ፓኪስታን በልጆቿ ፊት እናቲቱን የደፈሩ ሁለት ወንዶች ላይ የሞት ፍርድ በየነች

የፓኪስታን አደባባይ ተቃውሞ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የፓኪስታኑ ፍርድ ቤት በመድፈር ወንጀል ሁለት ወንዶች ላይ በሞት እንዲቀጡ በይኗል።

አቢድ ማልሂና ሻፍቃት አሊ ባጋ የተባሉት ግለሰቦች ሴትዮዋን የደፈሯት ከሁለት ልጆቿ ፊት ነው ተብሏል።

ሁኔታው በበርካታ ፓኪስታናውያን ዘንድ ከፍተኛ ቁጣንም ቀስቅሷል።

ስሟ ይፋ ያልሆነው ይህች ግለሰብና ልጆቿ መኪናቸው ነዳጅ አልቆበት መንገድ ላይ በነበሩበት ወቅት ሁለቱ ወንዶች መኪናውን ሰብረው ገብተው ዘርፈዋቸዋል እንዲሁም ልጆቿ ፊት ሴትዮዋን ደፍረዋታል።

ክስተቱ የተፈፀመው መስከረም ላይ ሲሆን በ30ዎቹ እድሜ ላይ የምትገኘው ይህች ሴት ዘመድ ጋር ደውላ የመኪናዋ ነዳጅ ማለቁንና መንገድ ላይ መቆሟን ተናግራ ነበር።

የተደወለለትም ዘመድ ለድንገተኛ የመኪና አገልግሎት እንዲመጣላት እያስተባበረ ነበር ተብሏል።

በዚህ ወቅት ነው ሁለቱ ግለሰቦች ገብተው ያላትን ጌጣጌጥ ከዘረፉ በኋላ በአካባቢው ወደሚገኝ ሜዳ ከልጆቿ ጋር ወስደው በነሱ ፊት ከደፈሯት በኋላ እንዳመለጡም ከፍርድ ቤቱ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

ይህ ሁኔታ ለፖሊስ ሪፖርት በተደረገበት ወቅት "ፖሊስ ብቻሽን እስከዚህ ሰዓት ለምን አመሸሽ?" የሚል ምላሽ መስጠቱ ቁጣን ቀስቅሷል።

በተለይም ላሆሬ የተባለችው ግዛት ከፍተኛ የፖሊስ ኃላፊ የሆኑት ኡመር ሼክ በሚዲያ ላይ ቀርበው በተወሰ መልኩ የሷ ጥፋት መሆኑን መናገራቸው በብዙዎች ዘንድ ከፍተኛ ውግዘትን እንዲያስተናግዱ ሆነዋል።

"ለምን ጭር ያለ መንገድ መረጠች፣ ከልጆቿ ጋር በዚያ በምሽት ብቻዋን ምን ትሰራለች፣ ከመውጣቷ በፊት መኪናዋ ነዳጅ መኖሩ አለመኖሩን ለምን አላረጋገጠችም" በማለት የተደፈረችውን ሴት ጥፋተኛ ሊያደርጉ ሞክረዋል ተብሏል የፖሊስ ኃላፊው።

የፖሊስ ኃላፊው ከዚህም በተጨማሪ ነዋሪነቷ ፈረንሳይ የሆነችው ይህችን ፓኪስታናዊ ሴት ፓኪስታን እንደ ፈረንሳይ ደህንነቷ የተጠበቀ መስሏት ይሆናል ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ይህም ሁኔታ በአገሪቷ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል።

"የጥቃት ሰለባዋን ጥፋተኛ እንዴት ያደርጋሉ?" ተብለውም ተዘልፈዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ የፓኪስታን ዜጎች የተሻለ ፍትህና አገሪቷ የሴቶችን ደህንነት ለመጠበቅ መስራት አለባት በሚል ወደ አደባባይ ተቃውሟቸውን ወስደውታል።

በትናንትናውም ዕለት ላሆሬ በምትባለው ግዛት የሚገኝ ልዩ ፍርድ ቤት ግለሰቦቹን በቡድን በመድፈር፣ ጠለፋ፣ ዝርፊያና በሌሎች ሽብር ወንጀሎች የሞት ፍርድ በይኖባቸዋል።

የአቢድ መሂልና የሻፍቃት አሊ ጠበቆች በበኩላቸው ይግባኝ እንደሚጠይቁ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።