ኮቪድ-19፡ የኮሮናቫይረስ ሥርጭት ያሰጋቸው ፈረንሳይና ፖላንድ በከፊል የእንቅስቃሴ ገደብ ጣሉ

የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አድርጋ የምትራመድ ሴት

የፎቶው ባለመብት, EPA

ፈረንሳይና ፖላንድ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በመጨመሩ በከፊል የእንቅስቃሴ ገደብ ጥለዋል።

ይህም በፈረንሳይ መዲና ፓሪስን ጨምሮ 16 በአካባቢዎች የሚኖሩ 21 ሚሊየን ሰዎችን እንቅስቃሴ አስተጓጉሏል።

አገሪቷ ሦስተኛ ዙር ወረርሽኝ እንዳይገጥማት ሰግታለች።

በሌላ በኩል በፖላንድ አንገብጋቢ ያልሆኑ ሱቆች፣ ሆቴሎች፣ የባህልና ስፖርት ማዕከላት ለሦስት ሳምንታት ተዘግተዋል።

አገሪቷ ከኅዳር ወር ወዲህ በአንድ ቀን ከፍተኛ የተባለው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ተመዝግቦባታል።

የኮሮናቫይረስ ሥርጭት በጀርመንም እየጨመረ ሲሆን መራሔተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል አገሪቷ አስቸኳይ የተሽከርካሪዎች የእንቅስቃሴ ገደብ እና ቤት ውስጥ የመቀመጥ ገደብ ልትጥል እንደምትችል አስጠንቅቀዋል።

በአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት የክትባቱ ሥርጭት በአቅርቦት መዘግየት እንዲሁም በርካታ የአውሮፓ አገራት የኦክስፎርዱ አስትራዜኔካ ክትባት ተጓዳኝ የጤና ችግር ያስከትላል በሚል ስጋት በማገዳቸው እንቅፋት ገጥሞታል።

በፈረንሳይና በፖላንድ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?

በፈረንሳይ በግማሽ የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ ከአርብ ሌሊት ጀምሮ ተግባራዊ ሆኗል።

ከፓሪስ ተነስተው እንደ ብሪታኒይ እና ሊዮን ባሉ የእንቅስቃሴ ገደብ ባልተጣለባቸው አካባቢዎች የሚሄዱ ባቡሮች ገደቡ ተግባራዊ ከመሆኑ ከሰዓታት በፊት ሙሉ በሙሉ ተይዘው ነበር ተብሏል።

መዲናዋን ለቀው በሚወጡ ተሽከርካሪዎችም በርካታ መንገዶች ተጨናንቀው ነበር።

ይሁን እንጂ አሁን የተጣለው ገደብ እንደ ከዚህ ቀደሙ የጠበቀ አይደለም። ሰዎች ከቤታቸው ውጭ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ይፈቀድላቸዋል።

በአገሪቷ አንገብጋቢ ያልሆኑ የንግድ ተቋማትም የተዘጉ ሲሆን፤ ትምህርት ቤቶችና ፀጉር ቤቶች ግን የጥንቃቄ መመሪያዎችን ከተከተሉ ክፍት ሆነው ይቆያሉ ተብሏል።

እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ ከሆነ በፈረንሳይ እስካሁን ከ4.2 ሚሊየን በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ከበሽታው ጋር በተያያዘ 92 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ህይወት አልፏል።

በፖላንድ ለሦስት ሳምንታት የተጣለው ገደብ የጀመረው ቅዳሜ ዕለት ነው።

የአገሪቷ የጤና ባለሥልጣናት በእንግሊዝ ተገኘ የተባለው አዲስ የኮሮናቫይረስ ዝርያ በአገሪቷ መስፋፋቱን ተከትሎ የእንቅስቃሴ ገደብ መጣል አስፈላጊ እንደሆነ ቀደም ብለው አስጠንቅቀው ነበር።

አዲሱ የቫይረስ ዝርያ እስካሁን ከተመዘገበው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 60 ከመቶ በላዩን ይይዛል።

እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ በፖላንድ ከ2 ሚሊየን በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን፤ 49 ሺህ የሚጠጉ ሰዎችም ህይወታቸው አልፏል።

አርብ ዕለት ጀርመን ጎረቤቷን ፖላንድን ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ አደገኛ ከሆኑ አገራት ዝርዝር ውስጥ አስገብታታለች።

በመሆኑም ከእሁድ ጀምሮ ከፖላንድ የጀርመንን ድንበር የሚያቋርጥ ማንኛውም ሰው ከኮሮናቫይረስ ነጻ መሆኑን የሚያሳይ የሕክምና ወረቀት ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።