ኮሮናቫይረስ፡በሙምባይ በተጨናነቁ ስፍራዎች የኮቪድ-19 ምርመራ አስገዳጅ ሊሆን ነው

የኮሮና ቫይረስ ምርመራ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የህንዷ ግዛት ሙምባይ በተጨናነቁ ስፍራዎች ላይ የኮቪድ-19 ምርመራ አስገዳጅ እንዲሆን ወስናለች።

በኮሮናቫይረስ ክፉኛ ከተመቱት መካከል አንዷ የሆነችው ህንድ ይህንን አስገዳጅ መመሪያ ያወጣችው ወረርሽኙን ለመግታት እንደሆነም አስታውቃለች።

መገበያያ ማዕከላትና የባቡር ጣቢያዎችን ጨምሮ ህዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ላይ ፈጣንና አስገዳጅ ምርመራም ይደረጋል ተብሏል።

ምርመራውን አልቀበልም ያለ አካል ቅጣት እንደሚጠብቀው ተገልጿል። ቅጣቱ ግን ምን ሊሆን ይችላል የሚለውን ተጨማሪ መረጃ ከመስጠት ባለስልጣናቱ ተቆጥበዋል።

አስገዳጅ መመሪያ ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆንም ባለስልጣናቱ አስታውቀዋል።

የአካባቢው ኮሚሽነር ለኢንዲያ ቱደይ እንደተናገሩት ዜጎች ህዝብ ወደሚበዛባቸው አካባቢዎች ሲመጡ ለምርመራ ዝግጁ መሆን አለባቸው ብለዋል።

በገበያ መደብሮች ውስጥ ከተገኙ ግለሰቦች በስተቀር ለሌሎች ምርመራው በነፃ እንደሚሆንም ተገልጿል።

በሙምባይ የኮሮናቫይረስ ማዕከል በተባለችው በማሃራሽትራ ግዛትም በባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ2 ሺህ 982 አዲስ ህሙማን ተመዝግበዋል።

ህንድ በያዝነው ሳምንት ቅዳሜ ብቻ በአንድ ቀን ውስጥ 40 ሺህ 953 የኮሮናቫይረስ ህሙማን መዝግባለች።

በአራት ወራትም ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር የታየበት ነው ተብሏል።

በአጠቃላይ ወረርሽኙ ከተከተባት እለት ጀምሮ 159 ሺህ ዜጎቿን አጥታለች።

በአገሪቷ ውስጥ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 11.5 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን ቁጥሩም ለሳምንታት ያህል እያሻቀበ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።

ህንድ በአለም ላይ በኮሮናቫይረስ ሶስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን በሟቾች ቁጥር አራተኛ ላይ እንደሆነም መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ምንም እንኳን ቁጥሩ ጥር አካባቢ ላይ በተወሰነ መልኩ መቀነስ አሳይቶ የነበረ ቢሆንም በርካቶች መመሪያዎችን ችላ በማለታቸው በሳምንታት ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ ነው ተብሏል።

ህንድ ዜጎቿን የቫይረሱን መከላከያ ለመክተብና አደገኛ የሚባለውን የቫይረሱ አይነት ለመለየትም ስራ እየሰራች ነው።