የቦምብ ማስፈራሪያና ግድያ የከበባቸው የእስያው ቁንጮ ሃብታም

የሙኬሽ አምባኒ ቤት

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታኅሣስ 18/2013 ዓ.ም ጥዋት በተቀጣጣይ ፈንጂዎች የተሞላ መኪና በእስያው ቁንጮ ሃብታም ቤት ሙኬሽ አምባኒ ቤት አጠገብ ተገኘ።

ሙኬሽ አምባኒ መኖሪያቸው ሕንድ ሙምባይ ነው።

በሚቀጥሉት ቀናት ደግሞ ቦምብና ተቀጣጣዮች ተሞልቶ ነበር የተባለው መኪና ባለቤት አስከሬን በባሕር ዳርቻ ላይ በውሃ ወደ ዳር ተገፍቶ ተገኘ።

በሕንድ የንግድ መዲና አጠገብ በሚገኘው ባሕር ዳርቻ የተገኘው አስከሬን በቁጥጥር ስር መዋሉን ፖሊስ አስታውቋል።

በአሁኑ ወቅት የፌደራል ፖሊሶች ከዚህ ግድያ ጀርባ ያለውን እንቆቅልሽ ለመፍታት ተጠምደዋል። እንዴትስ ነው ከቱጃሩ ጋር ግንኙነትስ ያለው?

እንዴት ተጀመረ?

የሙምባይ ፖሊስ እንደሚለው 27 ፎቅ ያለውን የቱጃሩን ሙኬሽ አምባኒ ከሚጠብቁት የፀጥታ አካላት መካከል አንደኛው ግለሰብ አረንጓዴ ቀለም ያላትና ሕንድ ሰራሿን መኪና ቱጃሩ ቤት አጠገብ ቆማ አየ። መኪናዋ ላይ ተቀጣጣይ ነገሮችን ማየቱን ተከትሎ ፖሊስ ጠራ።

ፖሊስም ቦምብ የሚያመክን ቡድኑን ይዞ መኪናዋን መመርመር ጀመረ። መኪናዋም ውስጥ 2.5 ኪሎግራም ክብደት ያለው ጌሊግናይት የተባለውን ተቀጣጣይ ቦምብ አገኙ። ይህ ጌሊግናይት የተሰኘው ፈንጂ በቅርፁ ዱላ መሳይና በስዊድናዊው የኬሚስትሪ ባለሙያ አልፍሬድ ኖቤል የተፈለሰፈውና በዋጋውም ረከስ ያለ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Mumbai Police

ዱላ መሳይ ተቀጣጣዮቹ ከምንም መሳሪያ ጋር አልተገናኙም እንዲሁም እርስ በርሳቸው መደራረብ ቢጠበቅባቸውም እንዲሁ አልተደረገም። የቦምብና ተቀጣጣይ መሳሪያዎች ባለሙያ የሆኑ አንድ ግለሰብ ለኢንዲያ ቱደይ እንደተናገሩት ቦምቡ ቢፈናዳ ኖሮ ሙሉ በሙሉ መኪናዋን ያወድማት ነበር ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ መኪናው ውስጥ አምስት የመኪና ፈቃድና የሰሌዳ ቁጥር የተመዘገበባቸው ወረቀቶች፣ እንዲሁም ለሙኬሽ አምባኒና ባለቤታቸው ኒታ የተፃፈ ማስታወሻ ተገኝቷል።

ማስታወሻውም "ይሄ በተወሰነ መልኩ ፍንጭ እንዲሆንህ ነው። አሁን ተቀጣጣዮቹን አላገናኘናቸውም። በሚቀጥለው ጊዜ ግን ሙሉ ቤተሰብህን ነው የምናፈነዳው" ይላል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ,

ሙኬሽ አምባኒ

ሙኬሽ አምባኒ ሪሊያንስ ኢንደስትሪስ የተባለው ኩባንያ ሊቀ መንበር ናቸው። አንጡራ ሃብታቸውም 76 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል።

ዋነኛ የቱጃሩ ሃብትም ነዳጅ ማጣሪያ ቢሆንም ቴሌኮምን ጨምሮ ሌሎች ዘርፎች ላይ ኢንቨስትመንት አላቸው።

ስለተተወችው መኪና ምን እናውቃለን?

የሙምባይ ፖሊስ እንዳስታወቀው ይህቺ መኪና ያለቦታዋ የተገኘች ናት። የሙኬሽ አምባኒ ቤት የሚገኘው ካርማይክል ተብሎ በሚጠራው መንገድ ለመኖሪያ ተብሎ በተከለለው ስፍራ አፓርትመንት አካባቢም ነው።

ፖሊስ በአካባቢው ያለ የደኅንት መቆጣተሪያ ካሜራን በማት ደረስኩበት ባለው መረጃ መኪናዋ የተነሳችው ከሙኬሽ አምባኒ መኖሪያ 15 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ካለ ስፍራ ነው። ስኮርፒዮ የተሰኘ ስያሜ ያላት ይህች መኪና ሌሊት 7 ሰዓት ላይ ቆማ የነበረ ሲሆን ከዚያም አንድ ሌላ ቶዮታ መኪና ሲደርስ ተከታትለው ቱጃሩ ለባለፉት 10 ዓመታት ወደኖረበት ስፍራ አቀኑ።

መኪኖቹ በስፍራው ሲደርሱ ከሌሊቱ 8፡30 ነበር። ከሙኬሽ ቤት 500 ሜትር ርቀት ሲደርሱ ቆሙ። ፖሊስ እንደሚለው ከስኮርፒዮዋ መኪና ጭምብል ያጠለቀ ግለሰብ ወረደና በቶዮታው ተሳፈረ። ከዚያም ቶዮታዋን እየነዱ ሄዱ።

የፎቶው ባለመብት, Mumbai Police

በተቀጣጣይ የተሞላችው መኪና ባለቤማን ነው?

የስኮርፒዮዋ መኪና ባለቤትት ማንሹክ ሃይረን የተባለ የአካባቢው ነጋዴና የመኪና መለዋወጫ ግለሰብ ነው።

ማንሹክ ከፖሊስ በቀረበለት ጥያቄ ሲመልስም መኪናው የእሱ እንዳልሆነችና የማደስ ሥራ ያልከፈለ ግለሰብ እንደሆነ ተናገረ። ግለሰቡ መክፈል ባለመቻሉ መኪናዋን በተያዥነት መያዙን ገለፀ።

የፎቶው ባለመብት, Mumbai Police

የምስሉ መግለጫ,

ማንሹክ ሂረን

ይኼው የመኪናው ባለቤት ግለሰብ ለፖሊስ እንደተናገረው ከሙምባይ ወደ ሌላ ከተማ ለመሄድ ባቡር ጣቢያ በሄደበት ወቅት መኪናው በመበላሸቱ እዚያው አቁሟት እንደሄደ ነበር። በነጋታው መኪናውን ለመውሰድ ወደ ቦታው ሲሄድ ካቆመበት ሊያገኘው አልቻለም። በአቅራቢያው ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ አምርቶ መኪናው እንደተሰረቀ አስታወቀ።

መኪናው ከቱጃሩ ቤት አቅራቢያ በተቀጣጣዮች ተሞልቶ የመገኘቱ ዜና በሕንድ መነጋገሪያም ሆነ። የመኪናው ባለቤትም ብቸኛው እማኝ ስለሆነ ጥበቃ እንዲደረግለትም ጥሪ ቀረበ። ነገር ግን ከሰዓታት በኋላ የማንሹክ ሂረን አስከሬን በሙምባይ አቅራቢያ ከሚገኝ የባሕር ዳርቻ ተገኘ።

ስለ ማንሹክ ሂረን ሞት ምን እናውቃለን?

ፖሊስ እንደሚለው የካቲት 25 ምሽት ሱቁን ዘግቶ ወደቤቱ ሄደ።

ቤቱም ከደረሰ በኋላ ታውዴ የሚባል ፖሊስ እንደደወለለትና ሊያገኘውም እንደሚወጣ ለቤተሰቦቹ ተናግሯል።

ነገር ግን በዚያችው ምሽት አልተመለሰም። በነገታው ቤተሰቦቹ ጠፍቷል ብለው ለፖሊስ አመለከቱ።

ፖሊስ በበኩሉ ሂረን ከቤቱ ማታ ሁለት ሰዓት ላይ እንደወጣና ከሦስት ሰዓት በኋላም ስልኩ እንደተዘጋ ተናግሯል።

በዚያችን ምሽት አገኘዋለሁ ብሎ የወጣው ፖሊስ ማንነት እስካሁን ድረስ አይታወቅም።

ፖሊሶች ምርመራ በጀመሩበት ወቅት ድንገት አንድ አስከሬን ከባህሩ ወደ ዳርቻው ተገፍቶ ወጥቶ እንደተገኘ ተነገራቸው።

በውሃ የተነፋው አስከሬን ከአራት- እስከ አምስት በሚሆኑ መሃረቦችም ፊቱ ተጠቅልሎ ነበር።

በአሁኑ ወቅት የአስከሬኑ የመጀመሪያ ምርመራ ቢጠናቀቅም የግለሰቡ አሟሟት የሚታወቀው ሙሉው ሪፖርት ሲጠናቀቅ ነው።

የሂረን አሟሟት ሴራ የተሞላበትና መረጃዎችንም ለማጥፋት ሙከራ ተደርጓል በማለት የሂረን ባለቤት ከሳለች። ከዚህም በተጨማሪ በተቀጣጣይ የተሞላው መኪናን በተመለከተም የብሔራዊ ምርመራ ኤጀንሲ የፀረ-ሽብር ዘርፍ በጥልቀት እየመረመርኩት ነው ብሏል።

ፖሊስ ለምን ታሰረ?

በቱጃሩ ቤት አጠገብ የተተወች መኪናን በተመለከተ መረጃ ከደረሳቸውና ወደ አካባቢው ከደረሱት መካከል ሳሺን ዌዝ የተባለ ፖሊስ አንዱ ነው። ፖሊሱ በሙምባይ ፖሊስ ውስጥ ታዋቂ የሆነ የወንጀል ምርመራ ቡድን ተባባሪ ኢንስክፔተር ነው።

ሳቪን ዌዝ በቦታው የደረሰው የአካባቢው ፖሊስና ኃላፊዎች ከደረሱ ከሦስት ወይም ከአራት ሰዓታት በኋላ ነው ተብሏል።

መጋቢት 4/2013 ዓ.ም የፌደራል መርማሪዎች ተባባሪ ኢንስፔክተሩን ለ12 ሰዓታት ያህል ከጠየቁት በኋላ በቁጥጥር ስር አዋሉት።

የፎቶው ባለመብት, PTI

የምስሉ መግለጫ,

ሳቺን ዌዝ

ተባባሪ ኢንስፔክተሩ በቁጥጥር ስር በዋለበት በነገታው ጠፋች የተባለችው ቶዮታ መኪና በሙምባይ ፖሊስ የወንጀል ዘርፍ ጋራዥ ውስጥ ተገኘች።

መርማሪዎች እንደሚሉት ተባባሪ ኢንስፔክተሩ ከቱጃሩ ቤት ተቀጣጣይ ቦምቦችን የያዘችውን መኪና ካቆሙ ሰዎች መካከል አንዱ ነው ይላሉ። የፖሊስ ኃላፊዎች ግን ይህንን ውንጀላ ነው በማለት አይቀበሉትም።

ነገር ግን የፀረ-ሽብር ዘርፉ ኢንስፔክተሩን በሴራና ተቀጣጣይ ቦንቦቹን በተመለከተ የሰሩት ምርመራ ቸልተኝነት የተሞላ መሆኑንና ማስፈራሪያዎች የነበሩበት ነው በሚል ከሶታል። ፍርድ ቤቱም ሳቺን ዌዝ የጠየቀውን የዋስትና መብት ከልክሎታል።

ከዚሁ ጋር በተገናኘ የሂረን ባለቤት ለጋዜጠኞች እንደተናገረችው ተባባሪ ኢንስፔክተሩና ባለቤቷ በቅርበት ይተዋወቁ እንደነበር ነው። ስኮርፒዮ የተባለው መኪናም ለሁለት ዓመታት ያህል አብረው ይጠቀሙ እንደነበር ነው። በርካታ ጊዜያትም ይገናኙ እንደነበርም ተናግራለች።

ሳቺን ዌዝ በበኩሉ ሂረንን እንደማያውቀውና ስለ ሞቱም ምንም እንደማያውቅ ተናግሯል።

ሳቺን ዝ ማን ነው?

ሳቺን ዌዝ የፖሊስን ኃይል የተቀላቀለው በአውሮፓውያኑ 1990 ነው።

በሙምምባይ 'ኢንካውንተር ስፔሻሊስት' የሚባሉና በከተሞች ያሉ ወንጀሎችን ማፅዳት በሚል ያነጣጠረ ቡድን አባል ሆኖ ሰርቷል።

ይህ ቡድን በወንጀለኞችና በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ዘንድ አወዛጋቢ ስም ነበረው። አንዳንድ ጊዜም በሕግ የማይመሩና ከወንጀለኞች ጋር የሚተባበሩ እየተባሉም ይከሰሳሉ።

በአውሮፓውያኑ 2004 ሳቺን ዌዝ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እያለ ህይወቱ ካለፈው የ27 ዓመቱ የሶፍት ዌር መሃንዲስ ጋር ተያይዞ ከሥራ ታገደ።

ክዋጃ ዩኑስ የተባለውን መሃንዲስ በቁጥጥር ስር ያዋሉት ሳቺን ዌዝና የሥራ ባልደቦቹ ሲሆኑ ይህም ከተማዋ ውስጥ ከነበረ የቦንብ ፍንዳታ ጋር ተያይዞ ነው። ሳቺን ከመሃንዲሱ ሞት ጋር በተያያዘ እጄ የለም ሲል ክዷል።

በአውሮፓውያኑ 2007 ከፖሊስ ኃላፊነቱ እለቃለሁ ቢልም ተቀባይነት አላገኘም። ወዲያው በቀጣዩ ዓመት በእግድ ላይ የነበረው ሳቺን ሺቭ ሴና የተባለ የቀኝ ክንፍ አክራሪ ፓርቲን ተቀላቀለ።

ፓርቲው መዲናዋ የሙምባይ በምትገኝበት ማሃራሽትራ ግዛት የጥምር መንግሥት ከመሰረቱት መካከል አንዱ ነው። የፓርቲው አመራሮች ኢንስፔክተሩ የፖለቲካ ህይወቱ እምብዛም ነው ይላሉ።

ባለፈው ዓመት ሰኔ እግዱ ተነስቶለት የወንጀል መርማሪ ቡድኑንም እንዲቀላለቀል ተደረገ። የፖሊስ ኃላፊዎች በኮቪድ-19 መመሪያዎች ምክንያት ባጋጠመ የፖሊስ እጥረት ምክንያት ወደ ሥራ እንደተመለሰ ይናገራሉ። ተችዎች በበኩላቸው የታገደ ፖሊስን የመለሱበት ምክንያት ፖለቲካዊ ነው ይላሉ።

ባለፈው ሳምንት የሙምባይ ፖሊስ ተባባሪ ኢንስፔክተሩን ለሁለተኛ ጊዜ አግዶታል። ጠበቆቹ ደንበኛችን ከውንጀላው ነፃ ነው እያሉ ይከራከራሉ።

ያልተመለሱ ጥያቄዎች ምንድን ናቸው?

በርካታ ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሉ፤ ለምሳሌም ያህል፦

  • በቱጃሩ ቤት ተቀጣጣይ የተሞላበት መኪና ማቆም ለምን አስፈለገ? ከጀርባው ያለው መልዕክት ምንድን ነው?
  • በኋላ በፖሊስ ጋራዥ የተገኘው መኪናስ ለምን ይህንን መኪና ሲከተለው ነበር?
  • ሁለቱን መኪኖች እየነዱ የነበሩት እነማን ናቸው?
  • ቦምብ የተገኘባት መኪና እውነት የሰረቀ ነው?
  • ሂረንን ማን ገደለው? ለምን?