የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ውሻ ዳግም የዋይት ሐውስ ሠራተኛ ነከሰ

ጆ ባይደን ከሜጀር ጋር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ሜጀር የተሰኘው የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ውሻ ዳግም የዋይት ሐውስ ሠራተኛ መንከሱ ተሰማ።

ሜጀር ከዚህ ወር ቀደም ብሎ በዋይት ሐውስ ሰው በመንከሱ የተነሳ ለስልጠና ወደ ዴልዌር ተልኮ የነበረ ቢሆንም በተመለሰ ማግስት ሌላ ሠራተኛ መንከሱ ተነግሯል።

የቀዳማይት እምቤት ጂል ባየደን ቃል አቀባይ "ተገቢውን ጥንቃቄ ለማድረግ ሲባል" የተነከሰው ግለሰብ ወደ ሥራ ከመመለሱ በፊት በዋይት ሐውስ የሕክምና ቡደን ክትትል እየተደረገለት እንደሆነ ገልጸዋል።

ሜጀር ጆ ባይደን ካሏቸው ሁለት የጀርመን ዝርያ ካላቸው ውሾች መካከል በእድሜ ትንሹ ሲሆን ወደ ዋይት ሐውስ የገባ የመጀመሪያው በማደጎ የተወሰደ ውሻ ነው ተብሏል።

ባይደን "በጣም ተወዳጅ ውሻ ነው" ሲሉ ያንቆለጳጵሱታል።

የጂል ባይደን ቃል አቀባይ ሚሼል ላሮሳ ሰኞ እለት ክስተቱ የተፈጠረው ሜጀር ከአዲሱ አካባቢ ጋር ራሱን ለማላመድ እየጣረ ባለበት ወቅት በአጠገቡ የሚያልፍን ግለሰብ በመንከሱ ነው ብላለች።

ሲኤንኤን ውሻው የብሔራዊ ፓርክ ሠራተኛ የሆነ ግለሰብ መንከሱንና በዚህም የተነሳ ግለሰቡ ሕክምና ለመከታተል ሥራ ማቆሙን ዘግቧል።

የብሔራዊ ፓርክ አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ለሲኤን ኤን ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።

በመጋቢት ወር የጆ ባይደን ሁለቱ ውሾች ሜጀርና ቻምፕ ሠራተኞችን መንከሳቸውን ተከትሎ ዊልሚንግተን ዴልዌር ወደሚገኘው የባይደን ቤተሰቦች ቤት ተወስደው ነበር።

ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ ግለሰብ ለሲኤንኤን እንደገለፀው ሜጀር የዋይት ሐውስ ሠራተኞችንና የደኅንነት ሰዎችን በሚያይበት ወቅት ይጮሃል ይዘላል።

ፕሬዝዳንት ባይደን ሜጀር በርካታ ሰው በዙሪያው ከመኖሩ ጋር የተፈጠረበትን ስሜት እየተላመደ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ለኤቢሲ ጉድ ሞርኒንግ አሜሪካ ፕሮግራም ላይ በየአቅጣጫው በዞረ ቁጥር የማያውቃቸው ሰዎች ሲንቀሳቀሱ ሲያይ ለመከላከል ሲል እንደሚጮህ አስረድተዋል።

"በዋይት ሐውስ ያሉ 85 በመቶ ሠራተኞች ይወዱታል። እርሱም ጭራውን እያወዛወዘ ይልሳቸዋል። ነገር ግን እንደተረዳሁት አንዳንድ ሰዎች በተፈጥሯቸው ውሾች ይፈራሉ" ብለዋል።

ባይደን የሚያሳድጉት ሜጀር ሦስት ዓመቱ ሲሆን ቻምፕ ግን ፕሬዝዳንት ባይደን የኦባማ ምክትል ሳሉ አብሯቸው በቤተመመንግሥት ውስጥ ነበር ተብሏል።