ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን የኮቪድ ክትባትን ለደሃ አገራት እንዲያጋሩ ተጠየቁ

ክትባት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በጎ አድራጊ ድርጅቶች የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን የኮቪድ-19 ክትባትን ለደሃ አገራት እንዲያጋሩ ተጠየቁ።

ድርጅቶቹ ዩናይትድ ኪንግደም ለደሃ አገራት የምታካፍለውን የኮቪድ-19 መጠን 'በፍጥነት' ያሳዉቁን ሲሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰንን በደብዳቤ ጠይቀዋል።

ዩኬ በኮቫክስ አማካኝነት ክትባት ለደሃ አገራት እንድታጋራ ከጠየቁት መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች መካከል የተባበሩት መንግሥታት የህጻናት አድን ድርጅት እና ዌልካም ትራስት ተጠቃሽ ናቸው።

የዩኬ መንግሥት በበኩሉ ወደፊት ከሚረከባቸው ክትባቶች የሚተርፈውን ለመስጠት ተስማምቻለሁ ብሏል። ከዚህ በተጨማሪም የዩኬ መንግሥት ለኮቫክስ ፕሮግራም 548 ሚሊዮን ፓውንድ ማዋጣቱን ገልጿል።

"ይህ ድጋፍ ዩኬን ከፍተኛ ድጋፍ ካደረጉ አገራት ዝርዝር ያካትታታል። ይህም ድጋፍ ከ20 ያላነሱ አነስተኛ ገቢ ያላቸው አገራት ክትባት እንዲደርሳቸው አድርጓል" ብሏል የዩኬ መንግሥት።

የዩናይትድ ኪንግደም 400 ሚሊዮን ክትባት እንዲቀርብላት ያዘዘች ሲሆን ይህም ጠቅላላ የሕዝብ ቁጥሯን ከግምት በማስገባት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ክትባት ይተርፋታል።

ቦሪስ ጆንሰን ክትባቶች ለደሃ አገራት እንዲሰጡ እየጠየቁ ያሉ በጎ አድራጊ ድርጅቶች እንደሚሉት ከሆነ ዩኬ ከ100 ሚሊዮን በላይ ትርፍ ክትባት ከአምራቾች እንዲቀርብላት አዛለች።

ኮቫክስ የተሰኘው ፕሮግራም አነስተኛ ገቢ ያላቸው አገራት የኮቪድ-19 ክትባት እንዲያገኙ የሚያስችል ህብረት ነው።

በኮቫክስ አማካኝነት ከዩኬ ክትባት ሊያገኙ የሚችሉት አነስተኛ ገቢ ያላቸው አገራት መካከል ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ፣ አፍጋኒስታን፣ ሄይቲ እና ዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኮንጎ ተጠቃሽ ናቸው።

እስካሁን ከ29 ሚሊዮን በላይ አዋቂዎች በዩናይትድ ኪንግደም ክትባቱን ውስደዋል።