በአሜሪካ የኒውክሌር ተቋም ትዊተር ላይ መልዕክት ያሰፈረው ታዳጊ ብዙዎችን አስደነገጠ

የድርጅቱ አርማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አንድ ታዳጊ የአሜሪካንን የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች በሚቆጣጠረው ተቋም የትዊተር ገጽ ላይ ለመረዳት ግልጽ ያልሆነ መልዕክት በማስፈሩ ምክንያት ግራ መጋባትና ፍርሃት ተፈጥሮ እንደነበረ ተገለጸ።

ነገሩ የተከሰተው ከጥቂት ቀናት በፊት ሲሆን ታዳጊው ምስጢራዊ የሚመስሉ ምንም ትርጉም የማይሰጡ የእንግሊዝኛ ፊደላትና ሥርዓተ ነጥቦችን ያሉበትን መልዕክት ሳያስበው በትልቁ ተቋም የትዊተር ሰሌዳ ላይ በማስፈሩ ነበር ብዙዎች ስጋት የገባቸው።

ይህን መልዕክት በርካቶች ከተመለከቱት በኋላ የተፈጠረው ስሜት የአገሪቱ ኒውክሌር ጦር መሣሪያዎችን የሚቆጣጠረው ወሳኝ ተቋም የመረጃ መረብ በኢንተርኔት ሰርሳሪዎች ቁጥጥር ስር ገብቶ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት ነበር።

ተቋሙ የአሜሪካ ኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች ጥበቃ የሚደረግላቸው ወሳኝ የጦር መሳሪያ የዕዝ ማዕከል ሲሆን የመረጃ መረቡ ደኅንነት አደጋ ላይ ከወደቀ ብሔራዊ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ ቀውስ ሊከስት ይችላል ተብሎ ይሰጋል።

የድርጅቱ አንደኛው መድረክ የማኅበራዊ መገናኛ የሆነው የትዊተር ገጹ ላይ ያልተጠበቀ ነገር ወጥቶ ሲገኝ እንግዳ የሆነውን መልዕክት የተመለከቱ ሰዎች፣ በተቋሙ ላይ አንዳች የመረጃ መረብ ጥቃት ሳይደርስ እንዳልቀረ በመገመት ስጋታቸውን ሲገልጹ ነበር።

ነገር ግን ክስተቱ እንደተሰጋው ሳይሆን የተቋሙን የሶሻል ሚዲያ ገጾች ከሚቆጣጠሩ ሠራተኞች መካከል የአንዱ ልጅ መነጋገሪያ የሆነውን መልዕክት ሳያስበው በድንገት እንዳሰፈረው በኋላ ላይ ታውቋል።

በትዊተር ገጹ ላይ የወጣው ጽሁፍም ";l;;gmlxzssaw" የሚል ነበር።

ትርጉም የሌላቸውን እነዚህ ፊደላትና ነጥቦች ምናልባት ምስጢራዊ ናቸው ብለው በርካቶች ቢጠረጥሩም ታዳጊው ሳያስበው ጣቶቹ የተጫናቸው ፊደላትና ምልክቶች ነበሩ።

መልዕክቱ በርካቶች ጋር ደርሶ ግራ መጋባትን ከፈጠረ እና መነጋገሪያ ከሆነ ከደቂቃዎች በኋላ ከተቋሙ ገጽ ላይ እንዲሰረዝ ተደርጓል።

የዜና ማሰራጫ ድረ ገጽ የሆነው "ዘ ዴይሊ ዶት" ተቋሙን ስለተፈጠረው ነገር ጠይቆ ክስተቱን ዘግቦታል።

ከቤቱ ሆኖ ሥራውን እያከናወነ የነበረው የተቋሙ የትዊተር ገጽ ተቆጣጣሪ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ክፍት አድርጎት የተፈጠረ ስህተት መሆኑን በመግለጽ ድርጅቱ ስለክስተቱ ምላሽ ሰጥቷል።

"የሠራተኛችን ታዳጊ ልጅ የመጻፊያ ቁልፎቹን እየተጫነች በምትጫወትበት ጊዜ ሳታስበው በድርጅታችን የትዊተር ገጽ ላይ መልዕክቱ ሊወጣ ችሏል" ሲል ተቋሙ ማብራሪያ ሰጥቷል።

የተቋሙ ቃል አቀባይም አንዳንድ ሰዎች የድርጅቱ የመረጃ መረብ በጠላፊዎች ቁጥጥር ስር ገብቷል በማለት ስጋታቸውን የገለጹት ሐሰት መሆኑንና እንዲህ አይነት ችግር እንዳልገጠማቸው አስተባብሏል።

የድርጅቱ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ በመረጃ መዝባሪዎች አለመጠለፉ ከታወቀ በኋላ በርካቶች እንዲህ ያለ ትልቅ ተቋም የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ በህጻናት እጅ ሊገባ የሚችልበት ዕድል እንዳለ ማወቃቸው አሳሳቢ መሆኑን አስተያየት ሰጥተዋል።