የእስራኤል ምርጫ፡ ኔታንያሁ መንግሥት መመሥረት የሚያስችላቸውን ድምጽ ሳያገኙ ቀሩ

ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ምስል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለአራተኛ ጊዜ በሚካሄደው የእስራኤል ምርጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አዲስ መንግሥት ለመመሥረት የሚያስፈልጋቸውን ድምጽ የማግኘት ዕድላቸው ዝቅተኛ እንደሚሆን ተገለጸ።

የኔታንያሁ ሊኩድ ፓርቲ እና አጋሮቻቸው 120 መቀመጫ ካለው የእስራኤል ፓርላማ 52 ወይም 53 መቀመጫዎችን ብቻ እንደሚያገኙ ተገምቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩን በኃላፊነት መቆየታቸውን የሚቃወሙ ፓርቲዎች 60 ወንበሮችን እንደሚያሸንፉ ተገምቷል።

በዚህም የያሚና ፓርቲን ድጋፍ ቢያገኙም ኔታንያሁ አብላጫ ድምፅ አይኖራቸውም ማለት ነው።

በቀድሞው የኔታንያሁ ደጋፊ ናፍታሊ ቤኔት የሚመራው ያሚና ፓርቲ ሰባት ወንበሮችን እንደሚያገኝ ቅድመ ግምት ቢሰጠውም የትኛውን ወገን እንደሚደግፍ እስካሁን በግልፅ አልታወቀም።

የቅድመ ምርጫ ውጤቶች ከተለቀቁ በኋላ ቤኔት በሰጡት መግለጫ “ለእስራኤል መንግሥት የሚጠቅመውን ብቻ አደርጋለሁ” ብለዋል።

ከቀጣይ እርምጃዎች በፊት ያሚና የመጨረሻ ውጤቱን እንደሚጠብቁ ለኔታንያሁ መናገራቸውን ገልጸዋል።

ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዙ ገደቦች ምክንያት ሁሉም ድምጾች ከረቡዕ ከሰዓት በፊት ይቆጠራሉ ተብሎ እንደማይጠበቅ የእስራኤል ማዕከላዊ የምርጫ ኮሚቴ አስታውቋል።

ኔታንያሁ ማክሰኞ ዕለት በትዊተር ገፃቸው ደጋፊዎቻቸውን አመስግነዋል። “በአመራሬ ቀኝ ዘመም እና ሊኩድ ከፍተኛ ድል አስመዝግበዋል። ሊኩድ እስካሁንም ድረስ ትልቁ ፓርቲ ነው” ብለዋል።

ዋነኛው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ያይር ላፒድ ፓርቲ የሽ አቲድ ከኔሴት ተብሎ በሚጠራው ከእስራኤል ፓርላማ መቀመጫዎች ውስጥ ከ 16 እስከ 18 የሚሆኑትን ያሸንፋል ተብሎ ተገምቷል። በፓርቲያቸው “እጅግ ትልቅ” ስኬት “ኩራት ይሰማኛል” ብለዋል።

“ከአንዳንድ የህብረቱ አመራሮች ጋር ለለውጥ የሚረዳ ውይይት ዛሬ አመሻሽ ጀምሬያለሁ። በቀጣዮቹ ቀናትም እቀጥላለሁ። በእስራኤል ጤናማ መንግስት ለማቋቋም የተቻለውን ሁሉ አደርጋለሁ” ሲሉ አስታውቀዋል።

በኔታንያሁ አመራር ላይ እንደ ህዝበ ውሳኔ በታየው ምርጫ ላይ ለመምረጥ ብቁ ከሆኑት መካከከል ከ 67.2% በላይ የሚሆኑት ድምጽ ሰጥተዋል፡፡

የ71 ዓመቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከጎርጎሮሳዊያኑ 2009 ጀምሮ በስልጣን ላይ ይገኛሉ። በ1990ዎቹ መገባደጃ ላይም ለሦስት ዓመታት በጠቅላይ ሚንስትርነት አገልግለዋል።

የምርጫ ዘመቻው ያተኮረው እስራኤል በዓለም ቀዳሚ ባደረጋት የኮቪድ -19 የክትባት መርሃግብር እና ከአንዳንድ የአረብ አገራት ጋር በፈጠሩት ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ላይ ነበር።

ተቃዋሚዎቻቸው ግን በሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸው በሥልጣን መቆየት እንደሌለባቸው ተከራክረዋል። ኔታንያሁ ግን ጥፋት አልፈጸምኩም በሚል ይከራከራሉ።

ባለፉት ሶስት ምርጫዎች ኔታንያሁም ሆኑ ተቀናቃኞቻቸው የተረጋጋ ጥምረት መመስረት አልቻሉም።