ቦርዱ የኦነግን ጠቅላላ ጉባኤና በምርጫ የመሳተፍ ጥያቄን ውድቅ አደረገ

አቶ አራርሶ ቢቂላ

የፎቶው ባለመብት, ONN

የምስሉ መግለጫ,

አቶ አራርሶ ቢቂላ

በቅርቡ አዲስ የአመራር አባላትን መርጫለሁ ያለው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ክንፍ ያካሄደው ጠቅላላ ጉባኤና በምርጫ ለመሳተፍ ያቀረበው ጥያቄ በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ውድቅ ተደረገበት።

በኦነግ ከፍተኛ የአመራር አባላት መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ሳቢያ ግንባሩ በሁለት ወገኖች መካከል ተከፍሎ በቀጣዩ ምርጫ ለመሳተፍ የዕጩዎች ምዝገባ ሳያከናውን የጊዜ ገደቡ ጊዜ እንዳለፈው ይታወሳል።

ቦርዱ ውሳኔውን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ላይ እንደጠቀሰው በግንባሩ አመራሮች መካከል የተፈጠረውን ክፍፍልና ውዝግብን ተከትሎ ከሁለቱም ወገን አቤቱታዎችና የማሳወቂያ ደብዳቤዎችን ሲቀበል መቆየቱ በመግለጽ ችግሩ መፍትሄ እንዲያገኝ የበኩሉን ጥረት ማድረጉን ገልጿል።

ግንባሩ በቀደምት ሊቀመንበሩ በአቶ ዳውድ ኢብሳና ምክትላቸው በነበሩት በአቶ አራርሶ ቢቂላ መካከል ለሁለት ተከፍሎ የተለያየ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ውሳኔዎችን እየሰጠ ነው።

በአቶ ዳውድ የሚመራው ቡድን በግንባሩ ላይ የተለያዩ ጫናዎች እየደረሱ ነው በሚል በምርጫው ላይ እንደማይሳተፍ ቢገልጽም የአቶ አራርሶ ቡድን ግን ተገቢውን ማስተካከያ እንዳደረገ በመግለጽ በምርጫው የመሳተፍ ፍላጎቱን ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አቅርቦ ነበር።

በግንባሩ ውስጥ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታትም ሁለቱ ወገኖችን በተናጠል እንዲሁም የፓርቲውን የሥነ ሥርዓት እና የቁጥጥር ኮሚቴን በማነጋገር ያሉ አስተዳደራዊና ሕጋዊ መንገዶች ሁሉ በመጠቀም መፍትሔ ለመስጠት ጥረት ማድረጉን ቦርዱ ገልጿል።

በመጨረሻም የግንባሩን ጠቅላላ ጉባኤ መጥራት ፓርቲው ለገጠመው ችግር ብቸኛ መፍትሔ መሆኑን በማስረዳት በውዝግብ ውስጥ ያሉ አመራሮችም ይህንኑ ሃሳብ በመቀበል የተፈጠረውን ችግር በጠቅላላ ጉባኤ እንዲፈታ መወሰኑ የምርጫ ቦርድ መግለጫ አስታውሷል።

በዚህም የግንባሩ አንደኛ ወገን ጠቅላላ ጉባኤ በማካሄድ አዲስ የአመራር አባላት መምረጡን በመግለጽ፣ "በውስጥ ችግሩ ምክንያት የጠቅላላ ጉባኤ ሳያካሂድ በመቆየቱ የነበረበትን ችግር ግምት ውስጥ በማስገባት የምልክት መረጣና የዕጩ ተወዳዳሪዎች ምዝገባ እንዲያደርግ እንዲፈቅድለት ጠቅላላ ጉባኤውንም እንዲጸድቅለት" መጠየቁን ምርጫ ቦርድ አመልክቷል።

ቦርዱም የቀረቡለትን ሰነዶች መርምሮ በጠቅላላ ጉባኤው አካሄድና ተሳታፊዎች በኩል የግንባሩን ሕገ ደንብ ባከበረ መንገድ አለመካሄዱን የሚያመለክቱ አምስት ነጥቦችን በማስቀመት የቀረበለትን የጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔና በምርጫ የመሳተፍ ጥያቄን እንዳልተቀበለው ገልጿል።

ስለዚህም በመጪው ግንቦት ወር ማብቂያ ላይ በሚካሄደው አጠቃላይ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ ፍላጎቱን ገልጾ የነበረው በአቶ አራርሶ ቢቂላ የሚመራው የኦነግ አንድ ክፍል ያካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።

ባለፈው ሳምንት በአገሪቱ ምክር ቤት ቀርበው ለተነሱ ጥያቄዎች መልስና ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በምርጫው ለመሳተፍ ፍላጎት ያለው ፓርቲን አሁንም ቦርዱ ቢቀበለው እንደሚደግፉ ገልጸው ነበር።

በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆነው ኦነግ በምርጫው የመሳተፉ ሁኔታ ጥያቄ ውስጥ የቆየ ቢሆንም አሁን በገጠመው ችግር ምክንያት ከምርጫው ውድድር ውጪ ሆኗል።

ከዚህ ቀደምም የኦሮሞ ፌደራሊስte ኮንግረስ በአባላቱ መታሰርና በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ጽህፈት ቤቶቹ መዘጋትን እንደምክንያት በማቅረብ በምርጫው ላይ ለመሳተፍ እንደሚቸገር መግለጹ ይታወሳል።

የብልጽግና ፓርቲ ሕዝብ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ፓርቲዎቹ መንግሥት ጫና ያደርስብናል፣ አባላቶቻችንን ያስራል፣ ጽህፈት ቤታችንን ዘግቷል ሲሉ የሚያቀርቡትን ውንጀላ "መሰረት የሌለው" ሲሉ ከዚህ በፊት ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

በመጪው ግንቦት ወር መጨረሻና በሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ ከትግራይ ክልል በስተቀር በቀሪው የአገሪቱ አካባቢዎች በሚካሄደው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ ላይ የሚወዳደሩ 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም 125 የግል ዕጩዎች ለመወዳደር ተመዝግበዋል።

ባለፈው ሳምንት ደግሞ ሁለት ወር ያህል በቀረው ምርጫ ላይ ድምጽ የሚሰጡ የመራጮች ዝገባ መጀመሩን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አሳውቋል።