የሃጫሉን ግድያ ተከትሎ በተከሰተ ሁከት ወቅት ወንጀል በፈጸሙ ላይ እስከ 20 ዓመት እስር ተፈረደ

ከሃጫሉ ግድያ በኋላ በተከሰተ ሁከት ከፍተኛ የንብረት ውድመት ከተከሰተባቸው ስፍራዎች መካከል ሻሸመኔ ከተማ አንዷ ነች

የፎቶው ባለመብት, -

የምስሉ መግለጫ,

ከሃጫሉ ግድያ በኋላ በተከሰተ ሁከት ከፍተኛ የንብረት ውድመት ከተከሰተባቸው ስፍራዎች መካከል ሻሸመኔ ከተማ አንዷ ነች

የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በተከሰተው ሁከት በኦሮሚያ ክልል በተፈጸሙ የግድያ ወንጀሎች ውስጥ የተሳተፉ ግለሰቦች እንደተፈረደባቸው የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታወቀ።

ዐቃቤ ሕግ እንዳለው በኦሮሚያ ክልል በወቅቱ በተከሰተው ሁከትና ብጥብጥ ውስጥ የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶችን በፈጸሙ ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ በማድረግ በስድስት ዞኖች ውስጥ ከ3,300 በላይ ተጠርጣሪዎች በሕግ እንዲጠየቁ ተደርጓል።

አቃቤ ሕግ በመግለጫው ላይ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ አምስት ሰዎችን በመግደልና በንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ ወንጀል የተሳተፉ ተከሳሾች ላይ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከአንድ አስከ 20 ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራትና የገንዘብ ቅጣት መጣሉን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ገልጿል።

ባለፈው ዓመት ሠኔ ወር ላይ አዲስ አበባ ውስጥ የተገደለውን የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ሞት ከተሰማ በኋላ በዋና ከተማዋን በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በሰዎችና በንብረት ላይ ጥቃት መፈጸሙ ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ በርካታ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን የግልና የመንግሥት ንብረቶች ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች በሚሊዮኖች ብር የሚገመት ንበረት ወድሟል።

በዚህ ሁከት ውስጥ የተሳተፉ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ በወቅቱ መንግሥት አሳውቆ ነበር።

ኢሰመኮና ሌሎች ወገኖች ጥቃቱን ተከትሎ ባወጧቸው ሪፖርቶች እንዳሉት ሁከቱ በተከሰተባቸው ሦስት ቀናት ውስጥ ከ120 በላይ ሰዎች ሲገደሉ ቢያንስ 500 በሚሆኑ ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ደርሷል።

ዐቃቤ ሕግ ጨምሮም በሁከቱ ውስጥ በተፈጸሙ ወንጀሎች ተጠርጥረው ከተከሰሱት ውስጥ 90 በመቶ በሚሆኑት ላይ የቅጣት ውሳኔ እንደተላለፈና በተመሳሳይም 90 በመቶ ያህል ምስክሮች ችሎት ቀርበው የምስክርነት ቃላቸውን መስጠታቸውን አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ሁከቱን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ቦታዎች የተፈጸሙ ጥቃቶችን በተመለከተ ባደረገው ምርመራ "በጥቃቱ በተሳተፉ ሰዎችና ቡድኖች በሲቪል ሰዎች ላይ የተፈጸሙት ጥቃቶች በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ባሕርያትን የሚያሟሉ ናቸው" ማለቱ ይታወሳል።

ኮሚሽኑ ጨምሮም ለተከታታይ ጊዜያት ቢያንስ በ40 የተለያዩ ቦታዎች በአብዛኛው በቡድን የተደራጁ ሰዎች ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ በርካታ ሰላማዊ ሰዎችን በአሰቃቂ ሁኔታ መግደላቸው፣ የአካልና የሥነ ልቦና ጉዳት ማድረሳቸው፣ ንብረት ማውደማቸውና ነዋሪዎችን ማፈናቀላቸው ጠቅሷል።

ጥቃቱ በከፊል በብሔርና በሐይማኖት ላይ፣ በከፊል ደግሞ ብሔርና ሐይማኖት ሳይለይ ሰላማዊ ነዋሪዎችን ላይ የተፈጸመ የወንጀል ድርጊት መሆኑ የገለጸው ኢሰመኮ፤ በወንጀል ድርጊቱ ሲሳተፉ የነበሩት ሰዎች፤ ተግባራቸው ስልታዊና የተቀናጀ ወይም የሰፊ ጥቃት አካል መሆኑን በማወቅ የተሳተፉበት እንደነበር ገልጾ ነበር።