀረበባቸው ክስ አልተዘጋም ነበር።

ምን አልባት ሰበቡ ይህ ሊሆን ይችላል ብለው አስበው የነበረ ቢሆንም፤ ይህ የክስ መዝገብ ከተዘጋ በኋላም ለሁለተኛ ጊዜ ከአገር መውጣት አለመቻላቸውን ይናገራሉ።

"ከቀረበብኝ ክስ ነጻ መሆኔን የሚያሳይ የፍርድ ቤት ውሳኔ አስተርጉሜ ይዤ ብቀርብም ከአለቆቻቸው ጋር ተነጋግረው 'አሁንም አልተፈቀደልህም' ብለው አሰናበቱኝ" ይላሉ።

አቤቱታ ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽን

አቶ ልደቱ እንደሚሉት መጀመሪያ ከአገር እንዳይወጡ ሲከለከሉ፤ ለሠላም ሚኒስቴር፣ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ለደኅንነት መሥሪያ ቤት እና ለሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በሕይወት የመኖር መብታቸው እንዲከበርላቸው ጥያቄ አቅርበው ነበር።

በወቅቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤትና የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጥያቄያቸውን ተቀብለው እንዳነጋገሯቸው፤ ሌሎቹ ግን ሊያነጋግሯቸው ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውን አቶ ልደቱ አስታውሰዋል።

ያነጋገሯቸውም "የራሳችንን ጥረት እያደረግን ነው፤ እስካሁን የተገኘ መፍትሔ የለም" የሚል መልስ እንደሰጧቸውም ይናገራሉ።

አሁን ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ደብዳቤ ያስገቡትም ጥያቄዬን በጽሁፍ እንዳስገባ ስለተጠየቅኩ ነው ብለዋል።

"አሁንም የራሳችንን ክትትል እናደርጋለን ነው ያሉኝ " ይላሉ።

ነገር ግን አቶ ልደቱ እነዚህ መሥሪያ ቤቶች መፍትሔ ይሰጡኛል የሚል እምነት እንደሌላቸው ይናገራሉ።

"ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥትም እንደ መንግሥት፤ ተቋም ወይም ባለሥልጣን የሚወስን ያለ አይመስለኝም። የሚወስነው አንድ ሰው ነው። በእኔ ጉዳይ የማየው ይህንን ነው" ሲሉም ምክንያታቸውን ያስቀምጣሉ።

ባለሥልጣናት የሚወስኑ ቢሆንና ሕግ ተቀባይነት ቢኖረው፤ መንግሥትና ሕግ ባለበት አገር የአንድ ዜጋ መብት በዚህ መልኩ ሊጣስ እንደማይችልም ያክላሉ።

"ባለሥልጣናትም፣ ተቋማትም፤ ሕግም የለም። ውሳኔ የሚሰጠው በግለሰቦች በጎ ፈቃድ ብቻ ነው። ከዚህ በኋላ ተስፋ አድርጌ የምጠይቀው አካል የለም። የሚሆነውን ማየት ነው" ብለዋል አቶ ልደቱ።

"የቂም በቀል ጉዳይ እንደሆነ መረዳት ይቻላል"

አቶ ልደቱ ጉዳያቸውን በተመለከተ የተለያዩ ባለሥልጣናትን ማናገራቸውን ይጠቅሳሉ፤ "መፍትሔ ይሰጡኛል ያልኳቸውን አካላት ሁኑ አናግሬያለሁ፤ ግን ፈቃደኛ አልሆኑም። የቂም በቀል ጉዳይ እንደሆነ ከአካሄዱ መረዳት ይቻላል" በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።

ለዚህም አያያዛቸው ሕገ ወጥ እንደነበር፣ አዲስ አበባ ተይዘው ኦሮሚያ መታሰራቸው እና የዋስትና መብታቸው ሲከበር መንግሥት ሊለቃቸው ፈቃደኛ እንዳልነበር ያነሳሉ።

"የጤናዬን ጉዳይ እኮ ከሐኪሜ ቀጥሎ መንግሥት ያውቀዋል። እኔ በጤናዬ ጉዳይ የምላላከውን ኢሜይል መንግሥት ያውቀዋል። ነገር ግን በውንጀላ ምክንያት አላስኬደኝ ብሏል" ሲሉም በጤና ምክንያት ሕይወታቸውን እንዲያጡ ካልተፈለገ በስተቀር ፤ የሚያስከለክላቸው ሌላ ምክንያት እንደሌለ ይናገራሉ።

አንዳንዶች ለክልከላው ከአገር ወጥተው ይቀራሉ የሚል ስጋት ሊሆን ይችላል ቢሉም አቶ ልደቱ ግን፤ "እንደዚህ እንደማላደርግ ያውቃሉ። ታክሞ ይድናል ነው እንጂ፤ ሄዶ ይቀራል ብለው አይደለም" ሲሉ ከአገራቸው ውጭ የመኖር ፍላጎት እንደሌላቸው ተናግረዋል።

"የፖለቲካ ታጋይ ነኝ በሕጋዊ መንገድ ሄጃለሁ፤ ከዚህ በኋላ ማንንም ባለሥልጣን ልለምን ወይም ልማፀን አልችልም፤ እንደ ትግሉ አካል ነው የምቆጥረው። ሕይወቴን ካጣሁም እንደከፈልኩት ዋጋ ነው የምቆጥረው" ብለዋል።

ለዚህ ሁሉ ችግር እንደምክንያት የሚተቅሱትም መንግሥትን ስለሚቃወሙ፣ የሽግግር መንግሥት ይቋቋም፤ ከመስከረም 30 በኋላ መንግሥት የለም ብለው በመናገራቸው በመንግሥት ቂም እንደተያዘባቸው ነው።

ይህንን ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአደባባይ 'እርምጃ እንወስዳለን' ሲሉ መዛታቸውን ያስታውሳሉ።

ከዚህ ባሻገር የብልፅግና ፓርቲ አባል እንዲሆኑ ተጠይቀው ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውም ባለሥልጣናቱን ሊያስከፋቸው እንደሚችል ያስባሉ።

"ይህ የእኔ የትግል አካል ነው። የሚያሳስበኝ አገሪቷ እንደ አንድ መንግሥትና ሥርዓት ሳይሆን እንደ አንድ ተንኮለኛና ቂመኛ ግለሰብ የሚያስብ ሥርዓት ውስጥ መውደቋ ነው" ብለዋል።

አቶ ልደቱ እንደሚሉት አሁን ከእርሳቸው ጉዳይ ይልቅ፤ የአገራቸው ሁኔታ እንደሚያሳስባቸው ይናገራሉ።

አገሪቷ ላይ የሚታየው ተስፋ አስቆራጭ ቢሆንም እርሳቸው ግን አሁንም አቅማቸው በፈቀደ መጠን አገራቸው ልትድን የምትችልበትን ትግል እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።