የቴስላ መኪኖች ቻይናን ለመሰለል ውለዋል መባሉን ኤለን መስክ አስተባበለ

ኤለን መስክ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የአሜሪካ ኤሌክትሪክ መኪና አምራች የሆነው ቴስላ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኤለን መስክ መኪናዎቻቸው ቻይናን ለመሰለል ጥቅም ላይ ውሎ ከሆነ ድርጅታቸው "ይዘጋል" ብለዋል፡፡

ዋና ስራ አስፈፃሚው ምላሹን የሰጡት የቻይና ጦር የቴስላ መኪናዎችን ላለመጠቀም አግዷል ተብሎ መዘገቡን ተከትሎ ነው፡፡

የጦር ኃይሉ በመኪኖቹ ላይ የተገጠሙት ካሜራዎች በሚሰበስቡትን መረጃዎች ዙሪያ የደህንነት ስጋቶችን አንስቶ ነበር፡፡

ቻይና በጎርጎሮሳዊያዩ 2020 ከድርጅቱ ዓለም አቀፍ ሽያጭ አንድ አራተኛውን በመያዝ ከአሜሪካ ቀጥላ ትልቋ የደርጅቱ ገበያ ናት፡፡

ቅዳሜ መስክ አንድ ድርጀት በባዕድ መንግሥት ላይ ቢሰልል "ለዚያ ኩባንያ የሚያስከትላቸው አሉታዊ ውጤቶች እጅግ የከፉ ይሆናሉ" ብለዋል፡፡

መስክ ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪ በሆነ የቻይና የንግድ መድረክ እንደተናገሩት "መረጃዎችን በሚስጥር እንድንይዝ ጠንካራ ማበረታቻ አለ። ቴስላ በቻይና ወይም በየትኛውም ቦታ መኪናዎቹን ለመሰለል የሚጠቀም ከሆነ ድርጅታችን ይዘጋል" ብለዋል።

በቻይናም ሆነ በአሜሪካ የሚሠሩ ትልልቅ የአገራቱ ኩባንያዎች ከረዥም ጊዜ መካረሮች ይታያሉ ተብሏል።

ሁለቱ ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለኃብቶች በሆኑት በቻይና እና በአሜሪካ መካከል ያሉ ግንኙነት ለዓመታት ውጥረት ነግሶበታል፡፡

በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ በቻይና መንግስት እና በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር መካከል ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገው ከፍተኛ ውይይት የሁለቱም አገራት ባለሥልጣናት ቁጣ ያዘሉ ቃላትን ተወራውረዋል።

መስክ በቻይና እና በአሜሪካ መካከል የበለጠ መተማመንን እንዲሰፍን አሳስበዋል፡፡

በቻይና በባለቤትነት የተያዘውን ቲክቶክን ጉዳይ በመጥቀስ ሚስጥራዊ መረጃዎችን ድርጅቶቹ ካሉበት መንግስታት ጋር የሚጋሩ ኩባንያዎች ላይ ያለውን ስጋት ቀለል አድርገው አልፈዋል፡፡

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተጠቃሚዎች መረጃ ለቻይና መንግስት ሊሰጥ ይችላል በሚል ስጋት ቲክቶክን አሜሪካ ውስጥ እንደሚያግዱት አስፈራርተው ነበር፡፡

መስክ "የስለላ ሥራ ቢኖርስ ሌላኛው ሃገር ምን ይማራል እና በእውነቱስ አስፈላጊ ነው?" ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ቻይና በዓለም ትልቋ የመኪና ገበያ ናት። መንግስትም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በከፍተኛ ደረጃ ሲያስተዋውቅ ቆይቷል፡፡ ይህ ፍላጎት ቴስላ በ 2020፣ 721 ሚሊዮን ዶላር ትርፍ እንዲያገኝ አግዞታል፡፡