አብደላ ሸሪፍ፡ በዩኔስኮ በቅርስነት በተመዘገበችው ከተማ በሐረር የግል ሙዚየም ያቋቋሙት ግለሰብ

የክብር ዶ/ር አብደላ አሊ ሸሪፍ

የፎቶው ባለመብት, Harari Communucation

መጋቢት 04/2013 ዓ,ም ሐረማያ ዩኒቨርስቲ ለሁለት ሰዎች የክብር ዶክተሬት ሰጥቶ ነበር። አንደኛው አቶ አብደላ ሸሪፍ ሲሆኑ ሌላኛው ደግሞ የቀድሞው ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን አቶ አባዱላ ገመዳ ናቸው።

የዛሬ ጉዳያችን ታድያ አቶ አብደላ ሸሪፍ ናቸው። የክብር ዶ/ር አብደላ አሊ ሸሪፍ ሙሉ ስማቸው አቶ አብዱላሂ አሊ ሸሪፍ እንደሚባል ነግረውናል። በአብዛኛው የሚታወቁት ግን አብደላ ሸሪፍ በመባል ነው።

ተወልደው ያደጉባት፣ ክፉ ደግ አይተው አግብተው የወለዱባት፣ ታሪኳንና ባህሏን የሚሰንዱላት ሐረር መኖሪያቸውም ጭምር ናት።

የሐረር ከተማ፣ በ2006 ዓ.ም በዩኔስኮ ቅርስነት ተመዝግባለች።

የ69 ዓመት አዛውንት የሆኑት እኚህ ግለሰብ፣ የግላቸውን ቅርሳ ቅርስ የሚሰበስቡበት ማዕከል በታሪካዊቷ ሐረር ከተማ አላቸው።

ይህንን ሥራ ለመጀመር ምክንያት የሆናቸው ከልጅነታቸው ጀምሮ አብሯቸው ያደገው "ራስን የመፈለግ ዝንባሌ" ነው ይላሉ።

በተለይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሚከታተሉበት ወቅት ስለ ቤተሰባቸው ታሪክ መጠየቅ መጀመራቸውን የሚያስታውሱት አቶ አብደላ "ታሪክ አዋቂ የሆኑ የአገር ሽማግሌዎችን መጠየቅሁ" ይላሉ።

በወቅቱ ታዲያ ለአቶ አብደላ ጥያቄ መልስ ለመስጠት የተሰየሙት የአገር ሽማግሌዎች "ታሪክ ድሮ ነበረን አሁን ግን የለንም" ስላሏቸው ያለፈውን ታሪካቸውን ያለማወቅ ችግር ገጠማቸው።

ከዚህ በኋላም የራሳቸውንና የማኅበረሰባቸው ታሪክ ለማወቅ ፍለጋ ጀመሩ። አቶ አብዱላሂ፣ በወቅቱ ለተፈጠረባቸው የማንነት ጥያቄ ምላሽ ለማግኘት ባህላቸውን የሚያንፀባርቅ ቅርስ ለማሰባሰብ ቆርጠው ተነሱ።

ከልጅነታቸው ጀምሮ ቅርስን የመጠበቅና የመንከባከብ ዝንባሌ የነበራቸው አብደላ አሊ ሸሪፍ፣ ህልማቸውን ለማሳካት ቀደምት የሐረሪ ሙዚቃዎችንና ጥንታዊ የእጅ ፅሁፎችን በማሰባሰብ ሥራቸውን 'ሀ' ብለው ጀመሩ።

በዚህም ታሪክን መመርመር ማጥናት ጀምረው ከ1982 ዓ.ም ጀምሮ መጻህፍትን የሐረሪ ዘፈኖችን፣ ጥናታዊ ጽሑፎችን፣ አልባሳትን እና የተለያዩ ባህላዊ እቃዎችን መሰብሰብ ጀመሩ።

በዚህም ሂደት ወቅት በምሥራቅ ኢትዮጵያ የሚገኙትን የኦሮሞን፣ የሐረሪን፣ የሶማሌ፣ የአፋርን እና የአርጎባን ባሕሎች የሚያስተዋውቁ ቅርሶችን እንደሰበሰቡ ይናገራሉ።

የሰበሰቧቸው እነዚህ የአገሪቱን የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን ባህልና ታሪክን የሚያሳዩ እቃዎችን ከቤተሰባቸው ጋር ለ17 ዓመታት ቤታቸው ውስጥ መቆየቱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በርካታ መጠን ያላቸውን እነዚህን እቃዎች በቤታቸው ውስጥ በጠባብ ስፍራ ለረጅም ጊዜ በማስቀመጣቸው የተነሳ "ለአስም በሽታ ልጋለጥ ችያለሁ" ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Isihaaq Shaafi

