በምዕራብ ወለጋ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት 28 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

አርማ

የፎቶው ባለመብት, Oromia Communication Bureau

በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት 28 ሰዎች መገደላቸውን የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ገለጸ።

ማክሰኞ መጋቢት 21/2013 ዓ.ም በዞኑ ውስጥ በሚገኘው ባቦ ገንቤል ወረዳ በቦኔ ቀበሌ የተፈጸመውን ጥቃት ኦነግ-ሸኔ የተባለው ቡድን እንደፈጸመው የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል አራርሳ መርዳሳ አመልክተዋል።

ቡድኑ በጥቃቱ ዕለት ከምሽቱ ሦሰት ሰዓት ላይ ከ50 በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎችን ሰብስቦ "ጭፍጨፋ ፈፅሟል" ሲሉ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

በጥቃቱ ከተገደሉት 28 ሰዎች መካከል 16ቱ ወንዶች ሲሆኑ 12ቱ ደግሞ ሴቶች መሆናቸውን የተናገሩት በተጨማሪ 12 ሰዎችም ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል።

ጥቃቱን በተመለከተ መግለጫ ያወጣው የኦሮሚያ ክልል መንግሥትም "አሰቃቂና ዘግናኝ" ያለውን ጥቃት የፈጸመው ኦነግ-ሸኔ እንደሆነ አመልክቷል።

የፖሊስ ኮሚሽነሩ አራርሳ መርዳሳም ከጥቃቱ በኋላ የክልሉ ፖሊስ በአካባቢው በወሰደው እርምጃ የታጣቂው ቡድን አባላት ላይ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል።

የክልሉ መንግሥት መግለጫ በጥቃቱ ምን ያህል ሰዎች እንደተገደሉና የጸጥታ አካላት በወሰዱት የአጸፋ እርምጃ በጥቃት ፈጻሚዎቹ ላይ ስለደረሰ ጉዳት ያለው ነገር የለም።

ጨምሮም ቡድኑን የህወሓት ተላላኪ በመሆን በአካባቢው የመንግሥት መዋቅርን በማፍረስ በገጠርና በከተማ በመንግሥት አመራሮችና በሰላማዊ ዜጎች ላይ ከዚህ በፊት "ዘግናኝ የሽብር ጥቃቶችን ሲፈፅም ቆይቷል" ብሏል።

ቡድኑ በሚፈጽመው ጥቃት የቀበሌና የክልል አመራሮችን ጨምሮ በርካታ ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውን ያመለከተው የክልሉ መንግሥት መግለጫ፤ በጥቃቶቹ የግልና የመንግሥት ንብረቶች መውደማቸውንም ገልጿል።

መንግሥት "የኦነግ ሸኔ እኩይ ተግባር ለማስወገድ በወሰደው የሕግ የበላይነትን የማስከበር እርምጃ" ቡድኑ እየተዳከመ መሆኑን በመጥቀስ ነገር ግን "በሞትና በህይወት መካከል ሆኖ የጥፋት ሴራውንና እርምጃውን ቀጥሏል" ብሏል።

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ውስጥ ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር ተለይቶ የወጣውና መንግሥት ኦነግ-ሸኔ የሚለው ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን እንደሚንቀሳቀስ ይነገራል።

በዚህ አካባቢ በተለያዩ ጊዜያት በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ሠላማዊ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን በርካቶች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው እንደተፈናቀሉ ሲዘገብ ቆይቷል።

በተጨማሪም በአካባቢው ባሉ የመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ የሚሰሩ ሰዎችና፣ የጸጥታ አካላትና አመራሮች በተለያዩ ጊዜያት በተፈጸሙ ጥቃቶች ሰለባ ሆነዋል።

ለእነዚህ ጥቃቶችም መንግሥት በኩምሳ ድሪባ (ጃል መሮ) ይመራል የሚባለው ኦነግ-ሸኔን ተጠያቂ ሲያደርግ ቡድኑ ግን ግድያዎቹን አለመፈጸሙን ሲያስተባብል ቆይቷል።

መንግሥት ታጣቂ ቡድኑን ከአካባቢው ለማስወገድ በተለያዩ ጊዜያት በወሰዳቸው እርምጃዎች በርካታ አባላቱን መግደሉንና መማረኩን ሲገልጽ መቆየቱ ይታወሳል።

የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር እንዳሉት ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ የጸጥታ አካላት በኦነግ-ሸኔ ላይ በተወሰዱት እርምጃ 1947 አባላቱ ሲገደሉ 489ቱ ደግሞ መማረካቸውን ተናግረዋል።

በዚህም ከጥቂት ወራት በፊትም የቡድኑ መሪ የሆነው ኩምሳ ድሪባ በጸጥታ ኃይሎች መገደሉ የተነገረ ቢሆንም ከቀናት በፊት በአልጀዚራ ቴሌቪዥን ላይ መታየቱ አነጋጋሪ ሆኗል።