የኢትዮጵያ የዝናብ ቴክኖሎጂና የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ድጋፍ

ደመና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ማክሰኞ ዕለት በተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት በጎጃም እና በሸዋ አካባቢዎች በሰው ሠራሽ ቴክኖሎጂ አማካይነት ዝናብ ማዝነብ እንደተቻለ መናገራቸው መነጋገሪያ ሆኗል።

አንዳንዶች በኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ሊሆን አይችልም ከሚል ግምት የተነሳ በተለያዩ መልኮች ጥርጣሬያቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ ሲያንጸባርቁ ነበር። ቀሪዎቹ ደግሞ የሌሎች አገራትን ተሞክሮ በማንሳት የጉዳዩን ሳይንሳዊነት እየገለጹ ነው።

የብሔራዊ ሜትሮሎጂ ድርጅት ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክንፈ ኃይለማርያም ጉዳዩ አዲስ ነገር እንዳልሆነ ጠቅሰው "በብዙ አገራት ውስጥ ተሞክሯል" ብለዋል።

ክላውድ ሲዲንግ ወይም "እኛ ደመና ማበልጸግ ልንለው እንችላለን" የሚሉት አቶ ክንፈ "ሳይንሱ በብዙ አገራት ተሞክሯል። ደመና የተፈለገውን ዝናብ የማይሰጥባቸው ምክንያቶች ስላሉ የደመና አቅምን የመጨመር ሂደት ነው። በዚህም ተጨማሪ ዝናብ እንዲፈጠር ያደርጋል" ይላሉ።

በተፈጥሯዊ ሂደት ደመና የተለያዩ ዑደቶችን አልፎ ዝናብ ይሆናል። ዑደቱ ተጠናቆ ወደ ዝናብ ለመቀየር በቂ ንጥረ ነገርም ያስፈልገዋል። ይህ ካልሆነ ዝናብ አይኖርም።

ሳይንሱም አስፈላጊውን ተጨማሪ ንጥረ ነገር በመጨመር ደመናን ወደ ዝናብ የሚቀይር ነው። ይህ ሂደት ነው ክላውድ ሲዲንግ ወይም ደመና ማበልጸግ የሚባለው።

ደመና እንዴት ዝናብ ይሆናል?

በአንድ ደመና ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወደ ዝናብ ያልተቀየሩ የዝናብ ነጠብጣቦችን ይኖራሉ። እነዚያም መጠናቸው አድጎ በመሬት ስበት ዝናብ ሆነው እንዲመጡ መሰባሰብ አለባቸው።

"በሂደቱ ነጠብጣቦቹን የሚሰበስብ ኬሚካል ነው የሚደረገው። የጨው ዝርያ ያላቸው እንደ ሶዲየም፣ ፖታሺየም፣ ክሎራይድና ናኖ ቴክኖሎጂ ለዚህ ተግባር ይውላሉ" ሲሉ አቶ ክንፈ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ስለዚህም ደመናው ኖሮ፣ በቂ እርጥበት ኖሮት፣ በበቂ ደረጃ አድጎ ወደ ዝናብ የማይቀየር ደመና የተጠቀሱት ንጥረ ነገሮችን ሲያገኝ በዓይን የማይታዩት የዝናብ ጠብታዎች ተሰብስበው ወደ ዝናብነት እንዲያድጉ ያደርጓቸዋል።

ይህ ተግባር እውን መሆን ከጀመረ ከሰባ ዓመታት በላይ የሆነው ሲሆን፤ ለዚህም በዓለም በሜትሮሎጂ ድርጀት የሚታወቁ ከ50 በላይ የዝናብ ማበልጸጊያ መንገዶችም አሉ።

እነዚህን ንጥረ ነገሮች ወደ ደመና ለማድረስ የተለያዩ አገራት የተለያዩ ዘዴዎች የሚጠቀሙ ሲሆን፤ ለምሳሌም ቻይና ሮኬት ስትጠቀም ኢራን ደግሞ በሰው አልባ አውሮፕላኖች (በድሮን) ወደ ደመና ትደርሳለች።

እንደ ኢትዮጵያ ተራራማ የሆኑ አገራት ከተራራዎች ላይ በመሆን ንፋስ በሚመጣበት አቅጣጫ ከመሬት ንጥረ ነገሮቹን በጭስ መልክ በመልቀቅ ወደ ደመናው እንዲደርስ ያደርጋሉ።

ለዚህ አገልግሎት በዋነኝነት የሚውለው ግን በአውሮፕላን አማካይነት የሚደረገው የንጥረ ነገሮቹ ርጭት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥም ተግባራዊ የተደረገው በአውሮፕላን መሆኑን የብሔራዊ ሜትሮሎጂ ድርጅት ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ ክንፈ እንደሚሉት ደመናን ወደ ዝናብ በመቀየር በኩል "ከአፍሪካ እንደ ኒጀር፣ ማሊ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ሞሮኮ ያሉ አገራት የሚጠቀሱ ሲሆን፤ ከእስያ በቻይና በስፋት ጥቃም ላይ ውሏል። እስራኤልም በዚህ የታወቀች ነች። በጠቃላይ ከ40 በላይ አገራት ዘዴውን ይጠቀማሉ" ይላሉ።

"ስለዚህም ለእኛ ነው እንጂ ለሌላው ዓለም ጉዳዩ አዲስ አይደለም። ለዚህ ደግሞ የደመናው ዓይነት ይለያል። ጊዜና ቦታውም ይለያል። የሚደረገውም ለመዝነብ የማይችል ደመናን ማበልጸግ ነው። በብዙ አገራት ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን፤ እኛ አገርም እየተሞከረ ነው" ሲሉ በተጨባጭ መሞከሩን አረጋግጠዋል።