'ሸሪፍ ሙዚየም''

ከዓመታት ጥረት በኋላም በ1991 ዓ.ም ''ሸሪፍ ሙዚየም'' በማለት በኢትዮጵያ ብቸኛውን "የግል ሙዝየም" ለመመስረት በቁ። ይህ የቅርስ ማዕከል አቶ አብደላ ባህላዊ እቃዎችን መሰብሰብ ከጀመሩ ከ17 ዓመት በኋላ የተቋቋመ ነው።

ሙዚየሙ በሐረር ከተማ መኪና ግርግር በሚባለው ስፍራ ላይ ይገኛል። ሙዚየሙ የሚገኝበት ቤት እራሱ ከ110 ዓመት በፊት የተሰራ በመሆኑ ታሪካዊ እንደሆነ ይናገራሉ።

በ1999 ዓ.ም የሐረሪ ክልል መስተዳደርም የአቶ አብደላ ሸሪፍን ጥረት ለመደገፍ፣ የተፈሪ መኮንን ጫጉላ ቤት የሚባለውና የ21 አባወራዎች መኖሪያ ሆኖ የቆየውን ታሪካዊ ቤት ለሙዚየምነት እንዲውል በመስጠት ከፍተኛ ድጋፍ እንዳደረገላቸው ገልጸዋል።

ይህ ቤት ራስ መኮንን ልጅ የነበሩት ተፈሪ መኮንን በኋላ ላይ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የነበሩት አጼ ኃይለሥላሴ የሐረር አስተዳዳሪ በነበሩት ጊዜ በ1903 ዓ.ም የተሰራ እንደነበር አቶ አብደላ ይናገራሉ።

እንዲህ አይነት የባህል እና የታሪክ ቅርሶችን በአንድ ስፍራ ሸክፎ ያዘ ሙዚየም ወይንም የግል የቅርስ ማዕከል በግል ማደራጀት በኢትዮጵያ የተለመደ አይደለም።

አቶ አብደላ ግን በዘርፉ በግል የተሰማራ እንደሌለ ሲተቅሱ ከኢትዮጵያ አልፈው የአካባቢውን አገራትን ይጠቅሳሉ። "በግል እኔ ብቻ ነኝ ያለኝ። በምሥራቅ አፍሪካም እኔ ብቻ ነኝ ያለሁት" ይላሉ።

በእርግጥ በምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ ካሉ በርካታ አገራት ውስጥ እርሳቸው ብቸኛ ስለመሆናቸው ማረጋገጥ ባይቻልም፣ በግል ተነሳሽነት ይህንን የሚያክል ሙዚየም ማደራጀት ቀላል እንዳልሆነ መረዳት ይቻላል።

በሙዚየሙ ውስጥ የሚገኙ ቅርሶች እንዴት እንደሰበሰቡ ሲናገሩ፤ የተወሰኑትን ሰዎች በስጦታ እያመጡላቸው፣ የተወሰኑትን ደግሞ በራሳቸው ገንዘብ በመግዛት እንደዚሁም ደግሞ ለሰዎች በአደራ በማስቀመጥ መሆኑን መሆኑን ይናገራሉ።

እንደዚህም ሆኖ ጥንታዊ እቃዎችን መሰብሰብ ቀላል አለመሆኑን አቶ አብዱላሂ ሸሪፍ ለቢቢሲ ይናገራሉ።

"መጀመሪያ ሰዎች አያምኑኝም ነበር። ምክንያቱም ይሸጠዋል ብለው ስለሚያስቡ ነበር። መሰብሰብ ጀምሬ ሰው መጥቶ ማየት ከጀመረ በኋላ ግን እምነት እያገኘሁ መጣሁ" ይላሉ።

የበዚህም ሳቢያ በሕዝቡ ዘንድ በተፈጠረው መተማመን ጥንታዊ መጽሐፍት በሙዝየማቸው ውስጥ ለመገኘት እንዲገኝ ምክንያት እንደሆነ ይናገራሉ።

"ከሰበሰብኳቸው ታሪካዊና ባህላዊ እቃዎች መካከል 60 በመቶ ያህሉ ሕዝቡ ነው የሰጠኝ" በማለት የተለያዩ ሰዎች ቅርሶቹን እንደሚያመጡላቸውም ይገልጻሉ።

"ቅርሶቹን የማሰባስበው ለታሪክ እንጂ ለሽያጭ አይደለም" የሚሉት አቶ አብደላ፣ በሙዚየሙ የሚገኙት የተለያዩ ቅርሳ ቅርሶች "የሕዝብ ታሪክ ነው፤ ለመሸጥ እና ነጋዴ መሆን አይደለም የሰበሰብኳቸው። ታሪክን ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ እንጂ እኔ ለመሸጥ አልገዛሁም አንድም አልሸጥኩም።"

የፎቶው ባለመብት, John Elk

በሙዚየሙ ውስጥ ምን ምን አለ?

