ኪነጥበብ፡ ከቤተመንግሥት እስከ ሕዝቡ የወረደው ቴአትር በ100 ዓመታት

የቴአትርን መቶኛ ዓመት ለማሳየት የተዘጋጀ

የፎቶው ባለመብት, SilThiatre Face book page

ቴአትር በአገራችን መድረክ ጅማሬውን ያገኘው ፖለቲካዊ ጭብጥን በመምዘዝና ንግሥቲቱንና ከፍተኛ ሹማምንቶቿን የክብር ታዳሚው በማድረግ ነው።

እንደውም የቤተ መንግሥትን ዐይን ብቻ ለመሳብ የተሰናዳ እስኪመስል ድረስ ተራውን ማኅበረሰብ እዩልኝ ወይንም ድግሴን ቅመሱልኝ የማለት ልምድ አልነበረውም።

በጊዜ ሒደት ግን ቴአትር ከዚህ ብቸኛ ዐውድ ወጥቶ፣ ሰውኛ በሆኑ ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ዙርያ ይጻፍም ይተወንም ጀመር።

ይኸው ዛሬ ላይ ደግሞ ስለ ፍቅር እያለቀስንም እየሳቅንም፣ ስለ ፖለቲካችን እየተሳለቅን፣ ረቂቅ የሰው መልኮች ግዘፍ ነስተው እየተመለከትንም፣ በተለያዩ የተውኔት ዘውጎች የስሜት መፈራረቆችን እያስተናገድን ከማዕዱ እየተካፈልን ነው።

ጷጉሜ 3/1913 ዓ. ም ሆቴል ውስጥ መታየት የጀመረው የአማርኛ ዘመናዊ ተውኔት፤ ዘንድሮ 100 ዓመት ሞልቶት በባለሙያዎቹ ሽር ጉድ እየተባለለት ነው።

ታሪክን የኋሊት

የኢትዮጵያ የአማርኛ ዘመናዊ ቴአትርን በ1913 ዓ. ም ያዋለዱት ፊታውራሪ ተክለሀዋርያት ተክለማርያም ናቸው።

እኚህ የአማርኛ ዘመናዊ ተውኔት ፈር ቀዳጅ የጻፉት እና ያዘጋጁት የመጀመሪያው ተውኔት "የአውሬዎች ኮሜዲያ መሳለቂያ" ነው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቴአትር ጥበባት መምህሩ ረዳት ፕሮፌሰር አሰፋ ወርቁ፤ ቴአትሩ ለዕይታ የበቃው በወቅቱ አገሪቱን ያስተዳድሩ ለነበሩ ከፍተኛ ሹማምንት ነበር ይላሉ።

"የአውሬዎች ኮሜዲያ መሳለቂያ" የዕይታ እድሜው አንድ ቀን ብቻ እንደነበርም ያስረዳሉ።

ይህ ተውኔት የቤት እና የዱር እንስሳትን ገጸ ባህሪ በማድረግ የተሠራ ነው።

እነዚህ ገጸ ባህሪያት በዘመኑ የነበሩ ፖለቲከኞችን ይወክላሉ በሚል በአንዳንድ ሹማምንት ዘንድ የተለጠጠ ትርጉም ተሰጥቶት ነበር።

"የአውሬዎች ኮሜዲያ መሳለቂያ" ለእነዚህ ከፍተኛ ሹማምንቶች ከቀረበ በኋላ ዳግም ለተመልካች እይታ ያልቀረበበት ምክንያት በወቅቱ ተውኔቱን ከተመለከቱ ሹማምንቶች መካከል ንግሥት ዘውዲቱ ፊት እየቀረቡ ተውኔቱ እኮ ሥርዓትሽን የሚሰድብ፣ የሚዘልፍ፣ የሚያናንቅ፣ የሚያዋርድ ነው በማለት ሹክ በማለታቸው ነው።

የበግ ገጸ ባህሪ ልጅ እያሱን፣ ተኩላው ደግሞ ራስ ተፈሪ መኮንንን ይወክላል ያሉ እና ወገን ለይተው የተከራከሩ ነበሩ።

በወቅቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ራስ ተፈሪ መኮንን ተብለው እየተጠሩ አልጋ ወራሽ ነበሩ። ንጉሠ ነገሥታት ዘውዲቱ ደግሞ የአገሪቱ ንግሥት በመሆን ኢትዮጵያን ያስተዳድሩ ነበር።

