የአውስትራሊያ አየር መንገድ ለመብረር የኮቪድ-19 ክትባት አስፈላጊ እንደሆነ አስታወቀ

የኳንታስ ዋና ስራ አስፈፃሚ

የአውስትራሊያ አየር መንገድ ኳንታስ ኃላፊ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ዓለም አቀፍ መንገደኞች እንዲከተቡ "የተለያዩ አገራት መንግሥታት ይጠይቃሉ" ሲሉ ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተጓዦቹ ቁጥር 75.6 በመቶ የቀነሱበትን ኢንዱስትሪ ለማነቃቃት የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባቶች ወሳኝ ናቸው ተብሏል፡፡

ዋና ሥራ አስፈፃሚው አለን ጆይስ እንዳሉት ብዙ መንግስታት ክትባትን "የመግቢያ ቅድመ ሁኔታ" ስለማድረግ እየተነጋገሩ ነው፡፡

ይህን ባያደርጉ እንኳ አየር መንገዱ የራሱን ፖሊሲ ማስፈፀም አለበት ብለው ያስባሉ፡፡

"በአውሮፕላኑ ውስጥ ያሉ ሰዎች ደህንነት የተጠበቀ መሆን አለበት። መንገደኞቻችን እና ሠራተኞቻችን የመንከባከብ ግዴታ አለብን" ብለዋል፡፡

ቲኬቶች የሚገዙበትን ውል እና ሁኔታ መለወጥ ትክክል ይሆናል ብለው ያምናሉ፡፡

ጆይስ መንገደኞች ለውጡን ለመቀበል ፈቃደኛ ይሆናሉ ብለው ያስባሉ፡፡ "አብዛኛዎቹ ደንበኞቻችን ይህ ጥሩ ሀሳብ ነው ብለው ያስባሉ። ጥናት ካደረግንባቸው ሰዎች 90 በመቶ የሚሆኑት ሰዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመብረር ክትባት መከተብ መስፈርት መሆን አለበት ብለው ያስባሉ" ብለዋል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅትን ጨምሮ አንዳንዶችም በሃሳቡ ካልተስማሙ መካከል ናቸው፡፡ የዲጂታል ሄልዝ እና ኢኖቬሽን ዳይሬክተር የሆኑት በርናርዶ ማሪያኖ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "የክትባት ፓስፖርት ለጉዞ መስፈርት መሆን አለበት የሚለውን አንቀበልም" ብለዋል፡፡

አክለውም የግሉ ዘርፍ ምንም ቢፈልግ እንዲህ ዓይነቱን ለውጥ ውጤታማ ለማድረግ ከመንግስታት ወጥ የሆነ አካሄድ ያስፈልጋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ወረርሽኙ አደጋን መቆጣጠር

አቪዬሽን ኢንዱስትሪው ለዓለም ኢኮኖሚ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማህበር ዘርፉ ለዓለም አቀፉ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ 1.8 ትሪሊዮን ዶላር እንደሚደግፍ ገምቷል፡፡

በጎርጎሮሳዊያኑ 2019 4.5 ቢሊዮን ሰዎችን ያመላለሰው ኢንዱስትሪ በኮሮናቫይረስን ስርጭት እና በመንግሥት ገደቦች ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የተሳፋሪዎች ቁጥር እንዲቀንስ ምክንያት ሆኗል፡፡

የአውስትራሊያ መንግሥት ድንበሮችን ለሁሉም የውጭ ዜጎች ዘግቷል። አልፎ አልፎም የሃገር ውስጥ ድንበሮችን ዘግታለች፡፡

እንደ ጆይስ ከሆነ ክትባቱ እያለም "አንዴ ዓለም አቀፍ ድንበራችንን ከከፈትን ቫይረሱ እየተዘዋወረ ይሄዳል፡፡"

የወረርሽኝ ኪሳራ

በተሳፋሪ እጥረት በ 2020 ያለፉት ስድስት ወራት ኳንታስ 800 ሚሊዮን ዶላር አጥቷል፡፡በ 2019 ተመሳሳይ ወቅት ከ 596 ሚሊዮን ዶላር ትርፍ አግኝቷል፡፡ በተጨማሪም 8,500 የሥራ ቅነሳዎች ተደርገዋል፡፡

በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም ደሞዛቸውን ከአውስትራሊያ መንግሥት እያገኙ ነው። ሌሎች ዓለም አቀፍ ኤር መንገዶችም ተመሳሳይ ዕጣ ገጥሟቸዋል።

በምላሹ አየር መንገዶች አቅማቸውን ቀንሰዋል። ብዛት ያላቸው አውሮፕላኖች ከሥራ ውጭ አድርገዋል፡፡ ኳንታስ ከ314 አውሮፕላኖቹ ውስጥ ሁለት ሦስተኛ ያህሉን ቀንሷል፡፡