ፊንላንድ የደስተኞች አገር በመሆን ከዓለም ቀዳሚ ሆናለች፤ ኢትዮጵያስ?

የሚስቁ ሴቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፊንላንድ ለአራት ዓመታት በተከታታይ የደስተኛ ሰዎች መኖሪያ መሆኗን ስታረጋግጥ ኢትዮጵያ ደግሞ በ133ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሚደገፈው በዚህ ዓመታዊ የዓለም አገራት ሕዝቦችን ደስተኝነት በሚለካው ጥናት መሠረት፤ ከመጀመሪያው ረድፍ ላይ የሚገኙት የአውሮፓ አገራት ናቸው።

የ149 አገራት ሕዝቦችን የደስተኝነት ደረጃን ባስቀመጠው ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያ 133ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ከአፍሪካ አገራት በተሻለ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሊቢያ [80ኛ]፣ ኮንጎ ብራዛቪል [83ኛ] እና አይቮሪ ኮስት [85ኛ] ናቸው።

የኢትዮጵያ ጉረቤቶች ከሆኑት አገራት መካከል በዝርዝሩ ውስጥ የተካተተችው ኬንያ ስትሆን በ121ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ከዓለም አገራት በተለያዩ መለኪያዎች ደስተኛ ሕዝብ ያላት ቀዳሚዋ አገር ፊንላንድ ስትሆን ዴንማርክ ሁለተኛ፣ ስዊትዘርላንድ ሦስተኛ፣ አይስላንድ አራተኛ እና ኔዘርላንድስ አምስተኛ በመሆን ተከትለዋታል።

ጥናቱ ደስተኛ የሆኑ ዜጎች እንዳሏቸው የመሰከረላቸውና ከአንደኛ እስከ አስረኛ ደረጃ ከያዙት አገራት ውስጥ አውሮፓዊ አገር ያልሆነችው ኒው ዚላንድ ብቻ ናት።

ይህ ውጤት የተገኘው ጋሉፕ በተባለው የመረጃ ተንታኝ አማካይነት ደስተኛነታቸውን ለማወቅ ከ149 የዓለም አገራት በተሰበሰበ መረጃ መሠረት ነው።

ይህ የሰዎች የደስተኝነት ሁኔታ የተለካው የሚያገኙት ማኅበራዊ ድጋፍ፣ ግለሰባዊ ነጻነት፣ ጠቅላላ አገራዊ ምርት (ጂዲፒ) እና በአገራቱ ውስጥ ባለው የሙስና መጠንን ጨምሮ ሌሎችንም መመዘኛዎች በመመልከት ነው።

በዚህ ዓመቱ ጥናት ከዓለም አገራት ውስጥ ደስተኛ ያልሆኑ ሕዝቦች ይኖሩባቸዋል የተባሉት አፍጋኒስታን፣ ሌሶቶ፣ ሩዋንዳ እና ዚምባብዌ ናቸው።

የጥናቱ አዘጋጆች እንዳሉት ዓለምን ባጠቃት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሰበብ አንድ ሦስተኛ በሚሆኑ አገራት ውስጥ "አሉታዊ የሆኑ ስሜቶች በተደጋጋሚ የመከሰታቸው ሁኔታ ከፍተኛ ነበር" ብለዋል።

ቢሆንም ግን ባለፈው ዓመት በ22 አገራት ውስጥ ነገሮች መሻሻል አሳይተዋል። በርካታ የእስያ አገራት ባለፈው ዓመት ከነበራቸው ደረጃ መሻሻልን ሲያሳዩ ቻይና ቀደም ባለው ዓመት ከነበራት የ94ኛ ደረጃ ወደ 84ኛ ከፍ ብላለች።

አጥኚዎች እንዳሉት በአንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው ፊንላንድ በወረርሽኙ ወቅት የሰዎችን ህይወትና ኑሮ በመንከባከብ በኩል ከሁሉም አገራት በላቀ ሁኔታ ከፍተኛ ነጥብን አግኝታለች።

የስካንዴኔቪያን አገር የሆነችው ፊንላንድ 5.5 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ሲሆን ከሌሎቹ የአውሮፓ አገራት በተሻለ ሁኔታ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር ችላለች። በጆንስ ሆፕኪንስ መረጃ መሠረት በአገሪቱ ከ70,000 ሰዎች በላይ በበሽታው የተያዙ ሲሆን 805 ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል።

በወጣው ሪፖርት መሠረት አስሩ የደስተኛ ሰዎች መኖሪያ የሆኑት አገራት ፊንላንድ፣ ስዊትዘርላንድ፣ አይስላንድ፣ ኔዘርላንድስ፣ ኖርዌይ፣ ስዊዲን፣ ሉክሰንበርግ፣ ኒው ዚላንድና ኦስትሪያ ናቸው።