የተባበሩት መንግሥታት ኢትዮጵያ ቅሬታ ያቀረበችባቸው ኃላፊው ከአገር እንዲወጡ ወሰነ

አርማ ያለበት ልብስ የለበሰ የድርጅቱ ሠራተኛ

የፎቶው ባለመብት, UNHCR

የኢትዮጵያ መንግሥት ቅሬታ ያቀረበባቸው የተባባሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት ምክትል ተወካይ የሆኑት ማቲጂስ ሌ ሩቴ ድርጅቱ ከአገሪቱ እንዲወጡ መወሰኑ ተሰማ።

ምክትል ተወካዩ ሩቴ ላለፈው አንድ ዓመት ከሁለት ወር በኢትዮጵያ የድርጅቱ ምክትል ኃላፊ ሆነው በማገልገል ላይ የነበሩ ሲሆን መንግሥት ባቀረበባቸው ቅሬታ ምክንያት ተቋማቸው ከኢትዮጵያ አንስቶ ወደሌላ አገር እንዲዘዋወሩ ማድረጉን ቢቢሲ ከድርጅቱ ሠራተኞችና ከመንግሥት ምንጮች ተረድቷል።

ቢቢሲ ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው የዲፕሎማቲክ ምንጮቹ እንደተረዳው የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ተቋም ከፍተኛ ኃላፊ የነበሩት ግለሰብን ጨምሮ ሌሎች የተቋሙ ሠራተኞች ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል ከተከሰተው ቀውስ ጋር በተያያዘ ቅሬታ ማቅረቡን ገልጸዋል።

ከከፍተኛ ባለስልጣኑ በተጨማሪም አንዲት ሴት የተቋሙ ሠራተኛ ሌላዋ ቅሬታ የቀረባበቸው ግለሰብ ሲሆኑ ግለሰቧ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት ላይ ያሉ መሆናቸው ታውቋል።

ቢቢሲ ከተቋሙ ሠራተኞችና ከሌሎች ምንጮች ባደረገው ማጣራት ግለሰቧ ተቋሙ በአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ዙሪያ በሚሰራቸው ሥራዎች ላይ ከፍተኛ አስተባባሪ ናቸው። ባላቸው ኃላፊነትም በድርጅቱ አምስተኛ የስልጣን እርከን ላይ ያሉ ሰው መሆናቸውን ለመረዳት ችሏል።

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ መንግሥት ቅሬታ የቀረበባቸው ምክትል ኃላፊው በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ተቋም ውስጥ ከ25 ዓመት በላይ ማገልገላቸውን ቢቢሲ ያገኛቸው ይፋዊ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከዚህ ቀደምም በቡልጋሪያ የስደተኞች ተቋሙ ዋና ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል።

"በአጠቃላይ በየተመድ የስደተኞች ድርጅት ውስጥ ያሉ በርከት ያሉ ሠራተኞች ላይ ቅሬታችንን ካስገባን ሰንብተናል። በዚህም ሠራተኞቹ የሚጠበቅባቸውን የፖለቲካ ገለልተኝነት አላሟሉም የሚል ሃሳብ አለን" ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለልጣን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

እኚሁ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣን ጨምረውም በሠራተኞቹ ላይ የተነሳው የገለልተኝነት ጥያቄ በትግራይ ክልል ከተካሄደው ወታደራዊ ግጭት ጋር የተያያዘ መሆኑንም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ቢቢሲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ የሆኑትን አምባሳደር ዲና ሙፍቲን የጠየቀ ሲሆን ስለተባለው ነገር መረጃ እንደሌላቸው ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ድርጅት በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጥበት ከቢቢሲ ጥያቄ ቀርቦለት በተቋሙ ሠራተኛ ላይ ቅሬታ መቅረቡን አረጋግጧል።

"የኢትዮጵያ መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በአንድ ባልደረባችን ላይ አቤቱታቸውን አቅርበዋል" ሲል ድርጅቱ ለቢቢሲ በሰጠው የኢሜይል ምላሽ ላይ ገልጿል።

አክሎም "ተቋሙ ግለሰቡን ወደ ሌላ ቦታ የመቀየር ሥራ ሰርቷል፤ ይህ ግን ቀድሞውንም እየሰራንበት ከነበረው የመዋቅር ማሻሻል ተግባር ጋር የሚገናኝ ነው" ሲል ድርጅቱ ስለእርምጃው አስረድቷል።

ድርጅቱ በትግራይ ክልል ካጋጠመው ድንገተኛ ቀውስ በኋላ በክልሉ ያለውን ሥራ ለማጠናከር የውስጥ ምክክሮች ሲደረጉ እንደነበር እና የተቋሙን ሰው ኃይል በድጋሚ መልሶ ለማዋቀር እየተሰራ እንደበርም የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት ገልጿል።

በተመሳሳይ መንግሥት ባቀረበው አቤቱታ መሠረት ከአገር እንዲወጡ ተወስኗል ሲሉ ምንጮቻችን የገለጿቸው የድርጅቱ የፕሮጀክት አስተባባሪ ጉዳይን በተመለከተ ግን ተቋሙ ምንም አይነት አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።

በትግራይ ውስጥ የተከሰተውን ወታደራዊ ቀውስ ተከትሎ ከ70 ሺህ በላይ ሰዎች ድንበር ተሻግረው ወደ ሱዳን የገቡ መሆኑን የእርዳታ ድርጅቶች የገለጹ ሲሆን፤ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩት ደግሞ በክልሉ ውስጥ ተፈናቅለው እንደሚገኙ ተገልጿል።

የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት የክልሉን ዋና ከተማ ተቆጣጥሮ ጦርነቱ ማብቃቱን ካሳወቀ በኋላ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማትና ሌሎች የእርዳታ ድርጅቶች በትግራይ ውስጥ ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት መስመር እንዲከፈት ሲጠይቁ ቆይተዋል።

መንግሥት በቀረበለት ጥያቄ መሠረት የረድኤት ድርጅቶች ወደ ክልሉ ገብተው ለነዋሪዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ የፈቀደ ቢሆንም አስካሁን ድረስ ከፍተኛውን የእርዳታ አቅርቦት እየሰጠ እንደሚገኝና የረድኤት ድርጅቶቹ ድረሻ ዝቅተኛ መሆኑን ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣንት ገልጸዋል።

በግጭቱ ለተለያዩ ችግሮች ከተጋለጡት የትግራይ ክልል ነዋሪዎች በተጨማሪ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት የሚደግፋቸው ኤርትራውያን ስደተኞች የሚገኙባቸው መጠለያዎች ትግራይ ውስጥ እንደሚገኙ ይታወቃል።