'የተናገርኩት ከአውዱ ውጪ ተወስዷል' አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

የፎቶው ባለመብት, MFA

የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ትናንት በሰጡት በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ስለኤርትራ የተናገርኩት ከአውዱ ውጪ ተወስዷል ሲሉ ተናገሩ።

አምሳደር ዲና ማክሰኞ ዕለት በሰጡት መግለጫ ላይ የኤርትራ ነጻነትን በሚመለከት የተናገሩበት አጭር ቪዲዮ በማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ ከተጋራ በኋላ በርካታ ኤርትራውያን ቅሬታቸውንና ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።

መነጋገሪያ የነበረው የአምባሳደሩ ንግግር "እያንዳንዱ ኤርትራዊ ቢጠየቅ ከኢትዮጵያ ጋር የተለዩበትን ቀን አያከብሩትም፤ አይወዱትም. . በኢትዮጵያም በኩል ተመሳሳይ ስሜት ነው ያለው። እንኳን ከኤርትራ ጋር አይደለም ከተቀሩት የጎረቤት አገራት ጋር አንድ ብንሆን ጥሩ ነው" የሚል ነው።

ይህንንም ተከትሎ በርካታ ኤርትራውያን በቪዲዮው ላይ የቀረበውን የቃል አቀባዩን ንግግር ተቃውመው የተባለው ነገር ትክክል እንዳልሆነና ለነጻነት ቀናቸው ያላቸውን ክብርና ፍቅር ገልጸዋል።

አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙት ቢኒያም በርሔ የተባሉት የኤርትራ ዲፕሎማትም ለዚሁ ምላሽ በሚመስል ሁኔታ የኤርትራ የነጻነት ቀን ከሁሉም የላቀ ዕለት መሆኑንና በአገር ቤትና በውጪ ያሉ ኤርትራውያን በድምቀት የሚያከብሩት ዕለት መሆኑን በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

አምባሳደር ዲና ንግግራቸውን ተከትሎ የተፈጠረውን ስሜትና የታየውን ምላሽ በተመለከተ ለቢቢሲ እንደገለጹት በጋዜጣዊ መግለጫው የተናገሩት ጉዳይ ከአጠቃላዩ የንግግራቸው አውድ ውጪ የተወሰደ ነው ብለዋል።

በሁለቱ አገራት መካከል የነበረው ቁርሾም ሆነ ጦርነት ህመም ያለው ያለው ነው ማለታቸውን ጠቅሰው፤ ኤርትራና ኢትዮጵያ በጦርነት ውስጥ ሆነው ተራርቀው ያሳለፉትን ጊዜ ሁለቱም ሕዝቦች አይወዱት ማለታቸውን ተናግረዋል።

"ይሁን እንጂ ኤርትራውያን ነፃነታቸውን አይፈልጉትም ማለት አይደለም" ሲሉ ንግግራቸው ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ መተርጎሙን ገልጸዋል።

ለኤርትራውያን፣ ለኤርትራ ነፃነት እና ኤርትራ ትልቅ አክብሮት እንዳላቸው የገለጹት አምባሳደር ዲና "አንዳንድ ሰዎች ንግግሩን ከአውዱ ውጪ ወስደው ስሜታዊ ያደርጉታል። ከዚያች መስመር በኋላ እኮ በምሥራቅ አፍሪካ ስላሉት አገራት መተሳሰርም ተናግሬአለሁ" ብለዋል።

"እንኳን እና ከኤርትራ ጋር አይደለም ከጂቡቲ፣ ከኬንያ፣ ከሶማሊያ፣ ከሱዳን ጋር ተሳስረን ምን አለ አንድ ብንሆን፤ ትልቁ ራዕይ እኮ እሱ ነው" ብለው መናገራቸውን ጠቅሰዋል።

በጋዜጣዊው መግለጫ ላይ ኢትዮጵያና ኤርትራ ያላቸውን ግንኙነት በተመለከተ ለተነሳው ጥያቄ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ መልስ ሲሰጡ፤ ሁለቱ አገራት ደም ባፋሰስ ጦርነት ውስጥ አልፈው ለሁለት አስርት ዓመታት በፍጥጫ ውስጥ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

አሁን ባላው ሁኔታ የአገራቱ ግንኙነት ተሻሽሎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መምጣቱ ትልቅ ነገር መሆኑንና ሁለቱ አገራት በተለያዩ ዘርፎች የሚያደርጉት ግንኙነትና ትስስር እየሰፋና እየዳበረ ይሄዳል ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ያለውን ግንኙነትና ትስስር ከኤርትራ ጋር ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ካሉ ሌሎች አገራት ጋር የበለጠ ማጠናከር እንደሚፈልግና ለዚህም አየሠራ መሆኑን አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።

ኤርትራ ለ30 ዓመታት ከተደረገ የነጻነት ትግል በኋላ ራሷን የቻለች አገር ከሆነች በመጪው ግንቦት 30ኛ ዓመቷን ታከብራለች።

ኤርትራ ከኢትዮጵያ ነጻ ከወጣች ከሰባት ዓመት በኋላ በሁለቱ አገራት መካከል ደም አፋሳሽና ከባድ ውድመትን ያስከተለ የድንበር ጦርነት ተካሂዶ ለ20 ዓመታት በጠላትንት መቆየታቸው ይታወሳል።

ከሁለት ዓመት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማሻሻል በወሰዱት እርምጃ ሠላም ወርዶ ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።

የኤርትራና የኢትዮጵያ ወዳጅነትን ለማጠናከር የሁለቱ አገራት መሪዎች ባለፉት ዓመታት ተደጋጋሚ ጉብኝቶችን በሁለቱ አገራት ውስጥ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

በትግራይ ክልል ውስጥ ከተካሄደው ወታደራዊ ግጭት ጋር በተያያዘም ኤርትራ የኢትዮጵያ መንግሥትን በመደገፍ ወታደሮቿን አሰማርታ የህወሓት ኃይሎችን ከመውጋቷ በተጨማሪ ሠራዊቷ ግድያን ጨምሮ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን እንዲሁም የንብረት ዘረፋና ውድመትን ፈጽሟል በሚል በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ሲከሰስ ነበር።

ሁለቱ አገራት በግጭቱ ውስጥ የኤርትራን ተሳትፎ ሲያስተባብሉ የቆዩት ቢሆንም ከሳምንት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ለአገሪቱ ፓርላማ የኤርትራ የደኅንነት ስጋት ስለነበረባት ሠራዊቷ ድንበር አልፎ መግባቱን አረጋግጠው ነበረ።

ይህንንም ተከትሎ ባለፈው ሳምንት ለጉብኝት ወደ አሥመራ የሄዱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ኤርትራ ሠራዊቷን ከኢትዮጵያ እንድታስወጣ ከፕሬዝደናት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር መስማማታቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።