ብሔራዊ ቡድኑን ወደ የአፍሪካ መድረክ ለመመለስ የሚመኘው ሽመልስ በቀለ

ሽመልስ በቀለ

የፎቶው ባለመብት, Shemeles Bekele

ትውልድ እና እድገቱ አዋሳ ከተማ ኮረም ሰፈር ነው።

እንደ አብዛኛው የኢትዮጵያ ልጆች ኳስ እና ሽመልስ በቀለን ያስተዋዋቃቸው ትምህርት ቤት ነው። በእረፍት ጊዜ ባለችው ትንሽ ክፍተት ኳስን መጫወት የጀመረው ሽመልስ ወደ ሰፈሩ ሲመለስም ከሰፈር ጓደኞቹ ጋር ከማታ ጥናት በፊት ያለችውን የ አንድ ሰዓት ክፍተት ኳስ በመጫወት ያሳልፋ ነበር።

ዛሬ ላይ በግብጽ ፕሪሚየር ሊግ ተወዳዳሪ ለሆነው ሚሰረ ሌል ማካሳ እየተጫወተ ይገኛል።

ዛሬ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ለማለፍ ከማደጋስካር አቻዋ ለምታደርገው ጨዋታ ቁልፍ ሚና ከሚኖራቸው መካከል አንዱ የሆነው እግር ኳሰኛው ሽመልስ በቀለ ስለ 'ፕሮፌሽናል' የእግር ኳስ ሕይወቱ ለቢቢሲ የሚከተለውን አጋርቷል።

ግብፅ ሊግ የመጫወት እድል

ግብፅ ሄጄ የመጫወት እድል የተፈጠረልኝ፤ በቅድሚያ ሊቢያ እና ሱዳን ሄጄ የነበረኝ አጭር ቆይታ ብሎም በኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩኝ እንቅስቃሴዎች ናቸው። በሱዳን ለስድስት ወር ያክል ተጫውቼ ነበር። ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ለ ሁለት ወር ያክል ዝግጅት ላይ እያለሁ አሁን ያለው ወኪሌ ቪዲዮዎችን እንድልክለት ይጠይቀኝ ነበር።

እኔም በውጪ የነበረኝን እና በአገር ውስጥ የነበሩኝን ቆይታ የሚያሳዩ ምስሎች ላኩለት። በተጨማሪም አጭር ግዜ ቢሆንም ወጥቼ የመጫወት ሪከርድ ስላለኝ አሱ ያገዘኝ ይመስለኛል። ፔትሮጅክት የሚባል ክለብ ቪዲዮዎቹን ተመልክቶ ነበር።

አሰልጣኞቹ ደስተኛ ነበሩ። በተለይ ምክትል አሰልጣኙ የበለጠ በእኔ ደስተኛ ነበር። ከቪዲዮ በተሸለ በአካል መጥተው ለማየት ተነጋገሩ እኔም ደስተኛ ነበርኩ። አዲስ አበባ ላይ ከአልጄሪያ ጋር በነበረን ጨዋታ መጥተው ተመለከቱኝ፤ ምንም እንኳን ሁለት ለአንድ ብንሸነፍም በእንቅስቃሴዬ ደስተኛ ስለነበሩ ለክለቡ ለመፈረም እድሉን አገኘሁ ማለት ነው።

በፕሮፌሽናል የኳስ ህይወትህ ወርቃማ የምትለው ጊዜ የቱ ነው?

በፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ህይወቴ ወርቃማ ብዬ የማስበው ከሁለት አመታት በፊት ፔትሮጄት የነበርኩበት ነው። ይህም በእግር ኳስ ህይወቴ አምበል ሆኜ ቡድን መርቼ አላውቅም ነበር። በወቅቱ አምበል ሁኜ ነበር። ይህ ከአገር ወጥቼ ለመጀመሪያ ክለቤ ፔትሮጄት መሪ መሆኔ ለእኔ ትልቅ ነገር ነው።

የብሔራዊ ቡድኑን አቋም እንዴት አገኘኸው?

