የአማራና የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፎች የመግለጫ ውዝግብ

ካርታ

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋና በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞኖች ውስጥ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ያወጣው መግለጫ ሕዝብን የማይመጥን ነው ሲል የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ነቀፈ።

ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ተከስቶ ለሰዎች ሞትና መፈናቀል እንዲሁም ለንብረት ውድመት ምክንያት እንደሆነ በተነገረው ግጭት ላይ የገዢው ብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያና የአማራ ቅርንጫፎች በመግለጫ እየተወዛገቡ ነው።

የአማራ ክልል መስተዳደር ክስተቱን አስመልክቶ ባለፈው ቅዳሜ ባወጣው መግለጫ "በንጹሐን ላይ የተፈፀመው ይህ ጥቃት በፍጹም ተቀባይነት የሌለው አደገኛና ከባድ ወንጀል ነው" ብሎ ነበር።

የገዢው ፓርቲ አንድ አካል የሆነው የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ የግጭቱ መነሻ "ጽንፈኝነት እና የፖለቲካ አሻጥር" እንደሆነ በመግለጽ "የአማራ ክልል መንግሥት ታጣቂዎች፤ ያልታጠቁ ሰዎችን፣ እርቅ ሲሰብኩ የነበሩ ሽማግሌዎችን፣ ሴቶችንና ሕጻናትን እንዲሁም ተጎድተው ወደ ሆስፒታል እየሄዱ የነበሩ ንፁሃንን በመግደል የጦር ወንጀል ፈጽመዋል" ሲል ባወጣው መግለጫ ወንጅሏል።

ለዚህም የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ ላይ በሰጠው ምላሽ በግጭቱ አካባቢ በሰውና በንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት በውል ሳይለይ የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ያወጣው መግለጫ "እራሱ ከሳሽና ፈራጅ" ሆኗል ብሏል።

ጨምሮም "መግለጫውን ለተመለከተ ሰው ፖለቲካችን ገና በአዝጋሚ የለውጥ ሂደት ውስጥ የሚገኝ፣ የምንመራውን ሕዝብ የማይመጥን፣ ከአገርና ከሕዝብ ክብር በእጅጉ የወረደ መሆኑን ያረጋግጣል" ሲል ተችቷል።

ግጭቱ የተከሰተበትን አካባቢ በተመለከተም "ውስብስብ አደጋ ያለበትና የኦነግ ሸኔ እንቅስቃሴ የሚጫነው" መሆኑን ገልጾ፣ "በተደጋጋሚ በተወሰዱ ስምሪቶች እርምጃ የተወሰደባቸው፣ በቁጥጥር ስር የሚገኙና በጥብቅ የሚፈለጉ የኦነግ ሸኔ አባላት መኖራቸው አዲስ መረጃ አይደለም" በማለት በአካባቢው ስውር ስልጠናዎችና አደረጃጀቶች እንዳሉ ገልጿል።

ነገር ግን የኦሮሚያ ብልጽግና ቀደም ሲል ባወጣው መግለጫ በዞኑ ውስጥ ኦነግ-ሸኔ እንደማይንቀሳቀስ ጠቅሶ "በንፁሃን ላይ የደረሰውን ጉዳት ለመደበቅ ሲባል ሕዝቡን በኦነግ ሸኔነት መፈረጅ ተቀባይነት የለውም" ሲል ገልጾ ነበር።

የግጭቱን መንስኤ በተመለከተም የአማራ ብልጽግና እንዳለው "የክልሉ ልዩ ኃይል ከአካባቢው መንቀሳቀሱን የተረዱ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች የሐይማኖት መሪና የአገር ሽማግሌ በመግደል" መጀመሩን ጠቅሶ በከባዱ የታጠቀ "የኦነግ ሸኔ ሠራዊት አካባቢውን በመውረር ድንገተኛ ጥቃት በመፈጸም በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳትና ዘረፋ ፈጽሟል" ሲል ከሷል።

ሁለቱ የብልጽግና ፓርቲ ዋነኛ ቅርንጫፎች በአማራ ክልል ውስጥ በተከሰተው በዚህ ግጭት ላይ ዙሪያ የክልሉ መንግሥት ያወጣውን መግለጫ ተከትሎ የሁለቱን ክልሎች የሚያስተዳድሩት የገዢው ፓርቲ ቅርንጫፎች እርስ በርስ የሚቃረን መግለጫ አውጥተዋል።