እንደ አቶ አብደላ አገላለጽ ሙዚየሙ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን ጌጣጌጦችን በሚያሳዩ ቅርሶች የተሞላ ነው። በዚህ ማዕከል ውስጥ የሐረሪና የአክሱም እንደዚሁም ከ120 አገራት በላይ ገንዘቦች ይገኛሉ።

በአብዛኛው በእጅ የተጻፉ ቅዱስ ቁርዓንን ጨምሮ ከ1000 ዓመት በላይ እድሜ ያላቸው የአረብኛና በተለያዩ ቋንቋዎች የተጻፉ መጻህፍት በሙዚየሙ ውስጥ በአግባቡ ተደራጅተው እንደሚገኙ ይናገራሉ።

አቶ አብደላ አሊ ሸሪፍ እንደሚሉት በዚህ የግል ሙዝየማቸው ውስጥ ከ13 ሺህ በላይ ውድና እድሜ ጠገብ የአገር ሀብት የሆኑ ቅርሶችን በማሰባሰብና በመጠበቅ ለትውልድ ለማቆየት ችለዋል።

"13 ሺህ በላይ የሚሆኑ ቅርሱች ይገኛሉ፤ አልባሳት፣ የጦር እቃዎች፣ ጎራዴ፣ ማህተሞች፣ የጌጣ ጌጥ እቃዎች ሁሉ በስብስቡ ውስጥ አሉ።"

በዚህ የግል ሙዚየም ቅርሶችን ከመሰብሰብ ባለፈም ቅርሶችን የመመዝገብና የመንከባከብ እንዲሁም የተጎዱ ቅርሶች የመጠገንና የማደስ ሥራዎችም እንደሚከናወኑ ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈም ከተለያዩ ዓለማት ለሚመጡ የውጭ አገር ጎብኚዎች እንዲሁም በተለያየ ደረጃ ለሚገኝ ኢትዮጵያዊያንም ሙዚየማቸውን በማስጎብኘት ታሪክን እና ማንነትን እንዲያውቁ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ እንደሆነ ያምናሉ።

አቶ አብዱላሂ ሸሪፍ ቀደም ሲል ይህንን ሙዚየም ለመጎብኘት ከሚመጡ ቱሪስቶች "በወር ከ25 ሺህ እስከ 30 ሺህ ብር ድረስ" እናገኝ ነበር ብለዋል።

አሁን ግን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በመላው ዓለም በመከሰቱ ምክንያት የጎብኚዎች ቁጥር ቀንሶ "እየከሰርን ነው ያለነው" ይላሉ።

የክልሉ መንግሥት ቀድሞ የተፈሪ መኮንን ቤተ መንግሥት የነበረውን ቤት ለቅርስ ማዕከልነት እንዲውል በማለት ለአቶ አብደላ ከመስጠት ባሻገር ሙዚየሙን የጥበቃ ሠራተኞች ደሞዝ በመክፈል ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ተናግረዋል።

በተጨማሪም በተለያዩ ጊዜያት ከኤምባሲ እና ከተለያዩ ድርጅቶች እንዲሁም ከሼህ አላሙዲን ጭምር ለሙዚየሙ ማጠናከሪያ ድጋፍ አግኝተዋል።

አቶ አብደላ ሸሪፍ ለሥራቸው የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ማግኘት የቻሉ ሲሆን በአገር ወስጥም የዓመቱ የበጎ ሰው ሽልማትን ጨምሮ በርካታ እውቅናዎችን አግኝተዋል።

መጋቢት 04/2013 ዓ.ም ደግሞ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ "የአገራችንን ጥንታዊና ዘመናዊ ስልጣኔዎችን በዓለም ሕዝቦች እንዲታወቁ የላቀ አስተዋፅኦ አበርክተዋል" በማለት የክብር ዶክትሬት አበርክቶላቸዋል።