ኬንያ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን የሚገኙባቸውን ጣቢያዎች ልትዘጋ ነው

በኬንያ የሚገኘው የደደብ መጠለያ ጣቢያ

የፎቶው ባለመብት, TONY KARUMBA

የምስሉ መግለጫ,

በኬንያ የሚገኘው የደደብ መጠለያ ጣቢያ

ኬንያ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን የሚገኙባቸውን የዳዳብ እና የካኩማ መጠለያ ጣቢያዎችን እዘጋለሁ አለች።

ይህ የኬንያ መንግሥት ውሳኔ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የምሥራቅ አፍሪካ ስደተኞችን እታ ፈንታ አጣብቂኝ ውስጥ የከተተ ሆኗል።

የኬንያ መንግሥት ዳዳባ እና ካኩማ የሰደተኛ መጠለያ ጣቢያዎችን እንደሚዘጋ ይፋ ያደረገው ትናንት ሲሆን፤ ኬንያ የተባበሩት መንግሥታት ስደተኞቹን ወዴት እንደሚወስድ እንዲያሳውቃት የ14 ቀናት የጊዜ ገደብ ሰጥታለች።

በሁለቱ መጠለያ ጣቢያዎቹ ውስጥ በዋናነት ከሶማሊያ እና ከደቡብ ሱዳን የመጡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰደተኞች ይገኛሉ።

በዳዳብ የሰደተኞ መጠለያ ጣቢያ ከ218 ሺህ በላይ ስደተኞች የሚገኙ ሲሆን አብዛኞቹ የሱማሊያ ዜጎች ናቸው።

በካኩማ ደግሞ ወደ 200 ሺህ የሚጠጉ ሰደተኞች የሚገኙ ሲሆን በዚህ መጠለያ ጣቢያ ደግሞ ትልቁን ቁጥር የሚይዙት ከደቡብ ሱዳን የተፈናቀሉ ናቸው።

የተባበሩት መንግሥት የሰደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን እንደሚለው ጥር 2013 ዓ.ም ላይ 29 ሺህ 718 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በኬንያ ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የሚገኙት በካኩማ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ነው።

ኬንያ እነዚህን ሁለት የሰደተኛ መጠለያ ጣቢያዎችን ለመዝጋት ስትወስን የአሁኑ የመጀመሪያዋ አይደለም። በተለያዩ ወቅቶች ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር በሚደረግ ንግግር ኬንያ መጠለያ ጣቢያዎቹን ለመዝጋት የሰጠቻቸውን ውሳኔዎች ስትሽር ቆይታ ነበር።

ይሁን እንጂ የኬንያ የአገር ውስጥ ሚንስትር ፍሬድ ማቲያንጊ፤ ትናንት መጠለያ ጣቢያዎቹን የመዝጋት ወሳኔን በተመለከተ ኬንያ ከተባበሩት መንግሥታት ጋር ምንም አይነት ንግግር እንደማይኖራት ተናግረዋል።

የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትሩ በኬንያ ላይ የሚቃጡ የሽብር ጥቃቶች መነሻ መጠለያ ጣቢያዎቹ መሆናቸውን እንደ ምክንያት በማንሳት አገራቸው መጠለያ ጣቢያዎቹን ለመዝጋት መወሰኗን አስረድተዋል።

ፍሬድ ማቲያንጊ በቅርቡ የኬንያ እና የሱማሊያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙት መሻከር መጠለያ ጣቢያውን ለመዝጋት ውሳኔ ላይ ካደረሱ ምክንያቶች መካከል እንደሚጠቀስም አውስተዋል።

በአሁኑ ወቅት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ስደተኞች በኬንያ የሚገኙ ሲሆን ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ቁጥር የያዙት ደግሞ ሶማሊያውያን ናቸው።

የተባበሩት መንግሥት የሰደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን በበኩሉ የኬንያ መንግሥት መጠለያ ጣቢያዎቹን ከመዝጋቱ በፊት የሰጠው ቀነ ገደብ አነስተኛ መሆኑን አስታውቋል።

ኮሚሽኑ የኬንያ መንግሥት ውሳኔ ስደተኞች ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ጫና ከፍተኛ መሆኑን እና የኮቪድ-19 ወረርሽኝም ስጋት እንደሆነ አስታውቋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን በጉዳዩ ላይ ከኬንያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር እንደሚመክር አስታውቋል።

ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ስጋት

ኢትዮጵያዊው ስደተኛ ሞሐመድ አብዱላሂ ላለፉት 27 ዓመታት በዳዳብ የሰደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ መኖራቸውን ይናገራሉ። በቆይታቸውም ትዳር መስረተው ሰባት የቤተሰብ አባላትን እንደሚያስተዳድሩ ይናገራሉ።

ስደተኛው አቶ ሞሐመድ የኬንያ መንግሥት ውሳኔ ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ እጣ ፈንታቸውን አጣበቂኝ ሁኔታ ውስጥ ሊከት እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።

"በጣም ተጨንቀዋል። ሰው ሁሉ 'ምንድነው ምንሆነው' እያለ እየተጨነቀ ነው" በማለት ከኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች በተጨማሪ የደቡብ ሱዳን፣ የኡጋንዳ እና የቡሩንዲ ዜጎች ስጋት እንደገባቸው ያስረዳሉ።

ሌላኛው በዳዳብ የሰደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ነዋሪ የሆነ እና ስሜ አይጠቀስ ያለ ኢትዮጵያ የኦሮሞ ማኅብረሰብ ተወካይ ውሳኔው ተግባራዊ የሚሆን አይመስለኝም ብሏል።

ከዚህ ቀደም የኬንያ መንግሥት በተደጋጋሚ የሰደተኞች መጠለያ ጣቢያዎቹን እዘጋለሁ ካለ በኋላ ውሳኔው መሻሩን በማስታወስም፤ "መንግሥት ጣቢያዎቹን እዘጋለሁ ይበል እንጂ በውሳኔው ሊጸና አይችልም የሚል እምነት አለኝ" ይላል።

ይህ ወጣት ምንም እንኳ መንግሥት ከሚለው በተቃራኒ ጣቢያዎቹ አይዘጉም የሚል ግምት ቢኖረውም፤ በመጠለያ ጣቢያዎቹ ውስጥ የሚኖሩ ስደተኞች ግን በውሳኔው ስጋት እንዳደረባቸው ለቢቢሲ ተናግሯል።