ለነዳጅ ዋጋ መጨመር ምክንያት የሆነው የግብጹ መተላለፊያ መዘጋት

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በመተላለፊያው ዳርቻ ላይ በአሸዋ የተያዘው የመርከቧ ክፍል
በሱዊዝ የመተላለፊያ መስመር ላይ ቆማ የባሕር ላይ ጉዞን ባስተጓጎለችው መርከብ ተነሳ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ ታይቷል።
በመተላለፊያ መስመሩ መዘጋት ሰበብ የድፍድፍ ነዳጅ አቅርቦት ሊስተጓጎል ይችላል በሚል ስጋት ነው ረቡዕ ዕለት የዓለም የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ የታየበት።
በግብጹ የሱዊዝ የባሕር መተላለፊያ ቦይ ዳርቻ ላይ መንቀሳቀስ አቅቷት የዓለማችንን ወሳኝ የባሕር መስመርን የዘጋችውን የጭነት መርከብ ለማንቀሳቀስ ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል።
የግብጽ ባለሥልጣናት እንዳሉት ኤቨር ጊቭን የተባለችው የጭነት መርከብ በመተላለፊያው መስመር ላይ መንቀሳቀስ አቅቷት የቆመችው ማክሰኞ ጠዋት በአካባቢው አሸዋ ያዘለ ከባድ አውሎ ነፋስ በተከሰተበት ጊዜ ነው።
በዚህም ሳቢያ ከእስያ ወደ አውሮፓ አስፈላጊ ቁሶችን ጭነው በመተላለፊያው በኩል ለማቋረጥ የመጡ ከቦዩ ሰሜንና ደቡብ በኩል እጅግ በርካታ መርከቦች ማለፊያ አጥተው እንዲቆሙ ተገደዋል።
በሰሜናዊ ምሥራቅ አፍሪካ የሚገኘውን ወሳኝ የባሕር ላይ መተላለፊያን ዘግታ የምትገኘው የጭነት መርከብ ባለቤት የሆነው ጃፓናዊ በመርከቧ ምክንያት በዓለም የንግድ ልውውጥ ላይ ለተፈጠረው መስተጓጎል ይቅርታ መጠየቁ ተነግሯል።
በከባድ ንፋስ ምክንያት መስመሯን ስታ መተላለፊያውን የዘጋችውን መርከብ ለማንቀሳቀስ በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ የገለጸው የመርከቧ ባለቤት "ነገር ግን የተቻላቸውን ጥረት በማድረግ" ላይ መሆናቸውን ገልጿል።
አስካሁን ቢያንስ በመተላለፊያው በኩል ለማቋረጥ እየጠበቁ ያሉ ከ150 በላይ የጭነት መርከቦች ተሰልፈው እየተጠባበቁ መሆኑ ተነግሯል።
ሜዲትራኒያንና ቀይ ባሕርን በሚያገናኘው በሱዊዝ መተላላፊያ ቦይ አውሮፓንና አስያን ለማገናኘት አጭሩ መስመር ሲሆን የዓለማችን 12 በመቶ የሚሆነው የንግድ ጭነት የሚያልፈው በዚሁ በኩል ነው።
በአሁኑ ወቅት መርከቧን መንገድ እንድትለቅ ለማድረግ ስምንት ጎታች ጀልባዎች ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።
ይህንን ሥራ እያከናወነ የሚገኘው ኩባንያ መተላለፊያውን ለማስከፈት ሳምንታት ሊወስድ እንደሚችል ያስጠነቀቀ ሲሆን የመርከቧን ክብደት ለመቀነስ የጫነቻቸውን ኮንቴይነሮች መቀነስ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል ተብሏል።
የፎቶው ባለመብት, EPA
መተላለፊያውን የዘጋችው ኮንቴይነር የጫነችው ኤቨርግሪን የጭነት መርከብ
የፎቶው ባለመብት, EPA
የፎቶው ባለመብት, Reuters
መተላለፊያውን የዘጋችው ኤቨርግሪን የጭነት መርከብ የሚያሳይ የሳተላይት ምሰል
የፎቶው ባለመብት, EPA
የሱዊዝ ቦይ ባለሥልጣናት ሁኔታውን በስፍራው ሆነው ሲከታተሉ
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለፈው ዓመት በየቀኑ መተላለፊያውን በአማካይ 52 የሚደርሱ መርከቦች አቋርጠውታል
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሱዊዝ ቦይ 193 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን ሦስት ተፈጥሯዊ ሐይቆች አሉት