የኦሮሚያ ብልጽግና የአማራ ክልል የጸጥታ ኃይል ሰላማዊ ሰዎችን ማጥቃቱን በመግለጽ ሲከስ የአማራ ክልል አቻው ክሱ ኃላፊነት የጎደለው እና ለችግሩ መፈታት አስተዋጽኦ የማያደርግ መሆኑን በመግለጽ ተችቶታል።

በዚህም "የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ያወጣው መግለጫም ከችግር ፈቺነቱ ይልቅ የአእምሮን ሚዛን ያልጠበቀ ችኩልነት የሚጫነው፣ ተራ ውግንና ያጠላበት ኃላፊነት የጎደለው" መግለጫ ሆኖ እንዳገኘው ገልጿል።

የተከሰተው ምንድን ነው?

ባለፈው አርብ ምሽት ከሦስት ሰዓት ጀምሮ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን፤ ኤፍራታና ግድም ወረዳና አጣዬ ከተማ ውስጥ በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት የሰላማዊ ሰዎች ሕይወት ማለፉን ነዋሪዎችና የአካባቢው ባለሥልጣን ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።

የኤፍራታና ግድም ወረዳ የሠላምና የሕዝብ ደኅንነት ጽ/ቤት ኃላፊ እንዲሁም ምክትል አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ሰለሞን አልታየ እስከ ቅዳሜ ረፋድ ድረስ የአራት ሰዎች ሕይወት ማለፉን መመልከታቸውን የተናገሩ ሲሆን፤ ከዚያ በኋላ ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከዚህም ከፍ እንደሚል እያመለከቱ ነው።

የጅሌ ጥሙጋ አስተዳዳሪ አቶ ጀማል ሐሰን በበኩላቸው አጣዬና ጅሌ ጥሙጋ እንዲህ አይነት ግጭት ሲፈጠር የመጀመሪያ አይደለም በማለት ከባለፈው ግጭት በኋላ ሰላም ወርዶ እንደነበር አስታውሰዋል።

"አሁን ግን የአንድ ግለሰብ መገደልን ተከትሎ በተቀሰቀሰው ግጭት የክልሉ ልዩ ኃይል ለአንድ ወገን ሲያደላ ይታያል" ሲሉ ከሰዋል።

የክልሉ አስተዳደር ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው ለተፈጠረው ግጭት ምክንያቱ ሐሙስ መጋቢት 9/2013 ዓ.ም ምሽት "ጅሌ ጥሙጋ ውስጥ በግለሰቦች መካከል በተፈጠረ ጠብ ምክንያት አንድ ሰው ህይወት መጥፋት" ነው ብሏል።

ይህንንም ተከትሎ በአገር ሽማግሌዎችና በሐይማኖት አባቶች አማካይነት እርቅ ተፈጽሞ እንደነበር ጠቅሶ ነገር ግን "የኦነግ ቡድንና እሱን መሰል ተባባሪ የሆኑ አካላት እርቀ ሰላም ወርዶ መፍትሔ ያገኘውን ክስተት ምክንያት በማድረግ" ጥቃቱ መፈጸሙን ገልጿል።

በዚህም ከአርብ መጋቢት 10/2013 ዓ.ም ጀምሮ "አርሶ አደር ይይዘዋል ተብሎ በማይጠበቅ ከባድና የቡድን መሣሪያ በመታገዝ የተደራጀና ብዛት ያለው የታጠቀ ኃይል በአጎራባቹ የሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬ ከተማና አካባቢው ሰላማዊ ዜጎች ላይ ነውረኛ የሆነ ጥቃት ተፈጽሟል" ብሏል።

የአማራ ክልል እሁድ እለት ባወጣው መግለጫ ላይ በክስተቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች መጠን አልገለጸም።

በአማራ ክልል ውስጥ በሚገኙት በሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬና በክልሉ የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ጅሌ ጥሙጋ አካባቢዎች ባለፈው ሳምንት ሐሙስ የተከሰተን ግድያ ተከትሎ ከአርብ በምሽት ጀምሮ ከባድ የተኩስ ድምጽ በአካባቢው መከሰቱንና በዚህም በርካታ ሰዎች እንደሞቱ ተነግሯል።

ግጭቱ ለተከታታይ ቀናት የቆየ ሲሆን በሰው ላይ ከደረሰው ቁጥሩ እስካሁን በውል ካልታወቀው ጉዳት ባሻገር በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በአካባቢው የአማራና የኦሮሞ ማኅበረሰቦች የሚኖሩ ሲሆን ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ ግጭቶች አጋጥመው በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል።