ኮሮናቫይረስ፡ ኢትዮጵያ ኮቪድ-19ን ለመቆጣጠር ጥብቅ እርምጃዎችን ተግባራዊ ልታደርግ ነው

በሚሌንየም ሆስፒታል ጽኑ ሕሙማን ክፍል ውስጥ የመተንፈሻ መሳሪያ የተገጠመለት ሰው

የፎቶው ባለመብት, AMANUEL SILESHI

ኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ መስፋፋትን ለመግታት ከዚህ በፊት ተቀምጠው የነበሩ የክልከላ መመሪያዎችን በጥብቅ ተግባራዊ የሚያደርጉ እርምጃዎችን መውሰድ ልትጀመር መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ቀደም ሲል የኮሮናቫይረስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ መመሪያ ቢኖርም ተግባራዊነቱ ላይ ችግሮች እንዳሉ ያመለከተው የጤና ሚኒስቴር፤ በአሁኑ ጊዜ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ቸልተኝነት ለማስወገድ በመመሪያው ላይ የተቀመጡ የክልከላ እርምጃዎችን ማስተግበር አስፈላጊ መሆኑን ገልጿል።

ስለሆነም አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰውን የወረርሽኙን መስፋፋት ለመቆጣጠር የጤና ሚኒስቴር፣ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና ፌደራል ፖሊስ እርምጃዎቹን ተግባራዊ ለማድረግና አፈጻጸሙን እንደሚከታተሉ ይፋ አድርገዋል።

በጥብቅ ተግባራዊ ይደረጋል በተባለው መመሪያ መሠረት፣ ማንኛውም ቫይረሱ የተገኘበት ሰው ወደ ማኅበረሰቡ ሳይቀላቀል ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ፣ እንዲሁም ቫይረሱ ሊተላለፍባቸው በሚያስችል ሁኔታ ንክኪ ማድረግ ደግሞ በሕግ የሚያስቀጣ ይሆናል።

በተጨማሪም በየትኛውም ቦታ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ሳያደርጉ መንቀሳቀስ በጥብቅ የተከለከለ ሲሆን፤ የንግድና ሌሎች የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎት ሰጪም ሆነ ተቀባይ ጭምብል ማድረግ የግድ ይኖርባቸዋል ተብሏል።

ስብሰባዎችም ቀደም ሲል በወጣው መመሪያ በተቀመጠው ግዴታ መሠረት አስፈላጊውን የበሽታውን መከላከያ ጥንቃቄዎች ማድረግ የሚጠበቅባቸው ሲሆን ይህም ተግባራዊ ስለመደረጉ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግ ተገልጿል።

በመመሪያው ላይ የተመለከቱ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ተግባራዊ በማያደርጉት ላይም እርምጃዎች እንደሚወሰድ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አመልክቷል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ ያለው የኮሮናቫይረስ ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ በአሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ባለፉት ሳምንታት የሚወጡት የወረርሽኙ መግለጫዎች ያመለከቱ ሲሆን የበሽታው መስፋፋት በአሳሳቢ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን የጤና ባለሙያዎች እየገለጹ ነው።

በዚህም ሳቢያ በበሽታው በየዕለቱ የሚያዙ፣ በጽኑ የሚታመሙና ለህልፈት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር ከዚህ በፊት ከነበረው በአስደንጋጭ ሁኔታ ጨምሯል።

በጽኑ ታምመው የህክምና ድጋፍ የሚፈልጉ ህሙማን ቁጥርም በማሻቀቡ የህክምና ተቋማት ያላቸው የማስተናገድ አቅም መፈተኑን፣ የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያና የኦክስጂን አቅርቦት እጥረት ማጋጠሙም ባለፈው ሳምንት መገለጹ ይታወሳል።

ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በተከታታይ የሚያወጣቸው መረጃዎች፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ከተመዘገበው በላይ በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው በበሽታው የተያዙ ሰዎች መመዝገባቸውን ያሳያል።

ከዚህ አንጻርም ከመጋቢት 11 አስከ መጋቢት 17/2013 ዓ.ም በተደረገ ምርመራ 12‚758 ግለሰቦች ላይ የኮቪድ-19 ቫይረስ የተገኘባቸው ሲሆን፤ በእነዚሁ ቀናት ውስጥ 151 ግለሰቦች በወረርሽኙ ሳቢያ ለሞት ተዳርገዋል።

ትናንት አርብ ምርመራ ከተደረገላቸው 8‚171 ሰዎች ውስጥ 2‚097ቱ በኮቪድ-19 መያዛቸው ሲረጋገጥ፤ ይህም ማለት ከተመረመሩት 100 ግለሰቦች 26ቱ በቫይረሱ ተይዘዋል።

ከዚህ ባሻገር ደግሞ በወረርሽኝ ተይዘው የጽኑ ህሙማን ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥርም እየጨመረ ሲሆን፤ የህክምና ተቋማቱ ካላቸው የሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መሳሪያና ግብዓት አቅርቦት አንጻር ቁጥራቸው ከፍተኛ በመሆኑ የተወሰኑት ድጋፉን ለማግኘት ወረፋ ለመጠበቅ መገደዳቸው ተገልጿል።

ቫይረሱ የሚገኝባቸው ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረባት ባለችው በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ 196,621 ሰዎች ላይ ወረርሽኙ የተገኘባቸው ሲሆን 2,769 ሰዎች ደግሞ በበሽታው ምክንያት ህይወታቸው ማለፉን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ ያመለክታል።