ይህም ተግባር ኢትዮጵያ ውስጥ በሙከራ ደረጃ ላይ መሆኑን የሚገልጹት ምክትል ሥራ አስፈጻሚው፤ ለዚህ የሚሆኑ አካባቢዎችም በተለያዩ መስፈርቶች አማካይነት እንደሚመረጡም ገልጸዋል።

"ቦታዎቹ የሚመረጡት በአየር ንብረት ራዳር የሚካለሉ እና ለሙከራው የሚሆን ደመና መኖሩ ሲረጋገጥ ነው። የአሁኑ ሙከራም የመጀመሪያ ነው" ብለው ከዚህ በመነሳትም ሰፋ ያለ ፕሮግራም እንደሚኖር አስረድተዋል።

የፎቶው ባለመብት, MINISTRY OF INNOVATION & TECHNOLOGY

የምስሉ መግለጫ,

ደመናን ወደ ዝንብ የሚለውጠው ንጥረ ነገር ከአውሮፕላን ክንፍ ላይ የሚረጭበት መንገድ

ድርቅን ለማስወገድ ሊውል ይችላል?

ደመናን ወደ ዝናብ ለመቀየር ጥቅም ላይ የሚውለው ቴክኖሎጂ የዓለም አገራትን በተለያዩ ጊዜያት የሚያጠቃውን የድርቅ ችግር በመቅረፍ በኩል አስተዋጽኦ ሊኖረው ይችል እንደሆነ የበርካቶች ጥያቄ ነው።

ድርቅ የረዥም ጊዜ የዝናብ እጥረት መሆኑን የሚናገሩት አቶ ክንፈ "ደመናው ካልመጣ ዝናቡን ማበልጸግ አይቻልም። ደመናውን ደግሞ አንፈጥርም። ለመበልጸግ ዝግጁ የሆነ ደመና በተፈጥሮ መምጣት አለበት" ይላሉ።

ይህ ዝናብን የማዝነብ ዘዴ ድርቅን ለመከላከል አስተዋጽኦው ዝቅተኛ ነው። ምክንያቱም ደመና በሌለበት ቦታ ተግባራዊ ሊሆን ስለማይችል ነው።

"ደመና ኖሮ ከደመናው የሚገኘውን ዝናብ የመጨመር ዘዴ ነው እንጂ፤ ሙሉ ለሙሉ በረዥም ጊዜ ድርቅ ደመና የማይፈጠር ከሆነ ድርቅን መቀየር አይደለም" ብለዋል አቶ ክንፈ።

ይህ ዝናብን የማግኘት ዘዴ በተለይ በአንድ ወቅት የሚጠበቀው የዝናብ መጠን ሳይገኝ ቀርቶ ደረቃማ ሁኔታ ሰፍቶ ሲገኝ በሰብሎች ላይ ጉዳት ሊደርስ ይችላል። ስለዚህም በዚያ ወቅት የተወሰኑ ቀናት እንዲዘንብ በማድረግ መስክ ላይ ያሉትን የአዝዕርቶች የማገዘዝ ዕድልን ይፈጥራል።

ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ ተራራማ መሆኗ ደመናን በማበልጸግ በኩል የራሱ ጠቀሜታ እንዳለው የሚጠቅሱት አቶ ክንፈ፤ "በአንዳንድ ወቅቶች ደመና እያለ የማይዘንብባቸው ቦታዎች አሉ። ተራራማ ቦታዎች ደመናን በማበልጸግ ከሜዳማ አካባቢዎች ይልቅ በተሻለ ሁኔታ የዝናብ መጠን ለመጨመር ያስችላሉ" ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከየት ድጋፍ አገኘች?

ኢትዮጵያ ዝናብ የማበልጸጉን የሙከራ ተግባር እያከናወነች ያለችው ከተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ መንግስት እና የሜትሮሎጂ ማዕከል ጋር በመተባበር ባገኘችው የቴክኖሎጂና የባለሙያዎች ድጋፍ እንደሆነ አቶ ክንፈ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይህንን ሥራ በዋናነት የሚያስተባብረውና የሚመራው ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር ሲሆን የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ፣ ብሔራዊ ሜትሮሎጂ፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ተቋም፣ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የግብርና ሚንስቴር እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ እየተሳተፉበት ይገኛሉ።

ሥራው አስካሁን በሙከራ ደረጃ ላይ ያለ ሲሆን ለዚህም አገሪቱ የነበራት አንድ የአየር ንብረት መከታተያ ራዳርን ወደ በሦስት ለማሳደግ እየተሰራ ነው። ከዚህ አንጻርም አገልግሎት ሊሰጥ የሚችል ሳተለይት እንዳመጠቁ የብሔራዊ ሜትሮሎጂ ድርጅት ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክንፈ ጠቅሰዋል።

ከደመና ዝናብ የማግኘቱ ሙከራ እንደሚቀጥልም ጠቅሰው በተከታይነት "ከአዲስ አበባ እስከ ሻውራ የተሻለ ደመና በተገኘበት አካባቢ ሙከራ ይደረጋል። ጥሩ ደመና ካገኘን ቅድሚያ ሰጥተን የምንሞክርበት ከሻውራ ወደ ወልዲያ ባለው አቅጣጫ ሰሜን እና ደቡብ ወሎን ጨምሮ ነው" ብለዋል።

ይህ ሙከራ ግን የሚወሰነው ከአየር ሁኔታ መከታተያ ራዳር የሚገኘው የደመና ዓይነቶች ይዘት እና መጠንን በሚያመለክተው መረጃ ላይ ይሆናል። "በዚህም ምክንያት ሙከራው የሚደረግበትን ትክክለኛ ቀንና ቦታ ለመግለጽ አስቸጋሪ ነው" ሲሉ አስረድተዋል።