ኮሮናቫይረስ፡ የአውሮፓ ሕብረት መሪዎች የክትባት አቅርቦትን ለመጨር እየተነጋገሩ ነው

ክትባት

የፎቶው ባለመብት, EPA

የአውሮፓ ሕብረት መሪዎች የኮቪድ-19 ክትባት አቅርቦትን ለመጨመር እና ስርጭቱን ማሻሻል በሚቻሉባቸው መንገዶች ላይ ሊወያዩ ነው።

ዛሬ ሐሙስ የአውሮፓ ኮሚሽን መሪዎች ክትባቶች ወደሌሎች አገራት የሚላኩበት ሁኔታ ላይ ተጨማሪ ቁጥጥር እንዲደረግ ድጋፋቸውን እንደሚጠይቅም ይጠበቃል።

የበይነ መረብ ስብሰባው የሚካሄደው በበርካታ የአውሮፓ አገራት ሶስተኛው ዙር የኮሮረናቫይረስ ስርጭት መስፋፋቱን ተከትሎ ነው።

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደንም ቢሆኑ ሐሙስ ዕለት ስብሰባውን እንደሚካፈሉና የአውሮፓ ሕብረትና የአሜሪካ ግንኙነት ላይ ምክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

የአውሮፓ ህብረት የክትባት ስርጭት ከዩናይትድ ኪንግደም የክትባት ስርጭት አንጻር ሲታይ መዘግየት ታይቶበታል ተብሏል። የአውሮፓ ኮሚሽን ለስርጭቱ መዘግየትና ተያያዥ ችግሮች በዋነኛነት እንደ አስትራዜኔካ ያሉ ክትባት አምራች ኩባንያዎችን ተጠያቂ አድርጓል።

ነገር ግን የአውሮፓ ህብረት መሪዎች አሁንም ቢሆን ከሕብረቱ ውጭ ወዳሉ አገራት የሚላኩ ክትባቶችን ላይ ክልከላ መጣል በሚለው ላይ የተለያየ አቋም ይዘዋል። ክትባቱ ወደ ሌሎች አገራት የማይላክ ከሆነ በሕብረቱ አገራት ውስጥ የሚኖረው የክትባት አቅርቦት በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል ተብሎ ይታመናል።

ቤልጂየም እንደገለጸቸው ከሆነ ባለፉት ሁለት ወራት ወደ ሌሎች አገራት ከተላከው 40 ሚሊየን ክትባት መካከል አንድ አራተኛ የሚሆነው የተላከው ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ነው።

የአውሮፓ ሕብረትና ዩናይትድ ኪንግደም ረቡዕ ዕለት በጋራ ባወጡት መግለጫ ላይ ሁሉም ተጠቃሚ መሆን የሚችልበትን ሁኔታ ለመፍጠርና የክትባት አቅርቦቱን ለማስፋት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

''ሁላችንም አንድ አይነት የሆነ ወረርሽኝ ነው እያጋጠመን ያለው፤ ስለዚህ ሶስተኛው ዙር የኮሮናቫይረስ ስርጭት በሕብረቱ እና በዩኬ መካከል የሚኖረውን ግንኙነት ይበልጥ አስፈላጊ ያደርገዋል'' ብለዋል በመግለጫቸው።

የአውሮፓ ሕብረት ወደ ውጪ የሚላኩ ክትባቶች ላይ ገደብ የሚያስቀምጥ ከሆነ ከሕብረቱ በተሻለ መልኩ ዜጎቻቸውን እየከተቡ የሚገኙት እንደ ዩኬ እና አሜሪካ ያሉ አገራት ተጎጂዎች ይሆናሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ ክትባቶቹን አምርተው ወደሌሎች አገራት የሚልኩ እንደ ቤልጂየምና ኔዘርላንድስ ያሉ የአውሮ ሕብረት አባል አገራት ገደቡን አጥብቀው እየተቃወሙት እንደሆነ ተገልጿል።