ከዚያ በኋላ ቴአትሩ ታገደ።

የብሔራዊ ቴአትር ዳይሬክተር የሆነው ደራሲና አዘጋጅ ማንያዘዋል እንደሻው ይህንን ታሪክ በመጥቀስ፤ የኢትዮጵያ ቴአትር ጉዞ የተጀመረው "በመከልከል ነው" ይላል።

ይህ ቴአትር ዳግም ለእይታ የበቃው አጼ ኃይለሥላሴ ከነገሡ ከሁለት ዓመት በኋላ በ1925 ዓ. ም ነው።

ለእይታ በሚበቃበት ወቅት እንደዛሬው ግርማ ሞገሥ የሞላቸው ቴአትር ቤቶች፣ በብርሃን የሚንቆጠቆጡ መድረኮች አልነበሩም።

በወቅቱ ቴራስ በሚባል ሆቴል ውስጥ መታየቱን ረዳት ፕሮፌሰር አሰፋ ይናገራሉ።

ያኔ ታድያ ተውኔት በማሳየት ስማቸው የሚጠቀሰው ግራንድ፣ ሮያል፣ ግሌዝ እና ማጀስቲክ የተሰኙት ሆቴሎች ነበሩ።

የኢትዮጵያ ተውኔት ሲጀምር ፖለቲካዊ ተውኔቶችን በማቅረብ እንደሆነ ፕሮፌሰሩ ይናገራሉ።

የዘመኑን የሥርዓት ብልሹነት፣ የባለሥልጣናቱን ደካማነት እና አላዋቂነት በማሳየት ነው የጀመረው። ይህ በማኅበረሰቡ ዘንድ የታዩ ጉድለቶችን በመንቀስ የጀመረው የኢትዮጵያ ተውኔት ጉዞ ቀጣይ መዳረሻ ተፈሪ መኮንን እና ዳግማዊ ትምህርት ቤት ሆነ።

ቴአትር በ1919 ዓ. ም ትምህርት ቤት የገባው፤ በሆቴል ቤቶች ውስጥ ያሳዩ በነበሩት ዶ/ር ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ፣ ባለቤታቸው ቀፀላወርቅ ቱሉ፣ የጊዮርጊስ ትምህርት ቤት መምህር በነበሩት መስፍን ቀለመወርቅ የሚባሉ መምህራን አማካይነት ነው።

እነዚህ በኢትዮጵያ ቴአትር ታሪክ ውስጥ የሚጠቀሱ ግለሰቦች የፍቅር እና የአገልግሎት ማኅበር የሚል አቋቁመው ማኅበሩ ለሚደግፋቸው ታዳጊዎች የሚሆን ገቢ ለማሰባሰብ ቴአትርን እንደመሣሪያነት መጠቀማቸው ይጠቀሳል።

ከዚህ በኋላ ከሆቴል ቤት ወጥቶ ቀስ በቀስ ለቋንቋ ማስተማሪያነት ወደ ትምህርት ቤት ገባ።

የፎቶው ባለመብት, Mekonen Ayele

የምስሉ መግለጫ,

በ1996 በብሔራዊ ትያትር የተመደረከው ኪሊዎፓትራ ተውኔት ላይ ዓለማየሁ ታደሰ እና ሙሉዓለም ታደሰ ሲተውኑ። ተውኔቱ በጆን ድራይደን ተደርሶ በአዶኒስ የተተረጎመ ሲሆን ኣዘጋጀው ደግሞ ተስፋዬ ገብረማርያም ነበር።

"ድርሰትና ዝግጅት በወንዶች ቁጥጥር ሥር የወደቀ ሙያ ነው"

ተውኔት ሲጀመር በወንዶች ነው የተጀመረው የምትለው ደራሲና አዘጋጅ መዓዛ ወርቁ ቴአትር በትምህርት ቤቶች ውስጥ ለቋንቋ ማስተማሪያነት ሲውል፤ በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ዮፍታሄ ንጉሤ፣ በመነን ትምህርት ቤት ደግሞ ወ/ሮ ስንዱ ገብሩ እንደነበሩ ታነሳለች።

በእርግጥ በትወናው ላይ ቀድሞውም ቢሆን ሴቶች እንደነበሩ የምታነሳው መዓዛ፤ በድርሰቱ እና ዝግጅቱ ፋና ወጊ በመሆን ግን ከፊት የነበሩት ወ/ሮ ስንዱ ገብሩ መሆናቸውን ትናገራለች።

