መሳፍንትነት በቃኝ ያለው ልዑል ሃሪ ሥራ ተቀጠረ

ልዑል ሄሪ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ,

ልዑል ሄሪ

የሰሴክስ ዱክ የተሰኘ ስም ያለው የብሪታኒያው ልዑል ሃሪ ንጉሣዊውን ቤተሰብ ጥሎ ከወጣ ወዲህ ሥራ ሲፈልግ ቆይቷል።

ልዑሉ አሁን የሥራ ቅጥሩ ተሳክቶለታል።

ሃሪ፤ የአሜሪካ የአእምሮ ጤና ድርጅት በሆነው 'ቤተርአፕ' ኩባንያ 'ተፅዕኖ ፈጣሪ መኮንን' ሆኖ ተቀጥሯል።

ልዑል ሃሪ በለቀቀው መግለጫ በአዲሱ ሹመቱ 'እጅግ እንደተደሰተ' ተናግሯል።

ሥራው ምን እንደሆነ፣ በቀን ስንት ሰዓት እንደሚሠራ እንዲሁም ምን ያህል እንደሚከፈለው አልተገለፀም።

ባለፈው ዓመት መጋቢት መሳፍንትነት ይብቃኝ ብሎ የዩናይትድ ኪንግደምን ንጉሣዊ ቤተሰብ ከባለቤቱ ሜጋን መርክል ጋር ጥሎ የወጣው ሃሪ ሥራ ሲቀጠር ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ሃሪና ሚስቱ ሜጋን በያዝነው ወር መጀመሪያ ለጉምቱዋ አሜሪካዊት የቴሌቪዥን ሴት ኦፕራ ዊንፍሬይ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ብዙዎችን አጀብ ያሰኘ ሚስጥር አጋልጠው ነበር።

በቃል መጠይቃቸው ጥንዶቹ ስሙ ያልተጠቀሰ የንጉሳውያን ቤተሰብ አባል ልጃቸው ሲወለድ ቆዳው ምን ያህል ይጠቁር ይሆን ብሎ እንደጠየቃቸው ተናግረው ነበር።

የንግስቷ ይፋዊ መኖሪያ የሆነው ባኪንግሃም ቤተ-መንግሥት ጉዳዩ 'አሳሳቢ' ነው ብሎ እንደሚመረምረው አሳውቆ ነበር።

ከቀናት በፊት ቤተ-መንግሥቱ የብዝሃነት ምርመራ እያካሄድኩ ነው ብሎ መግለጫ ማውጣቱ አይዘነጋም።

ልዑል ሃሪ ሥራ ማግኘቱን በተመለከተ በለቀቀው መግለጫ ሥራው በአእምሮ ጤና ዙሪያ እንደሚያጠነጥን ይፋ አድርጓል።

የኩባንያው ዋና ሥራ አስኪያጅ አሌክሲ ሮቢቻው እንዳሉት ልዑል ሃሪ በሥሩ ምንም ዓይነት ሠራተኞች ባይኖሩም ሳን ፍራንሲስኮ በሚገኘው የኩባንያው ቢሮ ሊሠራ ይችላል።

ዎል ስትሪት ጆርናል እንደዘገበው የኩባንያው የመጀመሪያው ተፅዕኖ ፈጣሪ መኮንን ሆኖ የተሾመው ልዑሉ የአእምሮ ጤናን ያስተዋውቃል እንዲሁም እርዳታ ያሰባስባል።

ዋና ተፅዕኖ ፈጣሪ መኮንን የተሰኘው የሥራ መደብ ብዙም የተለመደ ባይሆንም እንደ አምነስቲ ያሉ ለትርፍ ያልተቋቋሙ ድርጅቶች ይጠቀሙበታል ሲል ዎል ስትሪት ጆርናል ፅፏል።

በፈረንጆቹ 2013 የተቋቋመው ቤተርአፕ በተንቀሳቃሽ ስልክ በመታገዝ ሥልጠና፣ ምክርና እገዛ ይሰጣል።

ኩባንያው በ66 ሃገራት፤ በ49 ቀንቋዎች ሥልጠና የሚሰጡ 2 ሺህ አሠልጣኞች አሉኝ ይላል።

ልዑል ሃሪ ከዚህ በፊት የዩኬ መከላከያ ሠራዊት አባላት በስፖርት የአካላቸውንና የአእምሮ ጤናቸውን የሚጠግኑበት ፈንድ አቋቁሞ ነበር።

ልዑሉ የአእምሮ ጤና በተመለከተ በይፋ ሲናገር ይደመጣል።

ሃሪና ሚስቱ ሜጋን አሁን በአሜሪካዋ ካሊፎርኒያ ይኖራሉ።