ዶናልድ ትራምፕ፡ ፍሎሪዳ በሚገኘው የትራምፕ መኖሪያ ቤት የኮሮና ወረርሽኝ መከሰቱ ተነገረ

ማር አ ላጎ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ፍሎሪዳ ውስጥ የሚገኘውና ማር-ኤ-ላጎ የሚባለው የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ግዙፉ ዋነኛ መኖሪያ ቤት ውስጥ የኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ በመገኘቱ ምክንያት በከፊል መዘጋቱ ተገለፀ።

መኖሪያ ቤታቸው በከፊል የተዘጋው የተወሰኑ ሠራተኞቻቸው በኮቪድ-19 መያዛቸው በመረጋገጡ እንደሆነ የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ይህ የፕሬዝዳንቱ መኖሪያ በዘንባባ በተከበበችው የባህር ዳርቻ ግዛት ፍሎሪዳ የሚገኝ ታሪካዊ ቤት ነው።

በፍሎሪዳ የሚገኘው ይህ ቤት የቀድሞው ፕሬዚደንት ጥር ወር ላይ ዋይት ሐውስን ለቀው ከወጡ በኋላ በይፋ የሚታወቅ መኖሪያ ቤታቸው ሆኖ እያገለገለ ነው።

ድርጅቱ በግለጫው እንዳስታወቀው የባህር ዳርቻው ክለብ እና የሬስቶራንቱ መመገቢያ ክፍል ተዘግቷል።

ይሁን እንጅ ምን ያህል ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙ መግለጫው ያለው ነገር የለም።

ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ጥቅምት ወር በኮሮናቫይረስ ተይዘው የነበረ ሲሆን ጥር ላይ ክትባቱን ወስደዋል።

በበሽታው ተይዘው በነበረበት ወቅት ለበርካታ ቀናት ሆስፒታል ገብተው ነበር።

በታመሙ ወቅትም የተለያዩ የመተንፈሻ ህመሞችን ለማከም የሚረዳውን ዴክሳሜታሶን የተባለ መድኃኒት አነስተኛ መጠን በመውሰድ እንደታከሙ ተገልጿል።

ይህ መድኃኒት ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ በፅኑ ሕክምና ላይ የሚገኙ ህሙማንን የሞት መጠን እንደሚቀንስ፤ ነገር ግን አዎንታዊ ጠቀሜታውም በቁጥር ደረጃ ሲሰላ አነስተኛ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ለቀድሞ ፕሬዚደንቱ ቅርብ የሆኑ በርካታ የዋይት ሐውስ ባለሥልጣናት እንዲሁም ባለቤታቸው ሜላኒያ ትራምፕ እና ወንድ ልጃቸው ባሮንም በቫይረሱ ተይዘው ነበር።

ዋሽንግተን ፖስት ለሪዞርቱ ሠራተኞች ከተላከ የኢሜይል መልዕክት አገኘሁት ባለው መረጃ፤ የቀድሞው ፕሬዝደንት ቤት አስተዳደር አስፈላጊ የሆኑ የጥንቃቄ እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሆነ አስታውቋል።

የግብዣ እና ሌሎች ዝግጅቶች አገልግሎቶች ግን ክፍት ይሆናሉ ብሏል።

ጥር ወር ላይ በዚህ ቤት ውስጥ በተካሄደውና የአዲስ ዓመት ዋዜማ ዝግጅትን በሚያሳየው ምስል ላይ በርካታ እንግዶች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ ታይተዋል።

ይህንንም ተከትሎ ዝግጅቱ የኮሮናቫይረስ ሕግን ጥሷል በሚል ሪዞርቱ ከግዛቷ ይፋዊ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ድርጅቱ በሚቀጥለው ወር በሪፐብሊካን ፓርቲ ብሔራዊ ኮሚቴ የመዝናኛ ዝግጅትን ለማሳናደት ማቀዱንም ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል።