አለም አቀፍ ታዳሚዎች የማይስተናገዱበት የቶኪዮው ኦሎምፒክስ

የቶክዮ ኦሎምፒክስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በተራዘመው የ2020 ቶኪዮ ኦሎምፒክስና ፓራልምፒክስ አለም አቀፍ ታዳሚዎች የማይስተናገዱበት እንዲሆን ተወስኗል።

ይህም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል።

የጃፓን ባለስልጣናት ለኦሎምፒክና ፓራልምፒክ ኮሚቴዎች እንዳሳወቁት አለም አቀፍ ታዳሚዎች ወደ አገር የሚገቡበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደማይችልም ጠቁመዋል።

አዘጋጆቹ በበኩላቸው ይኼ ውሳኔ ውድድሮቹን ለማየት ቲኬት ለገዙት ግልፅ ያለ መልክት እንደሚያስተላልፍና " በውድድሮቹ ላይ ለሚሳተፉትም ሆነ ለጃፓን ህዝብ ደህንነቱ የተጠበቀ" እንደሚያደርገው ተናግረዋል።

ሁሉም ውድድሮች በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በሀምሌ 23 ይጀመራሉ።

የፓራላምፒክስ ውድድሮች ደግሞ ከወር በኋላ በነሐሴ 24 እንደሚጀመሩም ተገልጿል።

የውድድሩ አዘጋጆች እንዳሉት ጃፓንን ጨምሮ በተለያዩ አገራት ውስጥ ያለው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት፣ አለም አቀፍ የጉዞ እግዶችና አዳዲስ የሆኑ የቫይረሱ ዝርያዎች መምጣት እዚህ ውሳኔ ላይ እንዳደረሳቸው ነው።

ቲኬቱን ቀድመው የገዙ ሰዎችም ገንዘባቸው እንደሚመለስላቸው አዘጋጆቹ አስታውቀዋል።

የኦሎምፒክስ ውድድሮች በባለፈው አመት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት እንዲራዘምና በዚህ አመትም እንዲደረግ ተወስኗል።

ኦሎምፒክስ እንዲራዘም ሲደረግ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ከ200 በላይ አገራት የሚሳተፉበትና 11 ሺህ አትሌቶችም የሚወዳደሩበት ነው።

የአለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቶ ቶማስ ባች እንዳሉት ይሄ ውሳኔ ለሁሉም ቢሆን ትልቅ መስዋዕት እንደሆነ ነው።

"በአለም ላይ የሚገኙ የኦሎምፒክ አድናቂዎችና ወዳጆች፣ የአትሌቶች ቤተሰቦችና ጓደኞች በዚህ ሰዓት ምን አይነት አሳዛኘ ስሜት ሊሰማቸው እንደሚችል እንጋራለን። ውድድሮቹን ለማየት በጉጉት ሲጠብቁም እንደነበር እንረዳለን። ይህም ሁኔታ በመፈጠሩ በጣም አዝናለሁ" ብለዋል።

"ሁሉም ውሳኔ ቅድሚያ መስጠት ያለበት ደህንነትን ነው። የጃፓን አጋሮቻችንና ወዳጆቻችን እዚህ ውሳኔ ላይ በቀላሉ አልደረሱም" በማለትም ስላለው ሁኔታ ገልፀዋል።