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አቋም ከዓመት ዓመት ልዩነት አለው። እኔ በሄድኩበት ግዜ በተለይ በመጨረሻው ዓመት በፕሪሚየር ሊጉ 18 ጠንካራ ክለቦች ነበሩ። በዚህ ዓመት እንደሚታወቀው 13 ክለቦች ነው ያሉት። ይሄ በራሱ በብሔራዊ ቡድኑ አቋም ላይ የራሱ ጫና አለው። ነገር ግን አሁን ላይ ሊጋችን በቀጥታ ለዓለም መታየቱ [በዲኤስቲቪ አማካኝነት] ደግሞ የራሱ የሆነ በጎ ነገር ያመጣል ብዬ አስባለሁ።

እግር ኳስና ኮሮናቫይረስ እንዴት እየሄዱ ነው?

ኮሮናቫይረስ ከመጣ በኋላ ፊፋ ባወጣው ሕግ መሰረት ሁል ጊዜ ጨዋታ ሲኖረን ከሁለት ቀን በፊት ምርመራ እናደርጋለን። ኮሮናቫይረስ ያለበት ሰው አይጫወትም። ይሄ በኢትዮጵያም ተመሳሳይ ነው።

ለአፍሪካ ዋንጫ እየተዘጋጃችሁ ነው። ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ዋንጫ ካለፈች ዘጠኝ መት አለፈ። አሁን ያለው ቡድን የሚያልፍ ይመስልሃል?

አዎ ለአፍሪካ ዋንጫ እናልፋለን ብዬ አምናለሁ። ባፈው ሳምንት ከማላዊ ጋር ያካሄድነው የወዳጅነት ጨዋታ በብቃት ነው የተወጣነው። ጎበዝ ተጫዋቾች ከተለያዩ ክለቦች ወደ ብሔራዊ ቡድኑ ተጠርተዋል። ሁሉም ተጫዋች ጥሩ አቋም ላይ ነው ያለው።

ያለፈውን ሳምንት ጨዋታ በብቃት እንደጨረስነው ሁሉ ከማዳጋስካር ጋር የምናደርገውን ጨዋታም በድል እንወጣዋለን። ለዚህም ምክንያቱ አሪፍ ተጫዋቾች እና አሪፍ አሰልጣኞች ስላሉን ነው። ስለዚህ እነዚህን በድል ከቋጨን ወደ አፍሪካ ዋንጫ የማናልፍበት ምን ምክንያት አለ?

የፎቶው ባለመብት, SIMON MAINA

የምስሉ መግለጫ,

እአአ 2013 ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከናይጄሪያ አቻው ጋር በአዲስ አበባ ስታዲየም በነበረው ጨዋታ ወቅት የናይጄሪያው ግብ ጠባቂ ቪንሰንት ኢኒያም እና ሽመልስ በቀለ

ያኔ አንተ የነበርክበት ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ሲያልፍ አገሪቱ የነበረው ስሜት እንዴት ታስታውሰዋለህ?

ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ምንም የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ተሳትፎ አላደረግንም። ይሄ በጣም ረጅም ጊዜ ነው። አሁን ግን ወደ 10ኛ ዓመት ከመግባታችን በፊት እኛ ቡድኑን አሳልፈን ያኔ እኛ የነበረንን ስሜት ድጋሚ ለሁለተኛ እንዲሰማን እፈልጋለሁ።

የዚያን ጊዜ ለአፍሪካ ዋንጫ ካለፈው ቡድን ውስጥ አሁን ያለነው ሦስት ተጫዋቾች ብቻ ነን። እኛ ያለፍንበትን ስሜት አሁን ያሉት አዳዲስ ልጆች እንዲሰማቸው እንፈልጋለን። እሱ ጊዜ ሲነሳ በብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ ተፈጥሮ ያለፈው ከፍተኛ መነቃቃት እና ደስታ ይታወሰኛል። ያ ስሜት እንዲደገም እፈልጋለሁ።

ሕዝቡ ጋር የነበረው ስሜት ከባድ ነበር። ብዙ ነገሩን ትቶ ያኔ ኳስ ለመመለከት እና ለአገሩም የነበረው ትልቅ ስሜት ያንጸባርቅ ነበር። ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፋችን የፈጠረው ደስታ በጣም ትልቅ ነበር።