መነን ትምህርት ቤት በወቅቱ የሴቶች ትምህርት ቤት ሲሆን፤ ወ/ሮ ስንዱ ደግሞ በማስተዳደር ኃላፊነታቸውን ይወጡ ነበር።

ወ/ሮ ስንዱ ደርሰውና አዘጋጅተው ለቋንቋ ማስተማርያነት የሚያቀርቧቸው ተውኔቶች ላይ የወንድ ገጸ ባህሪንም ሴቶቹ በመተወን ይሳተፉ እንደነበር ትናገራለች።

ወ/ሮ ስንዱ በመራሔ ተውኔትነት (አዘጋጅነት) በመደረኳቸው ሥራዎች ላይ እህታቸው የውብዳር ገብሩን (እማሆይ ጽጌ ማርያም) በፒያኖ የማጀቢያ ሙዚቃ ያሠሩ እንደነበርም ትናገራለች።

ወ/ሮ ስንዱ ቴአትሮች መጻፍ ብቻ ሳይሆን በማሳተምም ስማቸው ጎልቶ እንደሚነሳ በመጥቀስ "የየካቲት እልቂት" የሚባል መጽሐፋቸውን ትጠቅሳለች።

ወ/ሮስንዱ ተውኔቶቻቸው በተለያዩ ሆቴሎች እንዲሁም በአገር ፍቅር ታይተዋል።

የአማርኛ ዘመናዊ ቴአትር የ100 ዓመት ጉዞን ወደኋላ መለስ ብሎ በሴታዊነት መነጽር ለሚመለከት፤ እንዲህ እንደ ወ/ሮ ስንዱ ሰንደቃቸው ከፍ ብሎ የሚውለበለብ በርካታ ሴቶችን በድርሰትና በዝግጅት ሙያ ውስጥ አያገኝም።

"ድርሰትና ዝግጅት በጣም በወንዶች ቁጥጥር ሥር የወደቀ ሙያ ነው" የምትለው መዓዛ፤ እንደማንኛውም ሙያ በጥበቡ ዓለም ውስጥም ጎልቶ እንደሚታይ ታነሳለች።

በቴአትር ጥበባት ውስጥ ድርሰትና ዝግጅት ማለት የውሳኔ ሰጪነት ሚና መሆኑን በማንሳትም፤ በዚህ የአመራር ሰጪነት ቦታ ላይ በጣት የሚቆጠሩ ሴቶች ብቻ እንደሚገኙ ትናገራለች።

በድርሰት የሚታወቁ ሴቶች በጣም ጥቂት መሆናቸውን በመጥቀስ የሚሠሩትም ከወንዶች ጋር በመተባበር መሆኑን ትናገራለች።

ሴቶች በድርሰትና በዝግጅቱ በብዛት መምጣት የጀመሩት ከኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ የግል ቴአትር ፕሮዳክሽኖች መስፋፋታቸውን ተከትሎ መሆኑን ትገልጻለች።

የግል ቴአትር ፕሮዳክሽኖች ሴቶች በግላቸው እንዲጽፉ፣ እንዲያዘጋጁና ፕሮዲውስ እንዲያደርጉ እድል መፍጠራቸውን ከራሷ ልምድ በመነሳት ትናገራለች።

በዚህም አዜብ ወርቁ፣ ገነት አጥላው፣ ባዩሽ ዓለማየሁ፣ ዓለምፀሀይ በቀለ እንዲሁም ትዕግሥት ዓለሙን በአስረጅነት ትጠቅሳለች።

የፎቶው ባለመብት, Siletheatre Facebook Page

የቴአትር ውጣ ውረድ

ደራሲና አዘጋጅ ማንያዘዋል ቴአትር ከመነሻው ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በጥርጣሬ የሚታይ ዘረፍ መሆኑን ይጠቅሳል።

አንዳንዴ የሳንሱር ገመዱ ጠበቅ ሲል ሌላ ጊዜ ደግሞ ሲላላ 100 ዓመት እንደሞላው በመግለጽ፤ በዚህ ምክንያት እድገቱ የ100 ዓመት እድሜው ያህል አለመሆኑን ያነሳል።

እንደ ማንያዘዋል ገለጻ የቴአትር ፈታኝ ጊዜያት ወታደራዊው የደርግ አገዛዝ ሥልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ነበር።

ወቅቱ ጠንካራ ሳንሱር የነበረበት፣ ሥራዎች በአብዛኛው የፕሮፓጋንዳ የነበሩበት እንደሆነ ይጠቅሳል።

ይህንንም ሲገልጸው ቴአትር "ታንቆ ተይዞ ነበር ማለት ይቻላል" ይላል።

በሌላ በኩል ደግሞ በዚሁ ዘመን ቴአትር እንዲስፋፋ፣ በበርካታ ተመልካቾች ዘንድ እንዲታይም የተሠሩ መልካም ነገሮች እነደነበሩ ያነሳል።

