ፌስቡክ ከኮቪድ ጋር በተየዘያዘ የቬንዙዌላ ፕሬዝዳንትን ገጽ አገደ

የቬንዙዌላው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ,

የቬንዙዌላው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ

የቬንዙዌላው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ምንም አይነት ማረጋገጫ ሳያቀርቡ ከእፅዋት የተቀመመ መድኃኒት ከኮቪድ-19 ሊፈውስ ይችላል ማለታቸውን ተከትሎ ፌስቡክ ገጻቸውን አግዷል።

ፕሬዝዳንቱ ባሳለፍነው ጥር የእጽዋት ውህድ የሆነው መድሃኒት ከበሽታው ሊፈውስይችላል ብለው ነበር። ለዚህም ነው ፌስቡክ ለ30 ቀናት በገጻቸው ላይ ምንም እንዳያሰፍሩ ያገዳቸው።

ማዱሮ ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዙ መረጃ ማሰራጨት ላይ ያወጣቸውን ፖሊሲዎች በተደጋጋሚ እንደጣሱም ፌስቡክ አስታውቋል።

ማዱሮ ከኮቪድ ጋር በተያያዘ ከማህበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎች እገዳ የደረሳቸው ብቸኛው የዓለም መሪ አይደሉም።

የቀድሞው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የብራዚሉ ፕሬዝደንት ጃየር ቦልሶናሮ ስለኮቪድ ባስተላለፉት መልዕክት እግድ ገጥሟቸው ነበር።

የፌስቡክ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ "በፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ገጽ ላይ ፖሊሲዎቻችንን በመጣስ ስለ ኮቪድ-19 የተዛባ መረጃ የሚያስተላልፍና ሰዎችን ለጉዳት የሚያጋልጥ ቪዲዮ አንስተናል። በአሁኑ ወቅት ቫይረሱን ለመፈወስ የሚያስችል መድኃኒት የለም የሚለዉን የዓለም የጤና ድርጅት መመሪያን እንከተላለን። በተደጋጋሚ ህጎቻችን በመተላለፋቸው ምክንያት ገፁን ለ 30 ቀናት ያገድን ሲሆን በዚህ ወቅት ማንበብ እንጂ መረጃ ማስተላል አይችሉም" ብለዋል፥

ባለፈው ዓመት ፌስቡክ ሃይድሮክሎሮኪን የተባለው መድሃኒት ኮሮናቫይረስን ለማከም ውጤታማ ነው በሚል በብራዚል ፕሬዝዳንት ቦልሶናሮ የተለጠፈውን ቪዲዮ ፌስቡክ ሰርዞ ነበር።

በጥቅምት ወር ዶናልድ ትራምፕ ኮቪድ -19 ከጉንፋን "ያነሰ ገዳይ" ነው የሚል ጽሑፍ ለጥፈው ፌስቡክ ሰርዞታል።

በማኅበራዊ ድር አምባዎች ላይ የኮቪድ-19 ሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ሰፊ ችግር ፈጥሯል።

በርካታ ሰዎች በሺዎች የሚቆጠሩ የፀረ-ክትባት መረጃዎችን በፌስቡክ እና በትዊተር አሰራጭተዋል ሲል በእንግሊዝ መቀመጫውን ያደረገው ካውንተር ዲጂታል ሄት አስታውቋል።

የማዳጋስካር ፕሬዚዳንት አንድሪ ራጆሊና ባለፈው ዓመት ኮቪድ-ኦርጋኒክስ የተባለ ያልተረጋገጠ የዕፅዋት ውህድ ቢያስተዋውቁም የዓለም ጤና ድርጅት ባህላዊ መድኃኒቶች አጠቃቀማቸውን የሚደግፍ ሳይንሳዊ ማስረጃ ሊኖራቸው ይገባል ብሎ ነበር።