የቻይና ትልቁ የመኪና አምራች ቴስላን ሊቀናቀን ነው

የቻይና ትልቁ የመኪና አምራች ቴልሳን ሊቀናቀን ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የቻይናው ትልቁ የመኪና አምራች ጊሊ ከቴስላ ጋር እንደሚያወዳድረው ተስፋ የጣለበትን የኤሌክትሪክ መኪና ሊጀምር ነው፡፡

የቮልቮ እና ሎተስ ባለቤት የሆነው የቻይናው ኩባንያ የቻይናን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ፍላጎት ለማሟላት ማክሰኞ ዕለት ዜክር የተሰኘ መኪናውን አስተዋውቋል፡፡

ቻይና የካርቦን ልቀትን ለመቋቋም ማቀዷን በማወደስ ኤለን መስክ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

የቴስላው መስራች መኪኖቹ ውስጥ ስለሚገጠሙት ካሜራዎች የደህንነት ጉዳይ የቻይናውያንን ጭንቀት ለማስወገድ እየሞከረ ነው፡፡

ጊሊ ዜክር በተሰኘው ስም ከፍተኛ የኤሌክትሪክ መኪናዎችን ያመርታል። በ2021 ሦስተኛው ሩብ ዓመት ለተጠቃሚዎች ማድረስ ይጀምራል ተብሎም ይጠበቃል፡፡

ኩባንያው ባለው ብራንዶች የኤሌክትሪክ መኪናዎችን ሲያመርት ነበር። በቮልቮ መኪናዎች ባለቤትነት ፖልስታር የተሰኙ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መኪኖችን ያመርታል፡፡ ዋና መሥሪያ ቤቱ ስዊድን ቢሆንም መኪናው የሚመረተው ቻይና ውስጥ ነው፡፡

በአብላጫው ባለቤትነት የጊሊ የሆነው ሎተስ በበኩሉ ኤቪጃ የተባለ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠራ መኪና ይሠራል፡፡

ጊሊ በተጨማሪም የለንደን ታክሲ አምራች የሆነውን የለንደን ኢቪ ኩባንያም ባለቤት ነው። ይህ ደግሞ የቤንዚን ሞተርም ሆነ በኤሌክትሪክ ባትሪ በሚሠሩ ታክሲዎች ላይ ትኩረት አድርጓል፡፡

ዜክር ባለፈው ዓመት በቻይና ከፍተኛ ሽያጭ ከነበረው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ የቴስላ ሞዴል 3 ከፍተኛ ፉክክር ይገጥመዋል ተብሏል፡፡ እንዲሁም ጤናማ ሽያጭ ካላቸው ኒዮ፣ ኤክስፔንግ እና ሊ አውቶ ጋርም ይወዳደራል፡፡

የጃፓኑ ኒሳን እና የፈረንሣዩ ፒ ኤስ ኤ ፔጆ ሲትሮን የቻይናው ዶንግፌንግ ሞተር አጋር ሲሆኑ አዲሱን ኤልክትሪክ መኪና ቮያህን በሐምሌ ወር ለቻይና ደንበኞቹ ማድረስ ይጀምራል ተብሏል፡፡

በ2025 ቻይና ውስጥ ከተሸጡት ተሽከርካሪዎች ከአንድ አምስተኛ በላይ የሚሆኑት ኤሌክትሪክ እንዲሆኑ ቤጂንግ ትፈልጋለች፡፡

ጊሊ ከቮልስዋገን ጋር ተመሳሳይ ተደራሽነት ያለው የቻይና የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ አምራች ለመሆን ፍላጎት አለው፡፡ ከቮልቮ እና ከሎተስ ጋር በመሆን በመርሴዲስ ቤንዝ ባለቤት ዳይምለር ውስጥም አናሳ ድርሻ አለው፡፡

የዜክር የመጀመሪያ ስትራቴጂ በቻይና ገበያ ላይ ያተኮረ ይሆናል። የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ዓለም አቀፋዊ ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱ የባህር ማዶ ዕድሎችንም ይመለከታል ተብሏል፡፡

ፕሪሚየም ብራንዱ ሊንግሊንግ ቴክኖሎጂ በተባለ አዲስ ኩባንያ ስር የሚሠራ ሲሆን መቀመጫውንም በምስራቅ ቻይና ሄፊይወ ውስጥ አድርጓል፡፡

"ሊቀ መንበር ሊ ሹፉ የ24 ዓመቱን ጊሊ ኩባንያን ማነቃቃት አስፈላጊ መሆኑን ተገንዝበዋል" ብለዋል በእስያ የመኪና ገበያ ላይ ትኩረቱን ያደረገው የዞዞ ጎ ዋና ስራ አስፈጻሚ ማይክል ደን።

“እዚያ ለመድረስም ከጊሊ ራሱን ችሎ የሚሠራውን ሊንግሊንግ ቴክኖሎጂዎችን ጀምረዋል” ብለዋል፡፡

ጊሊ በ2020 ብቻ 1.32 ሚሊዮን መኪናዎችን የሸጠበትን ዓመታዊ ውጤቱን ሪፖርት ሲያደርግ ባለፈው ዓመት ከነበረው 1.36 ሚሊዮን ጋር በማነጻጸር ነው፡፡

የቴስላ ውዝግብ

የቴስላ አለቃ ኤለን መስክ ማክሰኞ ከቻይናው የመንግስት ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት አጭር ቃለ ምልልስ በአገሪቱ የአምስት ዓመት የኢኮኖሚ ዕቅድ ውስጥ በተቀመጠው የካርቦን ልቀት ግቦች መደነቁን ተናግሯል፡፡

ቤጂንግ የመኪናው አምራች በቻይና መረጃን የሚይዝበት መንገድ ያሳስበኛል በሚል ወታደራዊ አባላት እና ቁልፍ የመንግስት ሠራተኞች ቴስላን እንዳይጠቀሙ አግዳለች።

መስክ ለቻይና ፖለቲከኞች እና ነጋዴዎች በሳምንቱ መጨረሻ በቪዲዮ እንደገለጹው ቴስላ ከቻይናም ሆነ ከሌሎች አገሮች በተሽከርካሪዎቹ የሚሰበሰበውን መረጃ ለአሜሪካ መንግስት በጭራሽ አይሰጥም፡፡

መከላከያው በመኪናዎቹ ውስጥ የተገጠሙ ካሜራዎች የተሰበሰቡትን መረጃዎች በተመለከተ የደህንነት ስጋቶች እንዳሉ አንስቶ ነበር፡፡

ቻይና በ2020 ከቴስላ ዓለም አቀፍ ገቢ አንድ አምስተኛ የሚሆነውን የ31.5 ቢሊዮን ዶላር ድርሻ እንደያዘች ይፋ ተደርጓል፡፡