ኢትዮጵያ እየሞከረችው ያለው ደመናን ወደ ዝናብ የመቀየር ቴክኖሎጂ

ደመና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ በተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ማብራርያ በሰጡበት ወቅት ካነሷቸው ነጥቦች መካከል ደመናን ወደ ዝናብ የመቀየር ቴክኖሎጂ ኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን የሚመለከተው ይገኝበታል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ሙከራ እንደተደረገና በቅርቡ በይፋ እንደሚገለጽ ተናግረዋል።

ከሕዝብ ቁጥር እና የእርሻ መሬት ፍላጎት መጨመር ጋር በተያያዘ ደረቅ አካባቢዎችን ለምና ምርታማ ለማድረግ ቴክኖሎጂው እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

ለመሆኑ ክላውድ ሲዲንግ ምንድን ነው?

ቴክኖሎጂውን በተለይም ደረቅ የሆኑና ዝናብ የሚያጥራቸው አገራት ሙከራ እያደረጉበት ነው። የተገበሩት አገራትም አሉ።

የአየር ንብረትን በማሻሻል ከደመና ዝናብ ወይም በረዶ መፍጠርን የሚያካትት ሲሆን፤ ተመራማሪዎች እንደሚሉት ሲልቨር አዮዳይድ፣ ፖታሽየም አዮዳይድ እና ሌሎችም ንጥረ ነገሮችን በመጠቀም የሚተገበር ነው።

ንጥረ ነገሮቹን ወደ ከባቢ አየር በመልቀቅ ነው ዝናብ እንዲዘንብ ለማድረግ ጥረት የሚደረገው።

ንጥረ ነገሮቹን ከምድር ወደ ደመና ተኩሶ በመልቀቅ ወይም በአውሮፕላን አማካይነት ደመና ውስጥ ተረጭተው ከሟሙ በኋላ፤ በተፈጥሯዊ መንገድ የተከማቸ ደመና ዝናብ ሆኖ ወደ መሬት እንዲወርድ ያደርጋሉ።

ይህም ደመና በውስጡ ያዘለውን ውሃ ወደ መሬት ሳይለቅ ቀርቶ ሲከማች በሰው ሠራሽ መንገድ ንጥረ ነገሮችን ደመናው ውስጥ በመልቀቅ ዝናብ ይፈጠራል ማለት ነው።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ ይህ ቴክኖሎጂ ከ10 አስከ 15 በመቶ የዝናብ መጠንን ከፍ ሊያደርግ ይችላል።

የፎቶው ባለመብት, Jose Antonio Bernat Bacete

ቴክኖሎጂውን ከተገበሩ አገራት ጥቂቱ

ቴክኖሎጂው እአአ ከ1940ዎቹ ወዲህ ጥናት እንደተደረገበት የሳይንስ መዛግብት ይጠቁማሉ።

ቴክኖሎጂው ከተሞከረባቸው አጋጣሚዎች መካከል በጉልህ የሚጠቀሰው የ2008 የቤይጂንግ የክረምት ኦሊምፒክስ ነው። በወቅቱ በተመረጡ ቀናት ከደመና ዝናብ በመፍጠር የኦሊምፒኩ መክፈቻ እና መዝጊያ ቀናት ላይ እንዳይዘንብ ለማድረግ ለማድረግ ተሞክሮ ነበር።

የቻይና መንግሥት የአገሪቱን የአየር ሁኔታን በመለዋወጥ ደመናን ወደ ዝናብ የመቀየር ቴክኖሎጂ ጀምሯል። ይህ ሰው ሠራሽ ሂደት በጥቂት የቻይና ከተሞች ብቻ ይተገበር የነበረ ሲሆን ከጥቅምት ወዲህ ግን አገር አቀፍ እንደሚደረግ ተነግሮ ነበር።

ሂደቱ በሰው ሠራሽ መንገድ ዝናብና በረዶ ማዝነብን ያካትታል። እአአ በ2015 ይህን ሂደት በቻይና 5.5 ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎ ሜትር (የአገሪቱን 60 በመቶ) ለማዳረስ ታቅዷል።

ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮችም ይህ ሂደት ይተገበራል። ማሊ እና ኒጀር ተጠቃሽ ናቸው። እንደ አውስትራሊያ ያሉ አገሮች ድርቅን ለመከላከል ይጠቀሙታል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ቴክኖሎጂውን ከተገበሩ መካከል ትጠቀሳለች።

ከአስር ዓመታት በላይ ከደመና ዝናብ የማዝነብ ሂደትን ተግብረዋል። በቅርቡ ደግሞ ደመና ላይ ንጥረ ነገሮችን ለመርጨት የሚውሉ አውሮፕላኖች ቁጥር ጨምሯል።

እአአ 2014 ላይ በተገኘ መረጃ መሠረት ከ200 በላይ አውሮፕላኖች በመቶ ሺህ ዶላሮች በሚቆጠር ወጪ ተሰማርተዋል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ደረቃማ ከሚባሉ የምድራችን ቦታዎች አንዷ እንደመሆኗ ከተከማቸ ደመና ዝናብ ለመፍጠር የሚደረገውን ሥራ ከፍተኛ ትኩረት ትሰጠዋለች።

ሂደቱ በተለይም በአሜሪካ ከ1940ዎቹ ወዲህ ነው እየታወቀ የመጣው። ውጤቱ ላይ ጥያቄ ያላቸው ባለሙያዎች ግን አሉ።

በተለይም በምዕራብ አሜሪካ ያሉ አካባቢዎች በድርቅ የመታት እድል ስላላቸው ብዙ ግዛቶች ቴክኖሎጂውን ይጠቀማሉ።

በቅርቡ የወጣ መረጃ እንደሚያሳየው ከምዕራቡ የአሜሪካ ክፍል 40 በመቶው ለድርቅ የተጋለጠ በመሆኑ የአየር ንብረትን በሰው ሠራሽ መንገድ በመለወጥ ከደመና ዝናብ የማውረድ አማራጭን መጠቀም አስፈላጊ ነው።

ምን ያህል ውጤታማ ነው?

በዘርፉ ግንባር ቀደም የሚባሉት አሜሪካውያኑ ሳይንቲስቶች ቪንሰንት ሻፈር እና በርናንድ ቮንጉ ናቸው። ከደመና በረዶ በማውረድ እአአ በ1946 ያደረጉት ሙከራ ፈር ቀዳጅ ነው።

ዓለም አቀፉ የሜትሮሎጂ ተቋም 2017 ላይ ባወጣው ዘገባ መሠረት 56 አገራት ቴክኖሎጂውን እየተጠቀሙበት ነው።

ሂደቱ በአካባቢ እንዲሁም በጤና ላይ ሊያስከትል ስለሚችለው ተጽእኖ ጥያቄ የሚያነሱ ባለሙያዎችም አሉ።

ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ዝናብ ወይም በረዶ ማግኘት የቻሉ አገሮች ቢኖሩም፤ አካባቢ ላይ ዘላቂ ተጽዕኖ ያሳድራል? የሚለው አሁንም ድረስ አከራካሪ ነው።

2003 ላይ የተባበሩት መንግሥታት የጥናት ካውንስል ስለ ቴክኖሎጂው ውጤታማነት እንዲሁም ተጽዕኖ የሚያስከትል ስለመሆኑ ጥናት መረደግ ይገባዋል ብሎ ነበር።