በደርግ ጊዜ በየተቋማቱ ሰኞ ከሰዓት የሚካሄድ የውይይት ክበብ ውስጥ ውይይት ይካሄድ ነበር።

ይህንን አሰልቺ የሆነ የፖለቲካና የፕሮፓጋንዳ ውይይት ለማለዘብ አብዮታዊ ተውኔቶች ሲወጡ እነርሱን የውይይት ክበብ አባላት እንዲያዩት ይደረግ ነበር።

እነዚህ ተውኔቶች በቅናሽ ለፋብሪካ እና ለመንግሥት ሠራተኞች ይቀርቡ ስለነበር ቴአትር ቤቶች በበርካታ ሰዎች እንዲጎበኙ እድል ፈጥሯል።

ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ሲመጣ በአንጻራዊነት ነጻነት ስለተገኘ በሳምንት በየቴአትር ቤቶቹ አምስት እና ስድስት ቴአትሮች መታየት መጀመራቸውን ይጠቅሳል።

ነገር ግን እየቆየ ሲሄድ በግልጽ ሳንሱር ባይካሄድም በተለያየ መልኩ ተጽዕኖ ማሳደር መጀመሩን ይናገራል።

ይህንንም ሲያስረዳ በብሔራዊ ቴአትር የጌትነት እንየው "ወይ አዲስ አበባ" የተሰኘው ሙዚቃዊ ቴአትር ድርሰት በካድሬዎች ፖለቲካዊ ትርጉም ተሰጥቶት ከመውጣቱ በፊት መታገዱን ይጠቅሳል።

የፎቶው ባለመብት, Mekonnen Ayele

የኢትዮጵያ ቴአትር ለወደፊትስ?

ለደራሲና አዘጋጅ ማንያዘዋል በአሁኑ ሰዓት በርካታ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍል ከፍተው ተማሪዎችን ማስመረቃቸው ለአገሪቱ የቴአትር እድገት አንዱ መልካም እድል ነው።

ነገር ግን አሁንም በአገሪቱ ያሉት ቴአትር ቤቶች ጥቂትና በአዲስ አበባ ብቻ የተወሰኑ በመሆናቸው እነዚህ ዩኒቨርስቲዎች የሚያስመርቋቸው ተማሪዎች የት ይቀጠራሉ? የሚለው ያስጨንቃቸዋል።

በቅርቡ ትምህርት ሚኒስቴር ከመዋዕለ ሕጻናት እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ኪነ ጥበብን በሥርዓተ ትምህርቱ ሊያካትት መሆኑን ሰምቻለሁ በማለትም ይህን ጭንቀታቸውን በተወሰነ መልኩ እንደሚቀንስላቸው ያምናል።

የኪነ ጥበብ ትምህርት በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ መካተቱ መሠረታዊ የጥበብ እውቀት ይዞ የሚያድግ ትውልድ እንዲሁም በሳል ተመልካች ለማፍራት አሌ የማይባል አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አያይዞ ያነሳል።

የኢትዮጵያ ቴአትርን ወደ ፊት ሲያስበው በአዲስ አበባ እና በአማርኛ ቋንቋ ብቻ ታጥሮ ባይቀር ደስ ይለዋል።

በተለያዩ የአገሪቱ ቋንቋዎች ቴአትሮች በብዛት አለመሠራታቸው ለእድገቱ እንቅፋት መሆኑንም ያክላል።

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ቴአትርን በመደበኛነት የሚያሳዩ ቢኖሩ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለዓለም የጥበብ እድገት እንደሚጠቅም ያሰምርበታል።

መዓዛ የሴቶች ተሳትፎን በቴአትር ውስጥ ከማየታችን በፊት ጥበቡ መቀጠል አለበት ትላለች።

ቴአትር ሲጻፍ ሲመደረክ እስትንፋሱ ሲቀጥል የሴቶች ተሳትፎ እየደረጀ እና እየሰፋ ይመጣል ባይ ናት።

እርሷ እና ባልደረቦቿ የቴአትርን መቶኛ ዓመት ለማሰብ በሚያደርጉት ውይይት ውስጥ የሴቶች ሚና ከፍ እንዲል እንደሚጥሩም ትገልጻለች።