አሜሪካ፡ በኮሎራዶ ጥቃት የሟቾች እና ጥቃት አድራሹ ማንነት ይፋ ተደረገ

ኮሎራዶ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኮሎራዶ ግዛት ባለስልጣናት በትናትናው ጥቃት የተገደሉ 10 ግለሰቦችን እና የጥቃት አድራሹን ማንነት ይፋ አደረጉ።

በገበያ ስፍራ የተገሉት ሰዎች እድሜ በ20 እና 65 መካከል የሚገኝ ሲሆን ከሟቾቹ መካከል የ7 ልጆች አባት የሆነ የፖሊስ አባል ይገኝበታል።

ጥቃቱ የቆመው ፖሊስ ከጥቃት አድራሹ ጋር የተኩስ ልውውጥ አድርጎ በቁጥጥር ሥር ካዋለ በኋላ ነው።

ተኳሹ የ21 ዓመት ወጣት አሕመድ አል አሊዊ አል ኢሳ የሚባል ሲሆን በ10 ሰዎች ግድያ ክስ ይመሰረትበታል ተብሏል።

ጥቃት አድራሹ አብዛኛውን ሕይወቱን በኮሎራዶ ግዛት በምትገኝ አርቫዳ መኖሩን ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል።

ፖሊስ ተኳሹ ይህን ጥቃት ለመሰንዘር ምን እንዳነሳሰው እስካሁን ግልጽ አይደለም ብሏል።

ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ከጥቃቱ በኋላ በሰጡት አጭር መግለጫ መሰል ጥቃቶችን ለማስቆም የጦር መሳሪያ ቁጥጥር መደረግ አለበት፤ የጦር መሳሪያ መግዛት በሚሹ ላይም የኋላ ማንነት ማጣራት አስፈላጊ ነው ሲሉ አሳስበዋል።

ስለ ጥቃቱ ምን እናውቃለን

በገበያ በደረሰው ጥቃት ፈጻሚው ቆስሎ መያዙ ተመልክቷል። የደረሰው ጥቃት በዩቲዩብ ቀጥታ መተላለፉም ታውቋል።

ጥቃቱ የደረሰው በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር 8፡30 ቀን ላይ ሲሆን ግለሰቡ ወደ ገበያ አዳራሹ እንደገባ መተኮስ ጀምሯል።

ጥቃቱ የደረሰበት አካባቢ፣ ቦውልደር ፖሊስ ከ20 ደቂቃ በኋላ በትዊተር ገፁ ላይ "በኪንግ ሱፐርስ የገበያ ስፍራ ተኩስ የከፈተ ግለሰብ አለ" ሲል ጽፎ ነበር።

ከሁለት ሰዓት በኋላ ፖሊስ ሰዎች ከአካባቢው እንዲርቁ አስጠንቅቋል።

በአከባቢው የነበሩት ሰዎች ሁኔታውን በተንቀሳቃሽ ምስል አስቀርተውት በማህበራዊ ሚዲያዎች አጋርተው ነበር። በአንዱ ቪዲዮ ላይ "ምን እንደተከሰተ አላውቅም. . . የተኩስ ድምጽ ሰማሁ። የሆነ ሰው ተመትቶ ወደቀ" ሲል ምስሉን የሚቀርጸው ይሰማል።

በቪዲዮው ላይ ፖሊስ ደርሶ የገበያ አዳራሹን ሲከብ ይታያል።