በኡጋንዳ ሳይመረዙ አልቀረም የተባሉ አንበሶች ሞተው ተገኙ

የተኛ አንበሳ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በኡጋንዳ ከሚገኙ ፓርኮች በአንዱ ሳይመረዙ አልቀረም በሚል የተጠረጠሩ ስድስት አንበሶች ሞተው አካላቸው ተቆራርጦ ተገኝቷል፡፡

አንበሶቹ በንግስት ኤልሳቤጥ ብሔራዊ ፓርክ ጭንቅላታቸውና መዳፎቻቸው ተቆርጠው አስከሬናቸውም በአሞራዎች ተከቦ ተገኝቷል ሲሉ ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡

የኡጋንዳ የዱር እንስሳት ባለስልጣን "ህገ-ወጥ የዱር እንስሳት ዝውውርን ከግድያው ጀርባ ሊሆን ይችላል" ብሏል፡፡

የጥበቃ ባለሙያዎች ከአከባቢው ፖሊሶች ጋር በቦታው በመገኘት ምርመራው ጀምረዋል፡፡

አንበሶቹ ዛፎችን በመውጣት ልዩ በሆነው ችሎታቸው ይታወቃሉ፡፡

የባለስልጣኑ የኮሙኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ በሽር ሃንጊ በሰጡት መግለጫ በግድያው "ማዘናቸውን" ተናግረዋል፡፡

የተፈጥሮ ቱሪዝም ለኡጋንዳ ኢኮኖሚ አስፈላጊ ሲሆን ለእንስሳት ጥበቃም ወሳኝ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡

"የኡጋንዳ የዱር እንስሳት ባለስልጣን የዱር እንስሳትን ህገ-ወጥ ግድያ አጥብቆ ያወግዛል። ምክንያቱም እንደ ሀገር በቱሪዝማችን ላይ አሉታዊ ተፅእኖን ስላለው ብቻ ሳይሆን አካባቢዎችን ለመጠበቅ እና የህብረተሰቡን ሥራ የሚደግፍ የገቢ ማስገኛ ጭምር ነው" ብለዋል፡፡

ከዚህ በፊት በንግስት ኤልሳቤጥ ብሔራዊ ፓርክ አንበሶች ተመርዘዋል ተብሎ የታመነባቸው በርካታ ክስተቶች ነበሩ፡፡

በ2018 ተመርዘዋል ተብለው የተጠረጠሩ ስምንት ደቦሎችን ጨምሮ 11 አንበሶች ሞተው ተገኝተዋል፡፡ ተመሳሳይ ክስተት በግንቦት 2010 ለአምስት አንበሶች ሞት ምክንያት ሆኗል፡፡