አገራችን አሁን ካለችበት ሁኔታ አንጻር ያ ስሜት እንደገና እንዲመጣ እንፈልጋለን። ከእግዚአብሔር ጋር ለአፍሪካ ዋንጫ የምናልፍ ከሆነ ሁሉንም ነገር የምናስረሳበት ጊዜ ይመጣል ብዬ አስባለሁ።

በፖለቲካ ምክንያት ሁሉም ቦታ ጭንቀት ነው የሚሰማው፤ ምንም ሰላም የለም። ሕዝቡ ሰላሙን እንዲያገኝ እና ያኔ የነበረው የደስታ ስሜት እንዲመጣ እፈልጋለሁ።

በብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ አዲስ እየመጡ ካሉ ጎበዝ ተጫዋቾች ውስ አንዱ አቡበከር ናስር ተደጋግሞ ስሙ ይነሳል። ከሱ ጋር ተጣምሮ መጫወት እንዴት አገኘኸው?

አቡበከር ናስር እና እኔ አሁን በብሔራዊ ቡድን ውስጥ አብረን የመጫወት እድል አግኝተናል። በእኔ አይን ባጭሩ ምርጡ ተጫዋች ነው። ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም። ጎበዝ ተጫዋች ነው።

ልጁ ገና 21 ዓመቱ ነው፤ ትልቅ ደረጃ መድረስ የሚችል ነው። ከዚህ በኋላ ራሱን አጠንክሮ እና ታግሶ የሚሰራ ከሆነ የሚያሳየው ብቃት ተስፋ ያሳድራል። ራሱን ወደ ላይ ሳያደርግ የሚጫወት ልጅ ነው። እያደርም እኔ ካለሁበት ደረጃ የበለጠ ትልቅ ቦታ ላይ መድረስ የሚችል ልጅ ነው።

የኳስ ተንታኞች የኢትዮጵያ ተጫዋቾች እድል አጥተው እንጂ የቴክኒክ ብቃት አላቸው ይላሉ። አንተ ከአገር ወጥተህ ስትጫወት ምን ታዘብክ?

አዎ በቴክኒክ በኩል ጥሩ ተጫዋቾች አሉን ከኳስ ጋር የተያያዙ ብዙ እድሎች ግን የሉም። ኢትዮጵያ ውስጥ በጣም ብዙ ተሰጥኦ ያላቸው አግር ኳስ የሚችሉ ምርጥ ልጆች አሉ።

ያሰልጣኝ ችግር፣ የቁሳቁስ ችግር እና የመሳሰሉት ነው ጎልተው እንዳይወጡ ያደረጋቸው። እነዚህ እድል ቢሰጣቸው የኢትዮጵያ ተጫዋቾች በጣም ስኬታማ መሆን እና ወደ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ መምጣት ይችላሉ።

ሰባት መት በግብጽ ስትኖር ሕዝቡን እንዴት አገኘኸው?

ብዙ ግብጻዊያን ጓደኞች አሉኝ። ከክለብ አጋሮቼ ባሻገርም በምኖርበትም አከባቢ ግብጻዊያን ጓደኞች አሉኝ። በደንብ እንነጋገራለን ጥሩ ጓደኝነት አለን። በኳስ ህይወቴ ላይም ምንም ያደረሰብኝ ጫናም የለም። ፖለቲካዊ ጉዳዮችን አንስተን ብዙም ተነጋግረን አናውቅም፤ ያው ግን ሁሉም ለአገሩ አይደለ፤ በተረፈ ግን አሪፍ ባህሪ አላቸው።

የፎቶው ባለመብት, Gallo Images

የምስሉ መግለጫ,

እአአ 2013 በአፍሪካ ዋንጫ መድረክ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከቡርኪና ፋሶ አቻው ጋር በተገናኘበት ወቅት።

በታዳጊነት እድሜህ ላይ ብትሆን እና አሁን ባለው እውቀትህ ላይ ሆነህ የእግር ኳስ አካዳሚ ብትገባ የትኛው ክህሎትህን ታሻሽል ነበር?

ያለኝን የኳስ ክህሎት ላይ በደንብ ብሰራ ደስ ይለኛል። ነገር ግን ዋናው የአካል ብቃት ጥንካሬ ላይ በጣም አተኩሬ የምሰራ ይመስለኛል። ምክኒያቱም አንድ ሰው ምንም ያህል የቴክኒክ ብቃት ቢኖረው ጥንካሬው ዝቅተኛ ከሆነ መቋቋም ይከብዳል። ምን አልባት ተመልሼ በልጅነት አካዳሚ ብገባ የአካል ጥንካሬዬ ላይ በጣም የምሰራ ይመስለኛል።

ብዙ ግዜ የኢትዮጵያ ተጫዋቾች ከአገር ሲወጡ ሳይሳካላቸው በቶሎ ይመለሳሉ። ምክያቱ ምድነው?

የሥነ ልቦና ጉዳይ በእግር ኳስ ህይወት ላይ ከባድ ችግር ነው። ሌላው ከአገር ቤት ይዘን የምንሄደው ብቃትን እዚያ ሄደን ከፍ ማድረግ ያስፈለጋል። እንደዛ ካልሆነ ብቃት ይወርዳል፤ ያኔ ተፈላጊነት ይቀንሳል። ብዙ ትንንሽ የሚመስሉ ከፍተኛ ጫና የሚፈጥሩ ፈተናዎች አሉ።

ለምሳሌ ተጫዋች ቤቱ ነው መመገብ ያለበት። እኔ ደግሞ ማብሰል አልችልም ነበር። ከፍተኛ ፈተና ሆኖብኝ ነበር። አገርም ይናፍቃል። እና እመለሳለሁ እያለ የሚጫወት ሰው ደግሞ ወዲያው ተመልሷል። ለሥራ እስከወጣን ድረስ ዋናው የሥነ ልቦና መጠንከር እና ትዕግስተኛ መሆን ለስኬት ቁልፍ ነው። በጣም ብዙ ችግሮች አሉ እነዚያን መቋቋም እና ዲሲፕሊንም ይጠይቃል።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በቴሌቪዝን መታየቱ የሚጨምረው ፋይዳ አለ?

አሁን ያለው ፕሪሚያር ሊግ በቀጥታ በቴሊቪዥን መቅረቡ ከፍተኛ የመታየት እድል መፍጠሩ አይቀርም። ቅድም እንዳልኩት ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የኳስ ተሰጥኦ ያላቸው ተጫዋቾች አሉ። ክለቦች ተጫዋቾቻው ወጥተው እንዲጫወቱ ማበረታታት አለባችው። ክለብ ብቻ ሳይሆን ፌዴሬሽኑ የራሱ ኃላፊነት አለበት።

ፌዴሬሽኑ ከመንግሥት ጋር ተባብሮ ትልቅ ነገር መስራት ይጠበቅበታል። ለምሳሌ ሌሎች አገራት ለተጫዋቾቻቸው ነፃ ቪዛ ስለሚያመቻቹ ሄደው ይሞክራሉ። ብዙ ግንኙነት ማድረግ እና ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር መነጋገር አለበት።

ባለሞያዎች እንደሚሉት አንድ ቡድን ከተገነባ ከ 4 እስከ 10 መት ዋና ቡድን ውስጥ ያሉ ሰዎች ሳይቀያየሩ በተመሳሳይ ብቃት መቀጠል ይችላል ይላሉ። ያኔ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈው ቡድን ወዲያውኑ ለምን ደከመ? ወይስ ያኔ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፋችሁት በአጋጣሚ ነበር?

ጠንካራ ክለብ ያለመኖሩ ነው ብሔራዊ ቡድኑን ያደከመው። ቡና እና ጊዮርጊስን ጨምሮ ብዙ ጠንካራ የክልል ክለቦች ነበሩ። አሪፍ ብሔራዊ ቡድን የተሰራው በዕድል ሳይሆን በጥንካሬ ነው።

ተጫዋቾችም በትንሽ ነገር እንሸወዳለን። ትንሽ ድል ያታልለናል። በዚያ ውስጥ እንጠፋለን። ተጫዋቾች ትንሽ ድል ስናገኝ ብዙ ነገር የሰራን ይመስለናል። የዓለም ዋንጫን ደጋግመው የወሰዱት እንደ ጀርመን እና ብራዚል እንኳን በዚያው ነው ጠንክረው የሚቀጥሉት።